
ከ 6 ሰአት በፊት
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ወትሮም ፍጥጫ የማይለየው ከምዕራባውያን ጋር የነበራት ግንኙነት ፍጹም ተበላሽቷል።
ለዓመታት በጥርጣሬ እና በውጥረት ውስጥ የቆየው የሩሲያ እና የምዕራባውያኑ ግንኙነት ዩክሬን ውስጥ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ለይቶለት ወደ ግጭት እንዳይገባ ስጋት ከተፈጠረ ሦስት ዓመታት ሆኖታል።
በ2014 ዓ.ም. ሩሲያ 200 ሺህ ወታደሮቿን አዝምታ ዩክሬንን ስትወር ምዕራባውያን ላይ ስጋት በመፈጠሩ በአንድንት ሆነው ዩክሬንን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው በማስታጠቅ በተዘዋዋሪ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።
በሦስት ዓመት ውስጥ በተካሄደው ጦርነት እስካሁን ከዩክሬን እና ከሩሲያ በኩል አንድ ሚሊዮን ያህል ሰዎች ሞተዋል ወይም ቆስለዋል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ፊት ለፊት ከምታደርገው ጦር ባሻገር ከምዕራባውያን ጋር በሌላ ግንባር የአሻጥር ጦርነት እያደረገች ነው ሲል የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ማኅበር (ኔቶ) ያምናል።
ኔቶ “ድብልቅ ጦርነት” (ሃይብሪድ ዋርፌር) በሚል የሰየመው የሩሲያ ጥቃት ዋነኛው ዒላማ ያደረገው የምዕራብ የአውሮፓ አገራትን ሲሆን፣ በዚህም ሌሎች ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ ለማስቆም በማሰብ የሚፈጸም ነው።
ይህ ድብልቅ ጦርነት አንድ ተቀናቃኝ መንግሥት ፈጻሚው በማይታወቅ እና ለማስተባበል የሚቻ፣ ነገር ግን በአብዛኛው በጣም አጠራጣሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚፈጸም ነው። በተለይም የባላንጣን የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመጉዳት በቂ ነው። ነገር ግን ፈጻሚው ሊታወቅ የሚችል የጦርነት ድርጊት ባለመሆኑ ጠላትን ለመለየት አዳጋች ነው።
ለእንዲህ ያለው ጥቃት በዋናነት ተጋላጭ የሆኑት በጥልቁ የባሕር ወለል ላይ የተዘረጉት የኃይል፣ የኢንተርኔት እና መሰል ግዙፍ እና ወሳኝ የማስተላለፊያ ቱቦዎች እና ገመዶች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ወደ 600 የሚጠጉ ኬብሎች ኤሌክትሪክ እና መረጃን በሰፊዎቹ ውቅያኖሶች እና ባሕሮች ወለል ላይ ተዘርግተው ያጓጉዛሉ።
እነዚህ 870,000 ማይሎች (1.4 ሚሊዮን ኪ.ሜ) የሚረዝሙት መስመሮች በባሕር ዳርቻ ላይ ወደ ሚገኙ በይፋ ወደ ሚታወቁ እና ወደ ምሥጢራዊ ስፍራዎች ይደርሳሉ። አብዛኞቹ የመረጃ አመላላሽ ኬብሎች ደግሞ ሁሉንም የበይነ መረብ መረጃዎችን የማስተላላፍ ሚና አላቸው።
በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት (ሩሲ) ከባሕር ወለል ላይ የሚዘረጉ የኃይል መስመሮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሲድሃርት ካውሻል “ወደ ባሕር ጠልቀው የሚገቡ ሰርጓጅ መርከቦች ኬብሎችን በጥልቅ ሊቆርጡ ይችላሉ፤ ይህም ጥገናውን እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል” የመረጃ ምዝበራ ሊፈጸምም እንሚችል ያመለክታሉ።
እነዚህ በባሕር ወለል ላይ ተዘርግተው መረጃ እና ኤሌክትሪክ በአገራት መካከል የሚያስተላልፉት ገመዶች ለአውሮፓ አገራት እንደ ወሳኝ የደም ሥር የሚቆጠሩ ናቸው።
