
ከ 8 ሰአት በፊት
ቻሪቲ ሙቱሪ ከለጋ እድሜዋ ጀምሮ ራስን ስለ ማጥፋት ታስብ ነበር።
ዕድሜዋ ወደ 30ዎቹ ሲገፋ ደግሞ ባይፖላር (በሁለት የስሜት ጽንፍ መካከል መዋለል) እንዳለባት ተነገራት።
ወደ አእምሮዋ አሁንም አሁንም የሚመላለሰውን ራስን የማጥፋት ሐሳብ ዝም ከማሰኘት ይልቅ ስለ አእምሮ ጤና ማስተማር እና መወትወትን ምርጫዋ አደረገች።
እንዲህ ዓይነት ሐሳቦች ከማኅበረሰቡ፣ ከቤተሰብ እና ከጓደኛ የሚያስከትለውን መገለል በሚገባ የምትገነዘበው ቻሪቲ፣ በከፍተኛ ጭንቀት፣ድባቴ ውስጥ ላሉ ሰዎች ተገቢውን ሕክምና እና ክትትል ማቅረብ እንጂ ቅጣት እንደማይገባቸው በማለት መንግሥት ይህንን ከግምት እንዲያስገባ ለጉዳዩም ትኩረት እንዲሰጥ ሳትታክት መሥራትን መርጣለች።
ቻሪቲን የሚያውቋት ሁሉ በአንድ ድምጽ ከራሷ በላይ ሌሎችን የምታስቀድም፣ ጠንካራ፣ ጊዜዋን ሌሎችን ለመርዳት የምታውል ሲሉ በአንድ ድምጽ ይመሰክሩላታል።
“ልክ እንደ ስሟ፣ ቻሪቲ [ጥሩ ነገር ማድረግ] በፍቅር የተመላች፣ ለእኔ ማለት የማታውቅ፣ መስዋዕት የምትከፍል ናት” ይላል ታናሽ ወንድሟ ቶም ሙቱሪ።
ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ቻሪቲ ራሷን አጠፋች።
ነገር ግን በሕይወት ዘመኗ በአእምሮ ጤና ላይ የሠራቻቸው የተለያዩ ሥራዎች በኬንያ ያለውን ግንዛቤ ቀይሮታል።
ለውጥ በ’ኢ-ሕገ መንግሥታዊ’ ሕግ ላይ
የአእምሮ ጤና ላይ የሚያስተምሩ ሁሉ የቻሪቲ ያለመታከት ስለ አእምሮ ጤና መወትወት እና መቀስቀስ ኬንያ ራስን ማጥፋት ላይ ያላትን ሕግ ዳግም እንድትመለከተው በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ።
በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ራስን ለማጥፋት መሞከርን እንደ ወንጀል የሚቆጥረውን ሕግ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው ብሏል።
ከዚህ በፊት ራሱን ለማጥፋት ሙከራ የሚያደርግ ማንኛውም ግለሰብ በሁለት ዓመት እስር አልያም በገንዘብ ወይንም ደግሞ በሁለቱም ይቀጣ ነበር።
ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ግለሰቦች የአእምሮ ጤና ድጋፍ እና ሕክምና ከማግኘት ይልቅ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆነው ቅጣት ይጣልባቸው ነበር።
በጥር ወር ላይ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በአእምሮ ጤና እክል የሚሰቃዩ ሰዎችን የሚቀጣው ሕግ የጤና ክብካቤ የማግኘት መብታቸውን የሚጋፋ ሆኖ አግኝቶታል።
ከቻሪቲ ጋር በቅርበት የሠራችው የሥነ ልቦና ባለሙያ እና የአዕምሮ ጤና መብት ተሟጋቿ አሚሳ ረሺድ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኬንያውያን ድል ነው በማለት አድንቃ፣ ለፍፃሜውም የቻሪቲ ሚና ከፍ ያለ እንደነበር መስክራለች።
“ሞቷ ለምናውቃት በጣም ብርቱ ህመም ነበር፤ ይህ ውሳኔ እርሷ በቀጣይ የምትታወስበት ይሆናል” ትላለች።
ይኹን እንጂ ረሺድ የአእምሮ ጤና ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ ለማምጣት እና ተቀባይነትን ለማግኘት የሚደረገው ትግል ይቀጥላል ሲል አሁን በርካታ የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ትናገራለች።
“ራስን ማጥፋትን በተመለከተ የባህሪ፣ የአመለካከት እንዲሁም የማኅበረሰብ ለውጥ ልናመጣባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ” ትላለች።

የኢትዮጵያ ሕግ እራስ ማጥፋትን እንዴት ይመለከተዋል?
