የአውሮፕላን መጓጓዣ

25 የካቲት 2025, 07:20 EAT

በተከታታይ ካጋጠሙ ከፍተኛ አደጋ በኋላ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የአየር መጓጓዣ አደጋዎች እየበዙ መምጣታቸውን ይናገራሉ።

ከመከስከስ ለጥቂት የተረፉ አውሮፕላኖችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ በስፋት በተሰራጩበት በዚህ ወቅት፣ የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሼን ዳፊ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ከሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቅርቡ በአሜሪካ እየተከሰቱ ያሉት የአውሮፕላን አደጋዎች “በጣም ልዩ” መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዳፊ አስተያየት በጥር ወር በዋሽንግተን ዲሲ በንግድ አየር መንገድ አውሮፕላን እና በወታደራዊ ሄሊኮፕተር መካከል በተፈጠረ የአየር ላይ ግጭት 67 ሰዎች የሞቱበትን ጨምሮ ከበርካታ ከባድ ክስተቶች በኋላ የተሰጠ ነው።

በቶሮንቶ ካናዳ በመጥፎ የአየር ጠባይ የተነሳ አንድ አውሮፕላን በመንደርደርያ አስፋልቱ ላይ ሲገለበጥ የሚያሳይ ምሥልም በበይነ መረብ ላይ በስፋት ተሰራጭቷል፤ ይህም የአደጋ ስጋቱን ከፍ አድርጎታል።

በጉዳዩ ላይ የተደረገው ጥናት ውስን ቢሆንም፣ አንድ የቅርብ ጊዜ የአሶሼትድ ፕሬስ ዳሰሳ እንደሚያመለክተው እነዚህ አስገራሚ የአደጋ ምሥሎች አንዳንድ አሜሪካውያን ለመብረር ያላቸው እምነት ላይ የተወሰነ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ነገር ግን ቢቢሲ ቬሪፋይ [የመረጃ ማጣሪያ] በአሜሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን መረጃ መሠረት አድርጎ ባደረገው ትንተና ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአውሮፕላን አደጋዎች አጠቃላይ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይተዋል።

የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት አደጋዎች እስከ ጥር ወር መጨረሻ ድረስ ያሉት አሃዞች የተደራጁት በአገሪቱ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ነው።

በዚህ በብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ መረጃ መሠረት በአሜሪካ ከ2005 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ የበረራዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም በአሜሪካ የአየር አደጋ አጠቃላይ መቀነስ አሳይቷል። የጥር 2025 አሃዝ ካለፈው ዓመት ጥር (58) እና ጥር 2023 (70) ያነሰ እንደነበር ያሳያል።

የዓለም አቀፍ የአየር ላይ ክስተቶችን የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መረጃ በበኩሉ፣ ከአንድ ሚሊዮን አውሮፕላን በረራዎች ውስጥ የዓለም አቀፍ አደጋዎች ቁጥር ሲታይ በ2005 እና 2023 መካከል ግልፅ የሆነ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል።

ባለፈው ሳምንት ካናዳ ውስጥ በአሜሪካው አየር መንገድ ዴልታ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ
የምስሉ መግለጫ,ባለፈው ሳምንት ካናዳ ውስጥ በአሜሪካው አየር መንገድ ዴልታ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የድርጅቱ የአውሮፕላን አደጋ ትርጓሜ በጣም ሰፊ ሲሆን፣ ተሳፋሪዎች ወይም የበረራ ሠራተኞች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ወይም የሞቱባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ አውሮፕላንን ለጉዳት እና ለጥገና የዳረጉ እንዲሁም የጠፉባቸውን ክስተቶች ያጠቃልላል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር አደጋዎች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ምንም እንኳን በአንዳንድ ዓመታት ከፍተኛ የአየር አደጋዎች የሚታዩ ቢሆንም እየቀነሰ መጥቷል።

በአውሮፓውያኑ 2014፣ ሁለት እንደዚህ ያሉ ክስተቶች ጉልህ የሆነ ጭማሪ አበርክተዋል።

በመጋቢት ወር የማሌዢያ አየር መንገድ አውሮፕላን 239 ሰዎችን አሳፍሮ ከኩዋላ ላምፑር ወደ ቤይጂንግ ሲጓዝ ጠፍቷል።

በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ሌላ የማሌዢያ አየር መንገድ ኤም ኤች 17 አውሮፕላን ሩሲያ ሰራሽ በሆነ ሚሳኤል ተመትቶ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል።

በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የስታቲስቲክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰር ዴቪድ ስፒገልሃልተር ለቢቢሲ ቬሪፋይ እንደተናገሩት እንደዚህ ያሉ የመረጃ ስብስቦች ድንገተኛ እና ትልቅ መዋዠቅን ያሳያሉ።

“ከአደጋዎች ይልቅ በሰው ሕይወት ላይ ደረሰውን ጉዳት ብንቆጥር እጅግ በጣም ተለዋዋጭ እና ለአንድ ትልቅ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው አይቀርም” ብለዋል።

“ድንገተኛ ክስተቶች በተደጋጋሚ አይከሰቱም – የተበታተኑ ናቸው። ስለዚህ በሚያሳዝን ሁኔታ የአውሮፕላን አደጋዎች ባይሆኑም እንኳ ግንኙነት ያላቸው እንደሚመስሉ መጠበቅ እንችላለን።”