- ከ10 ዓመት በኋላ ከሐማስ እስር ነጻ የወጣው ቤተ-እስራኤላዊ አቬራ መንግሥቱ ማን ነው?23 የካቲት 2025
- ዓለምን የሚዞረው ኢትዮጵያዊ ከዩቲዩብ ምን ያህል ያገኛል?22 የካቲት 2025
- በምሥራቅ እስያ በርካቶች ሃይማኖታቸውን መተው ወይም መቀየርን ለምን መረጡ?23 የካቲት 2025

ፈጻሚው በውል የማይታወቀው ጥቃት
ባለፉት ወራት በባልቲክ ባሕር ሥር በተዘረጉት ገመዶች ላይ በተደጋጋሚ የመቆረጥ አደጋ አጋጥሟል። ክስተቱም በድንገት የተከሰተ አደጋ ሳይሆን ወሳኝ በሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም አሻጥር አካል ነው ተብሎ ይታመናል።
ባለፈው ኅዳር በባልቲክ ባሕር ሥር ከጀርመን ወደ ፊንላንድ እንዲሁም ከስዊዲን ወደ ሊቱዋኒያ የተዘረጉ የፋይበር ኦብቲክ ኬብሎች ላይ የመቆረጥ አሻጥር እንደተፈጸመባቸው ጀርመን አመልክታለች።
በዚያው ወር መጨረሻ ላይ የፊንላንድ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች በፊንላንድ እና በኢስቶኒያ መካከል የተዘረጋን መስመር ቆርጣለች ብለው የጠረጠሯትን የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከብን በቁጥጥር ሥር አውለው ነበር።
የድብልቅ ጦርነት ሌላኛ ምሳሌ ነው ተብለው የሚጠረጠሩት ጥቃቶች ደግሞ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በዩናይትድ ኪንግደም፣ በጀርመን እና በፖላንድ ውስጥ የሚገኙ የመልዕክት አድራሽ ድርጅቶችን ዒላማ አድርገው በተላኩ እሽጎች ምክንያት የተፈጠሩ የእሳት አደጋዎች ይጠቀሳሉ።
የፖላንድ ዐቃቢያነ ሕጎች እነዚህ ክስተቶች ወደ አሜሪካ እና ካናዳ በሚበሩ አውሮፕላኖች ላይ ሊፈጸሙ ለታቀዱ አሻጥሮች የቅድሚያ ሙከራዎች ናቸው ብለው ያምባሉ።
ሩሲያ ከእነዚህ የአሻጥር ድርጊቶች ጀርባ የለሁበትም በማለት ብታስተባብልም፣ ስዊዲንን እና ቼክ ሪፐብሊክን ጨምሮ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ውስጥ በሚገኙ መጋዘኖች እና የባቡር ትስስር መስመሮች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ትጠረጠራለች።
እነዚህ ክስተቶች አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት የሩሲያ ወታደራዊ የደኅነንት ተቋም ዩክሬንን በሚረዱ አገራት ላይ ምሥጢራዊ የጥቃት ዘመቻ ሳይከፍት አይቀርም ብለው እንዲደምድሙ አድርጓቸዋል።

ሩሲያ ከባሕር በታች ያላት አቅም
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢኒስቲቲዩት (ሩሲ) ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሲድሃርት ካውሻል እንደሚሉት በባሕር ላይ ለግዳጅ የሚሰማራው የሩሲያ ወታደራዊ መዋቅር በተለያዩ ደረጃዎች የተከፋፈለ እና ሚናውም የተለያየ ነው።
ጥልቅ ባልሆኑ የውሃ ከፍሎች ላይ ለሚካሄዱ ተልዕኮዎች ‘ስፔትስናዝ’ ወይም ልዩ ኃይል፣ የወታደራዊ ደኅንንት ክፍል እና የሩሲያ ባሕር ኃይል ኃላፊነቱን ይወስዳሉ።
ነገር ግን በጥልቅ የውቅያኖስ ክፍሎች ውስጥ መረጃዎችን በመሰብሰብ አሻጥሮችን ይፈጽማል የሚባለው በቀጥታ ለፕሬዝዳንት ፑቲን እና ለመከላከያ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የጥልቅ ባሕር ምርምር ዋና መምሪያ የተባለው ከፍል ነው።
