
24 የካቲት 2025
የሱዳን ጦር አርኤስኤፍ እየተባለ የሚጠራውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከበባን በመስበር ኤል ኦቤይድ የተሰኘችውን ቁልፍ ከተማ መያዙን አስታወቀ።
በደቡባዊ ሱዳን የምትገኘውን የዚህችን ከተማ ከበባ ጦር መስበሩ ከመሰማቱ ሰዓታት ቀደም ብሎ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቁጥጥሩ ሥር የሚኙ አከባቢዎችን ይዞ መንግሥት ለመመስርት በኬንያ መዲና ናይሮቢ ላይ ቻርተር ፈርሟል።
ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የሱዳን ጦር ማዕከላዊ ስልጣንን ለመቆጣጠር እያደረጉት ባለው ጦርነት በሺዎች የተገደሉ ሲሆን ሚሊዮኖች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ይህ ጦርነት አገሪቱን ለሁለት የከፈለ ነው። የሱዳንን ሰሜናዊ እና ምሥራቃዊ ክፍል ጦሩ የተቆጣጠረ ሲሆን አብዛኛውን የዳርፉር ግዛት እና የደቡብ የሱዳን ክፍል በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ ሥር ይገኛል።
ዛሬ የሱዳን ጦር ከበባዋን የሰበረው ኤል ኦቤይድ ከተማ የሰሜናዊ ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ ስትሆን የሱዳንን መዲና ካርቱም ከዳርፉር ግዛት ጋር የምታገናኝ ቁልፍ ከተማ ናት።
ጦሩ በተከታታይ በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ሥር ያሉ በርካታ አካባቢዎችን ዳግም እየተቆጣጠረ እንደሆነ ይሰማል።
በከተማ ጎደናዎች የሱዳን ጦር ወታደሮች በደስታ ተውጥው ሲጓዙ ታይተዋል።
ጦሩ ከበባውን መስበሩን ያረጋገጡት የጦሩ ቃል አቀባይ ነቢል አብደላ የሱዳን ጦር የአርኤስኤፍን አሃዶች አውድሟል ሲሉ ተናግረዋል።
የሱዳን ገንዘብ ሚኒሰትር ጅብሪል ኢብራሂም ‘ድሉ’ ሌላኛዋን በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቁጥጥር ሥር ያለቸውን የዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል ፋሻርን ከበባ ለመስብር “ትልቅ እርምጃ” ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ለኮርዶፋን ግዛት ሰብዓዊ እርደታ ለማቅርብ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
- በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ሁኔታን በተመለከተ አሠራር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ተደረሰ24 የካቲት 2025
- ከ10 ዓመት በኋላ ከሐማስ እስር ነጻ የወጣው ቤተ-እስራኤላዊ አቬራ መንግሥቱ ማን ነው?23 የካቲት 2025
- ዘለንስኪ ‘ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ’ አሉ24 የካቲት 2025
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የሱዳን ሲቪል ማኅበረሰብ ተሟጋች የሆነችው ደሊል አቡዱልሞኒም የሱዳን ጦር ከተማዋን መልሶ መቆጣጠሩ ትልቅ እና ጠቃሚ ነው ብላለች።
ጨምራም ፈጥኖ ደራሸ ኃይሉ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲቪል ሰዎቸን “በምርኮ” ይዞ ነበር ስትል ገልጻለች።
በከተማዋ ያለው ሁኔታ “አሰቃቂ” ነው የምትለው ደሊል የምግብም ሆነ የሕክምና እርዳታ እንደሌለ አንስታለች።
ሁኔታውን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ አካባቢው ለርሃብ እና ለምግብ አጥረት ተጋላጭ መሆኑ ነው ብላለች።
ከበባው በጦሩ መሰበሩ እርዳታ እንዲገባ ያግዛል ብዬ አምናለሁ ስትልም ጨምራለች።
በከተማዋ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው የ53 ዓመቱ አህመድ ሁሴን “የከበባው መነሳት ከተማዋ ላይ ዳግም ሕይወት ይዘራባታል” ሲል ለኤኤፍፒ ተናግሯል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ነቢል የሱዳን ጦር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ማዕከሉ ወዳደረገው ምዕራባዊ ሱዳን ለመገስገስ “ጠጠር ያለ ተግባር” ሲያከናውን ነበር ብለዋል።
በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ሲቪል ሰዎች ላይ እልቂት ፈጽመዋል ሲሉ አንዳቸው ሌላኛቸውን ይከሳሉ።
አርኤሴፍ በዳርፉር የዘር ፍጅት ፈጽሟል የሚል ክስም ይቀርብበታል።
ሁለቱም ግን የሚቀርብባቸውን ክስ ያስተባብላሉ።
ኬንያ ባለፈው ሳምንት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በማስተናገድ ትይዩ መንግሥት (parallel government) ለመመስረት ሞክራለች በሚል በሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ተወቅሳለች።
ትናንት እሁድ የሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒሰትር አሊ የሱፍ አገራቸው “ትይዩ ተብሎ ለሚጠራ መንግሥት” ዕውቅና የሚሰጥ አገርን እንደማትቀበል ገልጸዋል።
ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ኬንያ ላይ የተቃውሞ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቆ ነበር።
ይህ ከተሰማ በኋላ የሱዳን መንግሥት በናይሮቢ የሚገኘውን አምባሳደሩን ጠርቷል።
የኬንያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ በግጭቱ እየተሳተፉ ላሉ ኃይሎች “ገለልተኛ የሆነ” መድረክ ከማቅረብ የዘለለ “የተደበቀ ዓላማ” እንደሌለው በውጪ ጉዳይ ሚኒስትቴር በኩል አሳውቋል።