
ከ 8 ሰአት በፊት
ዩክሬን እና አሜሪካ በማዕድን ዙሪያ እየተደራደሩ መሆናቸውን እና ስምምነት ለመፈራረም መቃረባቸውን የአገሪቱ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ይህ ስምምነት አሜሪካ የዩክሬን የማዕድን ክምችትን ለመጠቀም ያስችላታል ተብሏል።
የአውሮፓ እና የዩሮ-አትላንቲክ ጥምረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦልጋ ስቴፋኒሺና በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ድርድሩ በጣም ገንቢ ሲሆን፣ ሁሉም ቁልፍ ጉዳዮች ከሞላ ጎደል መስመር ይዘዋል” ብለዋል።
አክለውም “ይህንን ፊርማ ለፍጻሜ ለማድረስ እና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኞች ነን” ብለዋል።
ዜሌንስኪ ባለፈው መስከረም ወር ላይ ለዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት እና “የድል ዕቅድ” ሲሉ በጠሩት ሰነድ ላይ ማዕድን አውጥቶ የመጠቀንን ጉዳይ አካትተው ነበር።
ሃሳቡ አሜሪካ ዩክሬንን መደገፏን እንድትቀጥል በወቅቱ ለፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ለነበሩት ዶናልድ ትራምፕ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ነበር።
ሰኞ ዕለት የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኪዬቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ እንዲህ ዓይነቱ ስምምነት “ታላቅ ሽልማት” ነው።
ምክንያቱም “በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ነፃ፣ ሉዓላዊ እና ደኅንነቷ የተጠበቀ ዩክሬን” እንድትኖር ያስችላል ነበር ያሉት።
- ዘለንስኪ ‘ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ’ አሉ24 የካቲት 2025
- አሜሪካ ፊቷን ያዞረችባት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች የመቀጠል አቅም አላት?19 የካቲት 2025
- ዘለንስኪ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምላሽ ወሳኝ ማዕድን እንዲሰጡ አሜሪካ ጠየቀች21 የካቲት 2025
ዩክሬን ምን ዓይነት ማዕድኖች አሏት?
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
እንደሚገምተው ከዓለማችን “ወሳኝ ጥሬ ማዕድናት” ውስጥ 5 በመቶ ያህሉ በዩክሬን ይገኛሉ።
ይህ 19 ሚሊዮን ቶን የተረጋገጠ የግራፋይት ክምችትን ያጠቃልላል።
የዩክሬን የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ግዛት ኤጀንሲ እንዳለው ከሆነ አገሪቱ በግራፋይት ክምችት “ከአምስት ዋና ዋና መሪ አገሮች መካከል አንዷ ነች።”
ግራፋይት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎችን ለመሥራት ያገለግላል።
በተጨማሪም ዩክሬን ለባትሪዎች ቁልፍ ግብዓት የሆነው ሊቲየም፣ ከጠቅላላው የአውሮፓ ክምችት መካከል አንድ ሦስተኛው ይገኝባታል።
ከሩሲያ ወረራ በፊት ደግሞ ከአውሮፕላን ጀምሮ እስከ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ የሚውል ቀላል ክብደት ለማምረት የሚያገለግለው ቲታኒየም የምርት ድርሻዋ የዓለም 7 በመቶ ነበር።
በተጨማሪም ዩክሬን እጅግ በጣም ብዙ ብርቅዬ የማዕድናት ክምችት አላት።
እነዚህም የጦር መሳሪያዎች፣ የንፋስ ኃይል ተርባይኖች፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ሌሎች በዘመናዊው ዓለም አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን ለማምረት የሚያገለግሉ የ17 ንጥረ ነገሮች ስብስብ ናቸው።
አንዳንድ የማዕድን ክምችቶች ግን በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ግዛቶች ውስጥ ነው የሚገኙት።
የዩክሬን የኢኮኖሚ ሚኒስትር ዩሊያ ስቪሪደንኮ እንዳሉት 350 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት በሩሲያ በተያዙ ግዛቶች ይገኛል።
በካናዳ የሚገኘው የጂኦፖለቲካል ስጋት አማካሪ ድርጅት በ2022 ባደረገው ግምገማ ሩሲያ 63 በመቶ የዩክሬን የድንጋይ ከሰል ማዕድንን እና ግማሽ የማንጋኒዝ ማዕድንን፣ ካሲየም፣ ታንታለም እና ብርቅዬ ማዕድናትን የያዙ ግዛቶችን በቁጥጥሯ ስር አድርጋለች ብሏል።
ዶ/ር ሮበርት ሙጋህ እንዲህ ያሉት ማዕድናት በሩሲያ ቀጣይ ጥቃት ላይ “ስልታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ” ይጨምራሉ ብለዋል።
ሞስኮ እነዚህም ማዕድናት በመያዝ የዩክሬን ገቢን ማነቆ ውስጥ ከትታለች በሚለው አትስማም።
ሌሎች ግን ይህ የሩሲያን ሀብት ያሰፋዋል፤ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል ይላሉ።
አሜሪካ ማዕድናቱን ለምን ፈለገቻቸው?