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የተከሰቱትን ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን አደጋዎች በተመለከተ የቀድሞ የፊንላንድ የአየር አደጋ ዋና ዳይሬክተር ኢስሞ አልተን፣ የአውሮፕላን ደኅንነት ማሽቆልቆሉን አመላካች አይደሉም ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“በዚህ ወቅት ለተለያዩ ዓይነት አደጋዎች መዳረጋችን ዕድለ ቢስነት ነው። ነገር ግን ሰዎች በዚህ ላይ ተመሥርተው ምንም ዓይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ የለባቸውም፤ ምክንያቱም ክስተቶቹ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው” ብለዋል።

በታኅሣሥ ወር ካዛኪስታን ላይ የተከሰከሰውን የአዘርባጃን አየር መንገድ አውሮፕላን በሩሲያ ፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤል መመታቱን በመጥቀስ ባለፉት ጥቂት ወራት የተከሰቱ አንዳንድ ክስተቶች ሊገመቱ የማይችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በባኪንግሃምሻየር ኒው ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የቀድሞ ፓይለት ማርኮ ቻን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአየር ትራንስፖርት አደጋዎች ግንዛቤ መጨመር የበለጠ እየተስፋፋ ነው፤ ምክንያቱም “አደጋዎች ለማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች መጋለጣቸው እየጨመሩ ነው።”

በቲክቶክ ላይ የሚሠራጨው አንድ ቪዲዮ፣ ከሱፐርማን ፊልም የተቀዳ ጀግና አንድ ጄት ስታዲየም ውስጥ እንዳይከሰከስ ሲከላከል ያሳያል። ከክሊፑ ጋር ያለው መግለጫ “አሁን ባለው ሁኔታ፤ ፒት ቡታጃጅ በየዕለቱ ባለፉት አራት ዓመታት” ይላል። ክሊፑ እንደሚያመለክተው የቀድሞ የአሜሪካ የትራንስፖርት ኃላፊ በጥር ከቢሮ ከለቀቁ በኋላ የአቪዬሽን አደጋዎች እያደጉ መጥተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ የተከሰቱት ተከታታይ አደጋዎች በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በጥር ወር 2024 በበረራ ላይ ሳለ በሩ ከተከፈተ በኋላ ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል።

በዚህ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ስጋት ውስጥ የገቡት ደንበኞች በቦይንግ የተመረቱት አውሮፕላኖችን መቃወም የጀመሩ ሲሆን፣ የኩባንያው የአክሲዮን ዋጋም ወድቋል።

እንደ እነዚህ ያሉ የከባድ አደጋዎች ክስተቶች በባለሥልጣናት በጥልቀት እንደሚመረመሩ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዳዲስ ዝርዝሮች እና የአደጋ መረጃዎች ወደ ፓይለት ማሠልጠኛ አውሮፕላኖች ይገባሉ ስለዚህ ፓይለቶች ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዲዘጋጁ ይረዳቸዋል።

“ዛሬ የማሠልጠኛ አውሮፕላኖችን ብናይ ምን ያህል የላቁ መሆናቸውን እንረዳለን፤ እንደ እውነተኛ አውሮፕላኖች ናቸው” የሚሉት ኢስሞ አልቶን “ከ40 ዓመታት በፊት በረራ ከጀመርኩበት ጊዜ ፈጽሞ የተለየ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ተቆጣጣሪዎች ለደኅንነት ጥሰቶች የፍቃድ እገዳዎችን እና የአሠራር ገደቦችን የሚያካትቱ ቅጣቶችን ሊወስኑ ይችላሉ። የደኅንነት መስፈርቶችን ካላከበሩ አየር መንገዶች ከአገሮች እና ከቡድኖች ሊታገዱ ይችላሉ።

በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት ክስተቶች ቢኖሩም፣ የአየር ትራንስፖርት በጣም አስተማማኝ የጉዞ መንገድ ሆኖ ቆይቷል።

በአውሮፓውያኑ 2022 በአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የቅርብ ጊዜ አሃዞች መሠረት፣ ከትራንስፖርት ጋር ከተዛመዱ ሞቶች መካከል ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት በመንገድ ላይ የተከሰቱ ናቸው። ከአየር ጉዞ ጋር የተያያዙት ከ1 በመቶ ያነሱ ነበሩ።

እና በእያንዳንዱ ርቀት የተጓዙት ሰዎችን እና የሟቾች ቁጥርን ከተመለከትን የአየር መጓጓዣ ደኅንነት የበለጠ ግልፅ ነው።

በአሜሪካ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት በ2022፣ በ100 ሚሊዮን ማይል የአየር መንገደኞች ውስጥ 0.001 የመንገደኞች ሞት ብቻ ነበር የተመዘገበው።

ይህም በተሽከርካሪዎች ተሳፋሪ ካየነው 0.54 ነው።

ስለዚህም ሚስተር አልተን “ወደ አየር ማረፊያው እንዴት እንደሚጓዙ ይጠንቀቁ” ብለዋል። “ከትክክለኛው በረራ ጋር ሲወዳደር ይህ የጉዞው በጣም አደገኛው ክፍል ነው።”