ይህ ክፍል መርከቦችን በመጠቀም በባሕር ውስጥ የተዘረጉ ገመዶች እና ከነፋስ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች በየትኞቹ የባሕር ዳርቻዎች ላይ እንደሚገኙ መረጃዎችን ያሰባስባል። እንዲሁም በጥልቅ ባሕር ውስጥ ለሚካሄዱ ተልዕኮዎች ግዙፍ የባለስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤል ተሸካሚ ሰርጓጅ መርከቦችን ጥቅም ላይ ያውላል።
ተመራማሪው ጨምረውም ሩሲያ በሺዎች ሜትር ጥልቀት ከባሕር ወለል ላይ አስፈላጊውን ተግባር ሊፈጽሙ የሚችሉ እጅግ ዘመናዊ ሰርጓጅ መርከቦች እና የሠለጠኑ የባሕር ኃይል መኮንኖች እንዳላትም አመለክተዋል።
ጥልቅ በሆነው የውቅያኖስ ክፍል ውስጥ ምን እንደተቀመጠ ወይም ጠላቂ መርከቦቹ ምን እያከናወኑ እንደሆነ ማወቅ ለአሜሪካ ባሕር ኃይል እንኳን በእጅጉ አዳጋች ይሆንበታል።
በቻታም ሐውስ የሩሲያ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ኪር ጊልስ ይህ ከባሕር ወለል ላይ በተዘረጉ ገመዶች ላይ የሚፈጸመው አሻጥር መታየት ያለበት “እንደ ተናጠል የአጋጣሚ ክስተቶች ሳይሆን፣ ሩሲያ የግንኙነት መስመሮችን እና ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ አድርጋ የምትፈጽመው ሁሉን አቀፍ ጥቃት አካል ሆኖ ነው” ይላሉ።
ሩሲያ ከባሕር ሥር በተዘረጉት ኬብሎች እና የግንኙነት መስመሮች ላይ ትኩረት ያደረገችው “የመረጃ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም የመረጃ ለውውጥን ለማደናቀፍ በማለም ነው” መሆኑን የጥቃቱ ዒላማ በርካታ አገራትን ማድረጉን ገልጸዋል።

ምዕራባውያንን የሚያስጨንቀው የሩሲያ ዝግጅት
ተደጋጋሚ የባሕር ሥር ገመዶች መሠረተ ልማት መቆረጥ ያጋጠማቸው የፊንላንድ ባለሥልጣናት ለአሻጥሩ ሩሲያን በመጠርጠር ብቻቸውን አይደሉም።
ባለፈው ኅዳር ‘ያንታር’ የተባለችው የሩሲያ የቅኝት መርከብ “የዩናይትድ ኪንግደም ወሳኝ የባሕር ሥር መሠረተ ልማት በተዘረጋበት አካባቢ ስትቀዝፍ” መታየቷን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄንሊ ተናግረዋል።
ባለፈው ጥር ወር ደግሞ መርከቧ ተመሳሳይ ቅኝት ማድረጓን የብሪታኒያ ባሕር ኃይል ሪፖርት አድርጓል። የመከላከያ መሥሪያ ቤቱም መርከቧ “የደኅንነት መረጃ እያሰባሰበች እና የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ሥር መሠረተ ልማት አቀማመጥን” ለመለየት ጥቅም ላይ መዋሏን አመልክቷል።
የመከላከያ ሚኒስትሩም ይህ ድርጊት “እየጨመረ የመጣው የሩሲያ ትንኮሳ ሌላኛው ማሳያ ነው” ብለዋል።
ለንደን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ የቅኝት መርከቧን በተመለከተ በዩናይትድ ኪንግደም በኩል እየቀረበ ያለውን ክስ “ሙሉ ለሙሉ መሠረተ ቢስ” በማለት ውድቅ አድርጎታል።
ጨምሮም “በባልቲክ እና በሰሜን ባሕር ቀጣና ያለው ውጥረት የበለጠ እንዲባባስ ለማድረግ” በዩናይትድ ኪንግደም እና በአጋሮቿ በኩል “እየጨመረ የመጣ ፀረ ሩሲያ” አመለካከት ውጤት ነው ሲል ከሷል።