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጠፉ የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ቢሆንም አብዛኛው ክስተት ግን ከአእምሮ ጤና ጋር ትስስር አለው። በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን እንዲሁም የሚወዱትን ሰው ማጣት አንዳንድ ሰዎችን ለዚህ ከባድ እርምጃ ሊገፏቸው ይችላሉ።
በአብዛኞቹ የዓለም አገራት ራስን የማጥፋት ሙከራ እንደ ወንጀል ድርጊት ሳይሆን የአእምሮ ጤና እክል ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ በአንዳንድ አገራት ደግሞ ራስን የማጥፋት ሙከራ በወንጀል የሚያስጠይቅ እና ቅጣን የሚያስከትል ነው።
ከአፍሪካ ጋምቢያ፣ ማላዊ፣ ናይጀሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ራስን የማጥፋት ሙከራን እንደ ወንጀል ድርጊት ቆጥረው በወንጀል ሕጋቸው ደንግገውት ይገኛል። በመሆኑም በአገራቱ ራስን ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራ ከፍ ሲል እስከ 1 ዓመት በሚደርስ ቀላል እስር ወይም ቀለል ያሉ ቅጣቶችን ያስከትላል።
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ራስን የማጥፋት ሙከራ በግልጽ በወንጀል ሕጉ ተደንግጎ አይገኝም። በወንጀል ሕጉ በግልጽ ያልተደነገገ ድርጊት እንደ ወንጀል ተቆጥሮ እንደማያስቀጣ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 2 የሕጋዊነት መርኅ እንደሚያትት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ አበባየሁ ጌታ ይናገራሉ።
በመሆኑም በወንጀል ሕጉ ራስን ከማጥፋት ጋር ተያይዞ ሊያስቀጣ የሚችለው አንድ ሰው ራሱን እንዲያጠፋ ማነሳሳት እና ድጋፍ ማድረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ በአንቀጽ 542 ይደነግጋል።
በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው ሌላን ሰው ራሱን እንዲያጠፋ ያነሳሳ ወይም የረዳ እንደሆነ፣ ራስን የመግደል ሙከራው በተደረገ ጊዜ በቀላል እስራት ራስን የመግደሉ ተግባር በተፈጸመ ጊዜ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ መምህሩ ያስረዳሉ።
አቶ አበባየሁ አክለውም በሌላም በኩል ይህ ድርጊት ከፍ ባለ ቅጣት ማለትም ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችለው ራሱን እንዲገድል እርዳታ የተደረገለት ወይ የተነሳሳ ሰው በወቅቱ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ወይም በአእምሮ ህመም ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ ችሎታ ያልነበረው ሲሆን ነው ብለዋል።
በተለምዶ ራስን የማጥፋት ሙከራ በኢትዮጵያ በወንጀል እንደሚያስቀጣ የሚነገር ቢሆንም በወንጀል ሕጋችን በግልጽ የተደነገገ ነገር የለም። እንደ ወንጀል ሕጉ የሕጋዊነት መርኅ መሠረት ደግሞ አንድ ድርጊት ሕገወጥነቱ በሕግ በግልጽ ያልተደነገገውን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደ ወንጀል ሊቆጥረው እና ቅጣት ሊያስተላልፍ አይችልም ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።
- በሁለት የስሜት ጽንፍ ውስጥ መዋለል- ባይፖላር ዲስኦርደር17 ሰኔ 2022
- ዘግታችሁ የወጣችሁትን በር እንዳልተዘጋ የሚያሳስባችሁ የአእምሮ ሕመም – ኦሲዲ28 ነሐሴ 2022
- የአእምሮ ጤና እክል የሆነው ባይፖላር ዲስኦርደር ምንድን ነው? ለምንስ ከታዋቂው ሠዓሊ ጋር ተያያዘ?30 መጋቢት 2024
