
ከ 1 ሰአት በፊት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ አገራቸው በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ያሉትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ብርቅዬ ማዕድናትን ለአሜሪካ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።
ፑቲን ይህንን የገለጹት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን ከዋሽንግተን ድጋፍ ለማግኘት ከማዕድን ሀብቷ የተወሰነውን ለአሜሪካ እንድትሰጥ ተደጋጋሚ ግፊት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነው።
የዩክሬን ማዕድንን ለአሜሪካ ለመስጠት የሚደረገው ድርድር በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንድ የአገሪቱ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት ከሩሲያ መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ ከአሜሪካ አጋሮች ጋር የጋራ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሥራት የማዕደን ሀብቶችን ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፑቲን ለአጋርነት የሚያቀርቡት የሩሲያ “አዲስ ግዛቶች” ሲሉ በጠቀሷቸው እና ሩሲያ ከሦስት ዓመት በፊት ወረራ ስትፈፅም በተቆጣጠረቻቸው በምሥራቃዊ ዩክሬን ክፍል የሚገኙ ማዕድናትን መሆኑን አንስተዋል።
ይህ ዕቅድ ሁለቱ አገራት በትብብር አልሙኒየም አውጥቶ ለአሜሪካ በማቅረብ የማዕድኑን ገበያ ለማረጋጋት እንደሚያስችልም አክለዋል።
ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ትራምፕ የዩክሬንን የማዕድን ክምችት ለማግኘት የሚያደርጉትን ግፊት ያልተቃወሙት ፑቲን፤ በማዕድናት ማውጣት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ጨምሮ “ከውጭ አጋራት” ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ፑቲን፤ ብርቅዬ ማዕድናትን በተመለከተ አሜሪካ ከዩክሬን ጋር ልታደርግ የምትችለው ስምምነት ስጋት የሚፈጥር እንዳልሆነ ገልጸው፤ ሩሲያ “ያለ ጥርጥር ከዩክሬን በብዙ የሚበልጥ ተመሳሳይ የማዕድናት ሀብቶች አላት” ብለዋል።
“አዲሶቹን ግዛቶች በተመለከተም ተመሳሳይ ነው። አዲስ እየተባሉ በሚጠሩት እና ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን በተመለሱት የእኛ ታሪካዊ ግዛቶች ላይም የውጭ አጋሮችን ለመሳብ ዝግጁ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የሩሲያው የአልሙኒየም ኩባንያ ሩሳል ትልቅ ማቅለጫ በተከለበት የሳይቤሪያው ክራዝኒያስክም ሩሲያ እና አሜሪካ የአልሙኒየም ምርት ላይ ሊተባበሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
- ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ሀብቷን ለመስጠት የምትደራደረው ለምንድን ነው?ከ 9 ሰአት በፊት
- አሜሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ብዙዎችን ባስደነቀ ሁኔታ ከሩሲያ ጋር ወገነችከ 9 ሰአት በፊት
- ዘለንስኪ ‘ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ’ አሉ24 የካቲት 2025
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ፑቲን ቃለ መጠይቅ የሰጡት የሩሲያ ካቢኔ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በተመለከተ ስብሰባ ካደረገ በኋላ ነው።
ማክሰኞ ዕለት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ ይህ ዕቅድ “ሰፊ አማራጮችን” እንደከፈተ አንስተው፤ አሜሪካ ብርቅዬ ማዕድናት እንደሚያስፈልጋት እና ሩሲያ እነዚህ ማዕድናት “በብዛት” እንዳሏት ተናግረዋል።
ፑቲን ይህንን ዓይነቱን ጣልቃ ገብነት ያሳዩት ዩክሬን የማዕድን ክምችቷን ለመክፈት ስምምነት እንድትፈጽም ከትራምፕ አስተዳደር የሚደረግባት ጫና እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው።
እንደ ኪዬቭ ግምት ከሆነ አምስት በመቶ የሚሆነው የዓለም ወሳኝ ጥሬ እቃዎች የሚገኙት ዩክሬን ውስጥ ነው። ይኹን እንጂ የተወሰኑት የማዕድን ክምችቶች ሩሲያ ከሦስት ዓመት በፊት በፈጸመችው ወረራ ተይዘዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን የሰጠችው ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያ እርዳታ 500 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን በዚህ ወር መጀመሪያ የተናገሩት ትራምፕ፤ አገራቸው የዚህን ገንዘብ ያህል የሆነ የዩክሬን ማዕድን እንድታገኝ እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ይህንን ቁጥር የተቃወሙት ሲሆን፣ ከአሜሪካ ጋር የሚፈጸም ማንኛውም ስምምነት የደኅንነት ዋስትናንም ያካተተ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የአውሮፓ እና የዩሮ-አትላንቲክ ጥምረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦልጋ ስቴፋኒሺ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረገው ድርድር “በጣም ገንቢ እንደነበር እና ከሞላ ጎደል ሁሉም ቁልፍ ዝርዝሮች መጠናቀቃቸውን” ሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።
ምንም እንኳ ከአሜሪካ የተለየ አካሄድ ቢከተልም የአውሮፓ ኅብረትም በተመሳሳይ ማዕድናትን ለማግኘት የሚያስችለውን አጋርነት ከዩክሬን ጋር ለመፍጠር ሀሳብ አቅርቧል።
የአውሮፓ ኅብረት የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ኮሚሽነር ስቴፋን ሴጆርኔ ይህንን ዕቅድ፤ “ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት” ሲሉ ገልጸውታል።