
ከ 9 ሰአት በፊት
ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግሥታት ዩክሬንን በተመለከተ የቀረቡ ሁለት የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ለሩሲያ የሚወግን አቋም አንፀባረቀች።
የዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ ዓመትን በተመለከተ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የትራምፕ አስተዳደር በጦርነቱ ጉዳይ ያለውን የአቋም መለወጥ ያሳየ ሆኗል።
የመጀመሪያ የውሳኔ ሐሳብ በአውሮፓ ሀገራት የቀረበ ሲሆን የሞስኮውን ድርጊት የሚኮንን እና የዩክሬን የግዛት አንድነት እንዲከበር የሚጠይቅ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ እና ሩሲያ ይህን የውሳኔ ሐሳብ በመቃወም እጃቸውን አውጥተዋል።
በኒው ዮርክ የከተመው የተባበሩት መንግሥት ጠቅላላ ጉባዔ ይህን ምክረ ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።
በሌላ በኩል ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ሁለተኛው የውሳኔ ሐሳብ በአሜሪካ የረቀቀ ሲሆን በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቅ ቢሆንም ሩሲያን የሚያወግዝ አንቀፅ አላካተተም።
የፀጥታው ምክር ቤት ይህን የውሳኔ ሐሳብ ቢያሳልፈውም የአሜሪካ አጋር ሀገራት የሆኑት ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሁለቱ ሀገራት በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የቃላት ማሻሻያ እንዲደረግ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን ለኦፊሴላዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንተው ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተገናኝተዋል።
ትራምፕን በዋይት ሐውስ ያገኟቸው ማኽሮን በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የሁለቱ ሀገራት አቋም መራራቁን ለማጥበብ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ሁኔታን በተመለከተ አሠራር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ተደረሰ24 የካቲት 2025
- ራስን ማጥፋት ወንጀል ወይስ የጤና እክል? የኢትዮጵያ ሕግ ራስን ስለማጥፋት ምን ይላል?25 የካቲት 2025
- ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ሀብቷን ለመስጠት የምትደራደረው ለምንድን ነው?25 የካቲት 2025
በሚቀጥለው ሐሙስ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ወደ አሜሪካ አቅንተው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚወያዩ ተነግሯል።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከአውሮፓውያን ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት የሻከረው የትራምፕ አስተዳደር አቋሙ ከሩሲያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ ተገኝቷል።
አሜሪካ 193 አባል ሀገራት ላሉት የተባበሩት መንግሥት ጠቅላላ ጉባዔ ባቀረበችው የውሳኔ ሐሳብ “የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት” በአፋጣኝ እንዲቋጭ ጠይቃለች።
የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ደግሞ ዘርዘር ያለ እና ሩሲያ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ዩክሬን ላይ አውጃለች የሚል እንዲሁም የዩክሬን የግዛት አንድነት እንዲከበር የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል።
የጠቅላላው ጉባዔ አባላት በአውሮፓ ሀገራት የቀረበውን ሐሳብ በ93 ድምፅ ያሳለፉት ሲሆን ብዙዎችን ባስደነቀ ሁኔታ ዩናይትድ ስቴትስ ይህ ሐሳብ ተቃውማለች። ሌሎች የውሳኔ ሐሳቡን የተቃወሙት ሩሲያ፣ እስራኤል፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሱዳን፣ ቤላሩስ፣ ሀንጋሪ እና ሌሎች 11 ሀገራት ናቸው። 65 ሀገራት ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሁለተኛውና በዩናይትድ ስቴትስ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ደግሞ የቃላት ማሻሻያ እንዲደረግበት ተደርጎ ቢያልፍም አሜሪካ ድምፅ ከመስጠት ተቆጥባለች።
የበለጠ ጠንካራ በሚባለው እና 15 አባል ሀገራት ባሉት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የአሜሪካ የውሳኔ ሐሳብ በ10 ድምፅ ሲያልፍ ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ዴንማርክ ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው ሀገራት መካከል ዩናይትድ ስቴትስ እና ሩሲያ ይጠቀሳሉ።