ከወንጀል ሕጉ ባሻገር ያሉ ሥራዎች
ራስን የማጥፋት ሙከራ ወንጀል ታሪክ ውስብስብ ነው።
በቅኝ ግዛት ዘመን፣ ብዙ የአፍሪካ ቅኝ ገዢዎች ራስን ማጥፋትን የሚቃወሙ ሕጎች ነበሯቸው፤ እና ብዙ አገራት አሁን እነዚህን ሕጎች ሲሽሩ፣ አንዳንዶቹ ከነጻነት በኋላም ይዘዋቸው ቀጥለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2023 ራስን ለማጥፋት መሞከር ወንጀል አይደለም በተባለባት በጋና፣ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ምንም እንኳ ስር የሰደደ ባህል እና እምነት ፈታኝ ቢሆኑም ሕዝቡ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንደሚታይ ይናገራሉ።
የጋና የአእምሮ ጤና ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አኩዋሲ ኦሴይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ራስን ማጥፋትን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ የአመለካከት ለውጥ ስለመደረጉ የተመዘገቡ ማስረጃዎችን ለማግኘት ጊዜው ገና ቢሆንም፣ በአገሪቱ ውስጥ “ራስን ስለ ማጥፋት እና ራስን ለማጥፋት ሙከራ ማድረግ ላይ የተሻለ ግንዛቤ” እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
በኬንያ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች የፍርድ ቤት ውሳኔው ግለሰቦች ክስ እና እስር ሳይፈሩ እርዳታ እንዲፈልጉ እንደሚያበረታታ ተስፋ አድርገዋል።
ሆኖም ሕዝቡን ለማስተማር ተጨማሪ ጥረት እስካልተደረገ ድረስ ራስን ከማጥፋት ጋር በተያያዘ ያለው መገለል እንደሚቀጥል ብዙዎች ያምናሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ክልላዊ ጽህፈት ቤት የአእምሮ ጤና ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቺዶ ማድዝቫሙሴ “ወንጀል አይደለም ማለት አንድ እርምጃ ነው፣ አሁን ግን ስለ አእምሮ ጤና በአጠቃላይ ይበልጥ ግልጽ ወደሆነ ሀቀኛ ንግግሮች መሻገር አለብን” ብለዋል።
“የሕብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር ትምህርት፣ ግንዛቤ እና ርህራሄ የተመላበት የድጋፍ ሥርዓቶችን ይጠይቃል” ብለዋል።

ለለውጥ ተግዳሮት የሚሆኑ ባህላዊ አመለካከቶች
በበርካታ የአፍሪካ ማኅበረሰቦች ራስን ማጥፋት በግልጽ ውይይት የማይደረግበት ርዕሰ ጉዳይ ነው።
ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እምነቶች ብዙውን ጊዜ ከጤና ጉዳይ ይልቅ የሞራል ውድቀት አድርገው ይቀርጹታል፤ ይህም የተጎዱ ቤተሰቦችን በግልጽ ሐዘናቸውን ለመግለጽ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል።
በኬንያ ቤተሰቦች መገለልን በመፍራት እራስን በማጥፋት የተከሰተን ሞት መንስኤን መደበቅ የተለመደ ነገር ነው።
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ራሳቸውን በማጥፋት የሚሞቱ ሰዎች ባህላዊ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ይከለከላሉ፤ ቤተሰቦችም ማግለል ሊደርስባቸው ይችላል።
አገራት ሕጎቻቸውን ቢያሻሽሉም እንኳ እነዚህ የባህል ተግዳሮቶች ግለሰቦች ድጋፍ እንዳይፈልጉ ያደርጋቸዋል።
በብዙ የአፍሪካ አገራት ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ራስን የማጥፋት ሙከራዎችን ይቃወማሉ።
የናይጄሪያ የክርስቲያን ማኅበር ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፒተር ኦጉንሙዪዋ ለሚፈጸም በደል ምላሽ ሕይወትን የመውሰድ ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው ይላሉ።