ደራሲ እና በሩሲያ ጉዳዮች ላይ ባለሙያ ሆኑት ኤድዋርድ ሉካስ እንደሚሉት “ሩሲያውያኑ ምናልባትም አስካሁን ከውሃ በታች በተዘረጉት ኬብሎች እና የኃይል ማስተላላፊያ ቱቦች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ እየተጠባበቁ የሚገኙ የባሕር ውስጥ ድሮኖቻቸውን በባሕር ወለል ላይ ቦታ ቦታ አስይዘው ሊሆን ይችላል። የቅኝት መርከባቸው ያንታር በባሕር ወለል ላይ ለዓመታት ምን ስትሠራ እንደቆየች የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በዓለም ዙሪያ ከባሕር ሥር ያሉ ኬብሎች እና ቱቦዎች “ከንቱ በሆነ መተማመን” ላይ በመመሥረት የተዘረጉ ናቸው የሚሉት ሉካስ፤ እነዚህ መሠረተ ልማቶች “የተቀናቃኝ አገር ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ፈጽሞ አስበን አናውቅም፣ የቸልተኝነታችንን ውጤት አሁን እያየነው ነው” ብለዋል።
ይህንን በሩሲያ በኩል እየተፈጸመ እና ወደፊትም እየከፋ ሊሄድ ይችላል የሚሉትን ከባሕር ሥር የተዘረጉትን መሠረተ ልማቶች የመጉዳት ጥቃትን ለማስቆም ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ለእነሱም [ለሩሲያውያ] ጭምር ከባድ መሆኑን በማሳየት ከድርጊታው እንዲቆጠቡ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ነው ይላሉ።

የማንቂያ ደወል
ምንም እንኳን ሩሲያ በባሕር ሥር በተዘረጉት መሠረተ ልማቶች ላይ በተደጋጋሚ በተከሰቱት ጥቃቶች ውስጥ እጇ እንደሌለበት ብትገልጽም፣ ኬብሎቹ እና ቱቦዎቹ ካሉበት ቦታ አንጻር በአካል ጥበቃ ማድረግ አስቸጋሪ ነው።
እየተፈጸሙ ያሉት ጥቃቶች ወሳኝ የሆኑት የመሠረተ ልማት መስመሮች ከመሆናቸው አንጻር የሚደረግላቸው ጥበቃ ከሚገባው በታች መሆኑን የሚያመለክት የማንቂያ ደወል ሆነዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የሩሲያ ድብልቅ የጦርነት ዘዴ በርካታ ልምድ እንድታገኝ አድርጓታል። በዚህም የጥቃቱን ተጽእኖ፣ ዒላማ የሆኑት አገራት ምላሽ፣ በክስተቱ ላይ ምርመራ የማድረግ ብቃት እና ከተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ብዙ ትምህርት እንደተገኘበት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከሚፈጸሙ ትልዕኮዎች አንጻር ሩሲያ ያዳበረችው ልምድ ጦርነት በሚከሰት ጊዜ ተጨማሪ የጥቃት አማራጮችን እድትለይ አስችሏታል። ይሆናል ተብሎ የማይታሰበው ጦርነት ቢከሰት ሩሲያ በአውሮፓ ምጣኔ ሀብት ላይ እና በሕዝቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ከባድ ጉዳትን የሚያደርስ አቅም እንዳገኘች ይታሰባል።
በዚህም ጉዳቱ ከባሕር ሥር ባሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ መጠነ ሰፊ ቀውስን የሚያስከትል መሆኑን በቻታም ሐውስ የሩሲያ ባለሙያ የሆኑት ኪር ጊልስ በመጥቀስ “ሩሲያ ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ሁሉንም ርቀቶችን በሙሉ ልትጓዝ ያስችላታል” ይላሉ።
“ይህም በቅጥረኞች አማካይነት የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ የመረጃ መረብ ጥቃቶች፣ የበይነ መረብ አደገኛ ቫይረሶች በስፋት መሠራጨት፣ ተቀጣጣይ ነገሮችን ወደ አየር መንገዶች ማስገባት፣ እንዲሁም ጦርነት በሌለበት እና ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳይኖር ከሺዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚፈጸሙ የሚሳዔል ጥቃቶች ጭምር ሊያጋጥሙ ይችላሉ።”
ነገር ግን በእነዚህ ከባሕር ወለል ላይ የተዘረጉትን ወሳኝ ኬብሎች ላይ የሚፈጸሙት አሻጥርን ለመከላከል ምዕራባውያን የሚያደርጉት ጥረት በቭላድሚር ፑቲን ከምትመራው ሩሲያ ጋር ከሚያደርጉት ፍልሚያ ውስጥ አንደኛው ግንባር ነው።