ወሳኝ ማዕድናት “የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚ መሠረት ናቸው” ሲሉ ዶ/ር ሙጋህ ያብራራሉ።
ለታዳሽ ኃይል፣ ለወታደራዊ መሳሪያዎች እና ለኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ቁልፍ ናቸው።
“በጂኦፖለቲካ እና በጂኦ ኢኮኖሚክስ ላይ ከፍ ያለ ሚና ይጫወታሉ” ሲሉ ያክላሉ።
በተጨማሪም አሜሪካ የዩክሬን የማዕድን ሀብትን በተመለከተ ስምምነት ለማድረግ የምትፈልግበት አንዱ ምክንያት በዓለም ላይ 75 በመቶ ብርቅዬ የማዕድን ክምችቶችን የምትቆጣጠረው ቻይና ላይ ያላትን ጥገኝነትን ለመቀነስ እንደሆነ የጂኦሎጂካል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ይገልጻል።
በታኅሣሥ ወር ቻይና አንዳንድ ብርቅዬ ማዕድናትን ወደ አሜሪካ መላክን አግዳለች።
ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጉብኝት አስቀድሞ የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ “ስምምነቱ የተጠቃሚነት ድርሻን ከፍ የማድረግ እና አሜሪካን እና ዩክሬንን ለወደፊቱ ማስተሳሰር አካል ነው” ብለዋል።

ስለ ድርድሩ እስካሁን ምን እናውቃለን?
ስቴፋኒሺና ስምምነቱ መቃረቡን ከመናገራቸው በፊት ብዙ የሚያነጋግሩ ነጥቦች ነበሩ።
ባለፈው ረቡዕ ዜሌንስኪ አሜሪካን ያቀረበችውን የዩክሬንን ብርቅዬ ማዕድናት 50 በመቶ ድርሻ ጥያቄ ውድቅ አድርገው ነበር።
አሜሪካ ለዚህ ጥያቄዋ ያቀረበችው መከራከሪያ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለምታደርገው ጦርነት የሰጠችውን የእርዳታ መጠን ነው።
“ግዛታችንን መሸጥ አልችልም” ነበር ያሉት ዜሌኒስኪ።
በእሁዱ የስምምነቱ ሁለተኛ ረቂቅ ድንጋጌዎች ከመጀመሪያው ሰነድ የበለጠ ጠጠር ብለው ታይተዋል።
ዜሌንስኪ እሁድ ዕለት በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት ከእኩል (50/50) የገቢ ክፍፍል ይልቅ፣ የተሻሻለው ረቂቅ ዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ ቁጥጥርን ትፈልጋለች።
ዜሌንዝኪ በበኩላቸው ማንኛውንም ስምምነት የደኅንነት ዋስትናዎችን እንዲያካትት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አሜሪካ የዩክሬን ማዕድን የማግኘት ስምምነትን “ታላቅ ሽልማት” ሲሉ አንቆለጳጵሰውታል።
ስምምነቱ “ዘረፋ” ነው የሚለውን ሃሳብ ውድቅ በማድረግ “ዩክሬናውያን ከዚህ የሚያገኙት ነገር በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ነፃ፣ ሉዓላዊ እና ደኅንነቷ የተጠበቀ ዩክሬን መፍጠር ነው” ብለዋል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የአሜሪካን ፍላጎት “ቅኝ ግዛት” ሲሉ ገልጸውታል።
ይኹን አንጂ ኪዬቭ ሀብቷን በጋራ አውጥቶ የመጠቀም ፍላጎት አላት።
በዩክሬን የሚገኘው የማዕድን አማካሪ ድርጅት የጂኦሎጂካል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢሪና ሱፕሩን እነዚህን የማዕድን ሀብቶች ማልማት እጅግ አስቸጋሪ እና ውድ ነው ይላሉ።
የአሜሪካ ባለሀብቶችን በመሳብ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ማልማት ከቻሉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አክለው ገልጸዋል።
ሱፕሩን “የእኛ የማዕድን ኢንዱስትሪ እጅጉን የጎደላቸውን ቴክኖሎጂዎችን እናገኛለን” ሲሉ ይናገራሉ።
“ካፒታል እናገኛለን፤ ይህ ማለት ተጨማሪ ሥራዎች፣ የታክስ ክፍያዎች ማለት ነው። ከማዕድን ክምችታችን ልማትም ገቢ እናገኛለን።”