ዘለንስኪ፣ ትራምፕ ከመጡ በኋላ በከፍተኛ የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል
የምስሉ መግለጫ,ዘለንስኪ፣ ትራምፕ ከመጡ በኋላ በከፍተኛ የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

ከ 5 ሰአት በፊት

የዩክሬኑ ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሥልጣን መልቀቃቸው አገራቸው የኔቶ አባል ለመሆን የሚረዳ ከሆነና ለሰላም በር የሚከፍት ከሆነ ያን ለማድረግ ዘግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።

ይህን የተናገሩት ትናንት እሑድ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የከፈተችበት 3ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

‘ሰላም የሚያመጣ ከሆነና የኔቶ አባል የሚያደርገን ዕድል ካለ ስልጣኔን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ነኝ’ ብለዋል።

ይህ የዘለንስኪ አስተያየት የተሰነዘረው ዶናልድ ትራምፕ ዘለንስኪን ‘አምባገነን’ ብለው ከወረፏቸው በኋላ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ዘለንስኪን “ያለ ምርጫ ሥልጣን የተቆናጠጡ አምባገነን” ብለዋቸው ነበር።

በዚህ ሳያበቁ ‘ዘለንስኪ በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት የሌላቸው’ ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።

በግንቦት 2019 በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ዘሌንስኪ በትራምፕ አስተያየት “እምብዛምም አልተናደድኩም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አክለውም “በዛሬ የዩክሬን ደኅንነት ላይ አተኩራለሁ፤ መቼስ ለዐሥርታት በሥልጣን ላይ አልቆይም።” ብለዋል።

በዩክሬን አገሪቱ ጦርነት ላይ ስላለች በማርሻል ሕግ ምርጫ ታግዷል።

አሜሪካ በዩክሬን ላይ ፊቷን ማዞሯን ተከትሎ ዘለንስኪ በተከታታይ የምዕራብ አገራትን እርዳታ እንዲለግሷቸው እየወተወቱ ነው።

ዛሬ ሰኞ ከበርካታ ምዕራባውያን መሪዎች ጋር በአካልና በስልክ ይገናኛሉ።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ንግግራቸው ትኩረት የሚያደርገው ዩክሬን በድኅረ ጦርነት እንዴት የደኅንነት ከለላ ታግኝ? በሚለው ርእስ ዙርያ ነው።

አገራቸው ኔቶን የምትቀላቀልበት ዕድልም በውይይቱ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል።

ዘለንስኪ፣ አሜሪካን በተመለከተ ከአስታራቂነት ሚናዋ ባሻገር አጋራቸው እንድትሆን ምኞታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ሚና “በእርግጥ ከሽምግልና በላይ እንዲሆን እፈልጋለሁ…ሽምግልና ብቻውን በቂ አይደለም” ብለዋል፤ ዘለንስኪ።

በአንጻሩ አሜሪካ ዩክሬንን ገሸሽ ያደረገ የሰላም ንግግርና ድርድር በሳኡዲ አረቢያ ጀምራለች።

ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነት በአጭር ጊዜ እንዲቆም አበክረው ይሻሉ።

ይህም ብቻ ሳይሆን አገራቸው አሜሪካ በባይደን አስተዳደር ለዩክሬን የሰጠችውን ‘ግማሽ ትሪሊዮን’ ዶላር እርዳታ ዩክሬን መልሳ እንድትከፍል እየጠየቁ ነው።

ዘለንስኪ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነት ገንዘብ ከአሜሪካ እንዳልተሰጣቸውና በድምሩ100 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደተሰጣቸው፣ ያም ቢሆን ብድር ሳይሆን እርዳታ እንደነበረ ነው የሚናገሩት።

የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ለዩክሬን ለሰጠችው ወታደራዊ ዕርዳታ በምላሹ የዩክሬን የተፈጥሮ ውድ ማዕድን እንዲሰጠው ይሻል።

ዘለንስኪ በበኩላቸው፣ “ከትውልድ ወደ ትውልድ ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ” ላይ ስምምነት ፊርማቸውን እንደማያኖሩ ተናግረዋል።

ሆኖም በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ጋር ንግግር እንዳልተቋረጠ ጠቁመዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት እንዳሉት ገንዘቡን በከበረው ማዕድን መልክ “ለመክፈል ዝግጁ ነን” ነገር ግን ዋሽንግተን በመጀመሪያ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ይህን ጦርነት እንዲያበቃ” ማድረግ አለባት ብለዋል።

ከዚህ በሻገር አሜሪካ ለዩክሬን የደኅንነት ዋስትና እንድትሰጥ ይሻሉ።

ዘለንስኪ ትናንት እሑድ ከዓለም ሚዲያ ጥያቄዎችን ሲቀበሉ ከወትሮው በተለየ መልኩ ዘና ብለው ታይተዋል።

በቀደሙት ዓመታት በእንዲህ ዓይነት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ጊዜ ስሜታዊ ሆነው ነበር የሚታዩት።

ይህ በእንዲህ እያለ የአሜሪካና የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሳኡዲ አረቢያ ጦርነቱን ለማቆም የመጀመርያ ዙር ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

በዚህ ጉባኤ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ ዩክሬን አልተወከሉም።

ይህ ያሳሰባቸው የአውሮፓ መሪዎች በየፊናቸው ዲፕሎማሲያዊ ሩጫ ጀምረዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዛሬ ሰኞ ዋሽንግተንን ይጎበኛሉ ተብሎ ሲጠበቅ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ደግሞ ሐሙስ ዕለት እዚያ ይገኛሉ።

የሁለቱም መሪዎች ዋና ጉዳይ ዩክሬን ትሆናለች።