
24 የካቲት 2025
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች ወረዳ እና በጎረቤት አገር ኬንያ ቱርካና ካውንቲ ማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት እና ጥቃት በኢትዮጵያ በኩል 13 ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳደር ሲያስታውቅ፤ በኬንያ በኩል ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተዘገበ።
በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት “10 ሺህ” ሰዎች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን የወረዳው አስተዳደር ገልጿል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከሚዋሰኑባቸው አከባቢዎች አንዱ የሆነው የደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ፤ ከኬንያው የቱርካና ካውንቲ ጋር የሚጎራበት አካባቢ ነው።
በሁለቱም አካባቢዎች አርብቶ አደር ማኅበረሰቦችን የያዙ ሲሆን በሁለቱም አገራት ድንበር ውስጥ የሚገኘው የቱርካና ሐይቅ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ያስተሳስራል።
በሁለቱ አገራት ድንበሮች ውስጥ በሚገኙ ማኅበረሰቦች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከግጦሽ መሬት እና ቱርካና ሐይቅ ጋር የተያያዙ ግጭቶች እንደሚያጋጥሙ የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሐሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊትም በአካባቢው ግጭት ተፈጥሮ እንደ ነበር የሚያስታውሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ የወረዳው ኃላፊዎች ችግሩን ለመፍታት የኬንያ ከአጎራባች ኃላፊዎች ጋር ንግግር አድርገው እንደነበር አስረድተዋል።
ይኹን እንጂ በተከታዩ ቀናቶች የተፈጠሩ ክስተቶች በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል ከፍ ያለ ግጭት እንዲፈጠር እና የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ታደለ እንደሚያስረዱት የአሁኑ ግጭት የተጀመረው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 13/2017 ዓ.ም. በሐይቁ ላይ አሳ እያጠመዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ሰው መቁሰሉን ተከትሎ ነው።
- በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ሁኔታን በተመለከተ አሠራር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ተደረሰ24 የካቲት 2025
- ከ10 ዓመት በኋላ ከሐማስ እስር ነጻ የወጣው ቤተ-እስራኤላዊ አቬራ መንግሥቱ ማን ነው?23 የካቲት 2025
- ዘለንስኪ ‘ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ’ አሉ24 የካቲት 2025
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ለሁለቱ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጥቃት የተፈጸመው በኬንያውያን አሳ አጥማጆች እንደሆነም ተናግረዋል። በዚሁ ዕለት እንስሳትን በመጠበቅ ላይ የነበረ ሌላ ሰውም መገደሉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል።
እነዚህን ግድያዎች ተከትሎም ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የካቲት15፤ አሳ በማጥመድ ላይ በነበሩ ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን በሐይቁ ላይ እንዳሉ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።
አቶ ታደለ፤ “ከትናንትና ወዲያ ከፍተኛ ውጊያ ነበር። ውጊያው፤የእኛ ስምንት ሰው በሐይቅ ላይ የሞተበት እና የእነሱም ደግሞ ሙሉ በሙሉ ቁጥሩ ባይታወቅም ብዙ ሰው የሞተበት ነው” ሲሉ የስምንት ሰዎች ሕይወት ስላለፈበት እና ሁለት ሰዎች ስለቆሰሉበት ክስተት አስረድተዋል።
በሐይቁ ላይ የተካሄደውን ይህንን ግጭት ተከትሎ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ አሳ በማጥመድ ላይ የነበሩ 32 ኬንያውያን እና አምስት ጀልባዎች መያዛቸውን ተናግረዋል። በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ኬንያውያን ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መደረጉን እና ጀልባዎቹ ግን አሁንም እንደተያዙ መሆኑን አክለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው እንደሚናገሩት ይህ ግጭት በትናንትናው ዕለትም ቀጥሎ ውሏል።
“ትናንት የተፈጠረው የቅዳሜ ዕለቱ ጦርነት አጸፋ ነው። በኬንያ በኩል ‘የእኛን ሰዎች ጨርሰዋል፤ ገድለዋል’ ብለው አጸፋ የመመለስ አይነት ሁኔታ ነው” ሲሉ ስለ ትናንቱ ጥቃት ገልጸዋል።
ከኬንያ በኩል የመጡ ነዋሪዎች ሦስት ቀበሌዎችን በያዘ “ስየስ” ወደተባለ መንደር በመግባት “ሰዎችን ሙሉ በሙሉ የማስለቀቅ እና መንደሩን የማውደም ሙከራ” ማድረጋቸውን አቶ ታደለ አስረድተዋል።
“ይሄኛው መንደሩን ለመከላከል፣ ያ ደግሞ መንደሩን ለማጥፋት በሁለቱም በኩል ምልልሶች ነበሩ” ብለዋል።
በትናንቱ ግጭት የተጎዳ ሰው እንዳልነበረ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይሁንና ግጭት “ረግቦ ሰዎች ከተመለሱ በኋላ ከኬንያ በኩል የመጡ ሰዎች ምሽት ላይ ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን” ገልጸዋል።

ይህንን ጥቃት ተከትሎም አስር ሺህ የመንደሩ ነዋሪዎች ከአካባቢው ሸሽተው “ልበ ሙቀት” በተባለ አካባቢ መስፈራቸውን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በተከታታይ ቀናት በነበሩት ግጭቶች ከኢትዮጵያ በኩል13 ሰዎች መገደላቸውን የሚናገሩት አቶ ታደለ፤ በተጨማሪም ስድስት የአሳ ማስገሪያ ጀልባዎች፣ ከ120 በላይ የአሳ ማጥመጃ መረቦችን ጨምሮ ተለያዩ ንብረቶች መዘረፋቸውን ተናግረዋል።
አጎራባች የሆነው የኬንያው ቱርካና ካውንቲ ትናንት እሁድ የካቲት 16/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ቁጥራቸው ያልታወቁ ኬንያውን አሳ አጥማጆች መገደላቸውን አስታውቋል።
መግለጫው፤ አሳ አጥማጆቹ ቅዳሜ ዕለት ጥቃት የተፈጸመባቸው “በዳሰነች ታጣቂዎች” መሆኑን ጠቅሷል።
የኬንያ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው የተገደሉት ኬንያውያን ቁጥር ከ20 በላይ እንደሆነ ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል።
የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ግን በአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የተጠቀሰውን የኬንያውያን ሟቾች ቁጥር አይቀበሉትም።
“ቁጥሩ ትንሽ የተጋነነ ነው። ምናልባት ቁጥሩ ከዚያ ሊበልጥም፣ ሊያንስም ይችላል” የሚሉት አቶ ታደለ፤ ግጭቱ የተካሄደው በሐይቁ ላይ በመሆኑ በትክክለኛው ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ለማወቅ እንደሚያስቸግር አንስተዋል።
ላለፉት ተከታታይ ቀናት በድንበር አካበቢዎቹ የተፈጠሩት ግጭቶች አሁንም ቢሆን መፍትሄ እንዳልተበጀላቸው ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
አሁንም ድረስ ከኬንያ ድንበር በኩል “የታጠቁ ሰዎች ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ” የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።
የወረዳው አስተዳደር በአካባቢውን ያለውን ችግር ለደቡብ ኦሞ ዞን እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማሳወቁንም አቶ ታደለ አክለዋል።