“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ዋና ሕጎች አንዱ ‘አትግደል’ የሚለው ነው” ሲሉም አክለዋል።
“በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ ምንም ዓይነት ይቅርታ የማያሰጥ ኃጢአት ነው፤ በተለይም ሆን ተብሎ ሲደረግ።”
ነገር ግን ሊቀ ጳጳስ ኦጉንሙዪዋ እንዳሉት የአእምሮ ህሙማን መሆናቸውን በሕክምና ምስክር ወረቀት ለሚያረጋግጡ የተለየ ሁኔታ ሊደረግ ይችላል ።
በተመሳሳይ ኬንያዊው የእስልምና መምህር እና የኬንያ ሙስሊሞች ከፍተኛ ምክር ቤት የሕግ እና ሃይማኖት አማካሪ ሼክ ኢብራሂም ሊቶመ ራስን ማጥፋት በእስልምና እምነት የተከለከለ ነው ይላሉ።
“ሕይወት የአላህ ናት፤ ማንም በገዛ እጁ እራሱን ለማጥፋት መብት የለውም። በዓለም ዘንድ ቅጣት የለም፤ ግን በመጨረሻይቱ ዓለም ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ብለዋል።
“ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ እና የተረፉት ያለ ጥርጥር ኃጢአት ሠርተዋል” በማለት ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው ይላሉ።
በሕይወት የተረፉ ሰዎች ተስፋን ለማግኘት እንዲረዳቸው ቅጣት ሳይሆን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ሲሉም ያክላሉ።
ኬንያዊቷ የአእምሮ ጤና ተሟጋች አሚሳ ራሺድ ከሃይማኖት ባሻገር እንደ ቋንቋ ያሉ ባህላዊ ሁኔታዎች መገለልን ያጠናክራሉ ብላ ታምናለች።
ስዋሂሊ ለአእምሮ ጤና እክል የተጋለጡ ሰዎችን “እብድ” ሲል እንደሚጠራቸው ገልጻ፣ ይህ ቋንቋ የአእምሮ ህመም ያለባቸውን ሰዎች ያርቃል፣ ያገላል፣ ለጥቃት ያጋልጣል ትላለች።
ለአእምሮ ጤና በተለይም ቋንቋዎች፣ አገላለጾችን መቀየር ርህራሄን እና መደጋገፍን ለማዳበር ይረዳል ትላለች።
የሌሎች አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል?
የጋና ልምድ ለኬንያ ሽግግር ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ይሰጣል።
ጋና የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራን ወንጀል አይደለም ካለች በኋላ፤ እርዳታ እና ድጋፍ የመፈለግ ባህሪያትን ለማበረታታት ብሔራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን እና የተሻሻለ የአእምሮ ጤና አገልግሎቶችን ጀምራለች።
ይኹን እንጂ አገሪቱ ውስን በሆነ የአእምሮ ጤና መሠረተ ልማት እና ስር በሰደደ ማኅበራዊ መገለል መካከል እየታገለች ነው።
ራስን ማጥፋት አሁንም ወንጀል በሆነባት ናይጄሪያ፣ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሕጉን ለመቀየር ከመንግሥት ጋር እየሠሩ ነው።
ባለፈው ዓመት ራስን ለማጥፋት መሞከር ወንጀል አይደለም የአእምሮ ጤና ችግር እንጂ የሚለው ላይ የሚሠራ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ሥራ ጀምሯል። ዓላማውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ማቅረብ ነበር።
በናይጄሪያ ያሉ ባለሙያዎች የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በአገራቸው ለሚደረጉት ተመሳሳይ ለውጦች መነሳሳት ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።
የናይጄሪያ የግብረ ኃይል ሊቀ መንበር ቼሉቺ ኦንየመሉክዌ “አንድ ዓመት ተሰጥቶናል፤ በአገልግሎት ውላችን መሠረት እየሠራን ነው” ብለዋል።
“በአንድ ዓመት ውስጥ ሕጉን መቀየር የሚያስችል ረቂቅ ለፓርላማ እናቀርባለን ብለን እናስባለን።”