
24 የካቲት 2025
በሶማሊያ በሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁኔታን በተመለከተ አሠራር ለመዘርጋት የሁለቱ አገራት የጦር አዛዦች ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
በኢትዮጵያው መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና በሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኃይሎች የመከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ መካከል የተደረሰው ስምምነት በሶማሊያ ያለው የኢትዮጵያ ጦር ስምሪትን፣ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም አጠቃላይ ክንዋኔዎች የሚመለከተውን ‘ስታተስ ኦፍ ፎርስ አግሪመንት’ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው።
አንዲት አገር ጦሯን በሌላ ውጭ አገር በምታሰማራበት ወቅት የጦሩ ስምሪት፣ ተግባራት፣ ኃላፊነት፣ መብቶችን የሚመለከተው በአገራቱ መካከል የሚደረስ አሳሪ (ሕጋዊ ስምምነት) ስታተስ ኦፍ ፎርስ አግሪመንት ይሰኛል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቿን በአገሪቱ ውስጥ ማሰማራቷ ይታወሳል።
ይህ ‘ስታተስ ኦፍ ፎርስ’ ስምምነት በአውሮፓውያኑ 2023 በአገራቱ መካከል የተፈረመው የመከላከያ ትብብር የመግባቢያ ስምምነት ዋና አካል እንደሚሆንም አገራቱ በጋራ ባወጡት እና በመንግሥታዊው የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ሶና የካቲት 16/2017 ዓ.ም. የወጣው መግለጫ ያትታል።
በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሚመራ ልዑክ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ የካቲት 15/2017 ዓ.ም. ባደረገው የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ይህንን ስምምነት ጨምሮ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በሶማሊያ እና በቀጠናው ሰላም፣ ደኅንነት፣ ፀጥታ እና የመረጋጋት ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ሁለቱ የጦር አዛዦች የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ጅማሮ አድንቀው ከዚህ ቀደም በነበረው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት አትሚስ ስኬቶች ማስቀጠል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በኤዩሶም ስምሪት ላይ እንዲካተት የጦር አዛዦቹ በዚህ ወቅት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም 3 ሺህ ያህል ጦር በአትሚስ አሰማርታ የነበረችው ኢትዮጵያ በቀጣዩ ተልዕኮ ምን ያህል ወታደሮችን ታሰማራለች የሚለው አልተጠቀሰም።
በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ውስጥ ላለማካተት አሳልፋው የነበረውን ውሳኔ ልትቀለብስ እና በተልዕኮው ለማካተት እያጤነች እንደሆነ ከዚህ ቀደም ተዘግቦ ነበር።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት እና እራሷን ነጻ አገር ነኝ ብላ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች ጦሯ በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ እንደማይካተት የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው ሶማሊላንድ በተደረሰ የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ካወዘገቧቸው ሌሎች ጉዳዮች መካል የኢትዮጵያ ጦር ወደ ጁባላንድ ገብቷል የሚለው ክስ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት የሶማሊያ ማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ደቡባዊ ጁባላንድ፣ ጌዶ ክልል በሚገኘው ቡሎሃዎ አንቀሳቅሳለች ሲል ወንጅሏል።
በተጨማሪም ጦሯን ብቻ ሳይሆን ሁለት ሕገወጥ መሳሪያ የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ ጁባላንድ መዲና ኪስማዮ አስገብታለች ሲል ወንጅሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራት አገሪቱ የበለጠ እንዳትረጋጋ እና ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ የጌዶ ክልልን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት አካል ነው በማለት ከሶ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ወታደሮች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች ገብቷባታል የተባለችው ጁባላንድ አስተዳደር በበኩሉ የሶማሊያን ክስ “ፍጹም ፕሮፖጋንዳ እና ሐሰተኛ” ሲል አጣጥሏል። “ዓለምን ለማሳሳት ይፈልጋሉ” ሲልም የፌደራሉን መንግሥት ወቅሶ በጭራሽ የተሰማራ የኢትዮጵያ ጦር የለም ብሏል።
ውንጀላውን አስመልክቶ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ በይፋ የሰጠችው አስተያየት የለም።
የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በተጨማሪ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ የሚደረጉ ማንኛውም ግንኙነቶች በሶማሊያ የፌደራላዊ መንግሥት በኩል ብቻ እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱን የጋራ መግለጫቸው አትቷል።
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስምምነት ላይ ለመድረስ የመጀመሪያውን ዙር የቴክኒክ ድርድር አካሄዱ19 የካቲት 2025
- የጸጥታው ምክር ቤት ለአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ፈቃድ ሰጠ28 ታህሳስ 2024
- የሶማሊያ ታጣቂዎች የአሜሪካን የጦር ሄሊኮፕተሮች የጣሉበት ወቅት በነዋሪዎች ሲታወስ11 የካቲት 2025

በተጨማሪም የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ለማክበር የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት መስማማታቸውን የአገራቱ የጋራ መግለጫ ያትታል።
ኢትዮጵያ ከፊል ራስ ገዞቹ ፑንትላንድ፣ ጁባላንድን ጨምሮ በጋልሙዱግ እና በሂርሻበሌ በሚገኙ ግዛቶች ውስጥ ለሚገኙ ታጣቂዎች መሳሪያ እና ሥልጠና እየሰጠች ነው በሚል የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርብ ይሰማል።
ባለሥልጣናቱ ኢትዮጵያ የምታደርገው ግንኙነት በሶማሊያ የፌደራል መንግሥት በኩል ብቻ እንዲሆን የተደረሰው ስምምነት ከዚህ ቀደም የቀረቡ ክሶችን መነሻ ስለማድረጉ የተባለ ነገር የለም።
በአንድ ቀኑ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ ከኢትዮጵያ በኩል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲገኙ፤ ከሶማሊያ በኩል ደግሞ ከመከላከያ ሠራዊት አዛዡ በተጨማሪ የአገሪቱ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ መሐመድ አሉ ተወክለዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሁለተኛ ዙር የቴክኒክ ድርድራቸውን በሶማሊያዋ መዲና፣ ሞቃዲሾ ለማድረግ መስማማታቸውን ይኸው የጋራ መግለጫ አመልክቷል።
የመጀመሪያ ዙር የቴክኒክ ድርድር ባለፈው ሳምንት በቱርክ መዲና አንካራ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
በቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም. የተደረሰው የአንካራ ስምምነት ለአንድ ዓመት ያህል በቃላት ጦርነት ሲወዛገቡ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በድርድር ጠረጴዛ ለመፍታት እንዲቀመጡ ያደረገ ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚያረጋግጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ የምታገኝበትን ስምምነት መድረስ የሚያስችል የቴክኒካል ድርድሮች እንደሚጀምሩ ተነጋግረው ነበር።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት የቆየውን አለመግባባት በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሠረት፤ “ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።”
ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ” ሲል ያትታል።