
Tibebe Samuel Ferenji
ኢሳያስ አፈወርቂ የተባለ በደም የሰከረ አዛውንት እንኳን አንተን እራሱን ማዳን አይችልም።
=========================================
ሻእቢያ የተባለ የአፍሪካ ቀንድ የጉሮር አጥንት፤ ለኢትዮጵያ መቼም አይተኛም። ሻዕብያ አገር መምራት እንደማይችል ከሥራው የበለጠ ምንም ምስክር የለም። ከ 33 ዓመታት በላይ የግፍ የኢሳያስ አገዛዝ፤ ኤርትራና ሕዝቧ ደቀዋል። በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ ንጉሴ ወልደማርያም “ኢሳያስ ጥይት ካልሰሙ እንቅልፍ አይተኙም” የምትል አንድምታ ያላት ጥሩ ጽሁፍ “አንድ ኢትዮጵያ” በተባለ ሬድዮ ላይ አቅርቦ ነበር።
ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራን ሕዝብ እረግጦ የገዛው፤ “ኢትዮጵያ ትወረናለች” በሚል የሃሰት ትርከት ሕዝቡን በፍርሃት በመሸበበ ነው። የኢሳያስ አገዛዝ ያልተዋጋው የጎረቤት አገር የለም። ኢትዮጵያ በልጽጋና አድጋ ማየት አይፈልግም። “እልህ ምላጭ ያስውጣል እንዲሉ” ኢትዮጵያ የአሰብን ወደ ተጠቅማ ከምትበለጽግና ለኢርትራውያንም የእድገትና የብልጽግና በር ከምትከፍት፤ አሰብ እንዲዝግና የአሞራ መጫወቻ እንዲሆን ነው ኢሳያስ የመረጠው።
ይህ የ79 ዓመት ዓዛውንት፤ ወጣቱ ትውልድ ወደ አመራር እንዲመጣ አይፈልግም።የኢርትራ ወጣት ስለአገሩ እንዳይጨነቅና እንዳያስብ፤ በውትድርና እገልግሎት ስም ሸብቦ ይዞታል። ይህ አረመኔ የኤርትራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አይሳስበውም። በእራሱ ፍርሃትና ቅዠት የተሸበበ፤ ከእራሱ ድንክ አስተሳሰብ ነፃ ያልወጣ እንካኳን አገር እራሱን በቅጡ መምራት የማይችል ሰው፤ ዛሬም “በድሮ ዝናው” የሚያሞግሱት የኢትዮጵያ ባንዳዎች ይህ ሰው “ነፃ ያወጣናል” ብለው ማሰባቸው ገራሚ ሊሆን አይችልም። ባንዳ ከዚህ በላይ ርቆ መሄድ አይችልም። ዛሬ “ከኤርትራ ጋር ቆማለሁ” ብሎ የሚደሰኩር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ኩስ የሆነ ዝተት በየማህበራዊ ሚድያው ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። በባንዳነት የሚኮራ ትውልድ ፈጥረናል።
የገጠመን ችግር ይኽው ነው፤ በአገር ብሔራዊ ጥቅምና አገዛዝን በመቃወም መካከል ልዩነት የጠፋቸው “ያልነቁ” አንቂዎች ናቸው ፖለቲካውን የሚያተራምሱት። ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን በጦርነት ለማተራመስ ለሚፈልጉ ኃይሎች ትጥቅና ስንቅ የሚያቀብል፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚያብር፤ በቅናት ደዌ የታመመ፤ ለኤርትራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ነቀርሳ የሆነ ሰው ነው። ኢትዮጵያን የሚተነኩሰው እሱ እንጂ፤ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የፈጸመችው ምንም ትንኮሳ የለም።
ዐብይን እንጠላለን የሚሉ የአስተሳሰብ ድንኮች ግን ኢትዮጵያ ሻዕብያን የመውጋት ዓላማ እንድነደፈች አድርገው የአሰት ትርከታቸውን ይደልቃሉ። ፋኖ የሚል ክብር ስም የያዘ ዝርክርክና አረመኔ ቡድን፤ ኢሳያስን እንድ ግል አዳኙ የተቀበለ ኃይል ለመሆኑ፤ በዋሽንግተን የተቸነከሩት ቱልቱላውቹ ነጋ ጠባ የሚያወሩት ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ ፈጽሟል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን በትዕግስት የሚያልፈው “የኤርትራ ሕዝብ ወንድምና እህት ሕዝብ ነው” ከሚል ለኤርትራ ሕዝብ ካለው ክብር ለመሆኑ የሮኬት ሳይንስ ሊቅ መሆን አያስፈልግም።
እንደ አንድ ትውልደ ኤርትራዊ፤ ኢሳያስ አፈወርቂ በኢርትራ ሕዝብ ላይ የፈፀመው ግፍ ያመኛል።እንደ ኩሩ ኢትዮጵያዊ፤ ኢሳያስ አፍወርቂ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽመው ትንኮሳ ልቤን ይሰብረዋል። ይህ በደም ነፍስ የሚነቀስቅቀስ በደም የተነከረ አጁዛ፤ በቅርቡ እንኳን ሶስት የአዘርባጃን መርከቦችን በኤርትራ የቀይ ባሕር መስመር ሲያልፉ ይዟቸዋል። በርካታ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት፤ መርከቦቹ የጫኑት ወደ ኢትዮጵያ የተላኩ እቃዎችን ነው። አንዱ የሻእብያ ሻማ ላሽ፤ በሚድያው፤ “ኤርትራ በያዘችው መርከብ የተገኘው ወደ ኢትዮጵያ ይሄድ የነበረ የጦር መሳሪያ ነው፤ በመረከቡ ሲጉጓዙ የነበሩ ድሮኖችንና የጦር መሳሪያዎችን ኢሳያስ ለፋኖ ሊሰጥ ነው” እያለ የድንቁርና ታምቡሩን ሲደልቅ ሰማሁ። አዘኑለት እንጂ አላዘንኩበትም። ከሻዕብያ ጫማ ላሽ ከዚህ የተሻለ ነገር አይጠበቅም። ከዚህ የበለጠ ትንኮሳ ከየት ይምጣ? የወያኔ ጄነራሎች ከኢሳያስ ጋር እየመከሩ መሆኑን ዛሬ አፍሪካን ኢንተለጀንስ የተባለ ተቋም ይፋ አውጥቷል። ምክክሩ ማንን ለማጥቃት ነው? “እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ፤ በአሉባልታ ፈረስ አገር አዳረሰ” ይሉሃል ይህ ነው። ትላንት “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” የሚል ጭምብል ያጠለቁ፤ ዛሬ ከፀር ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ሲተባበሩ ማየት፤ ማንነታቸውን ፍንትው አድርጎ ያሳያ ነው። ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ፤ በአድዋም በማይጨውም የባንዶችን ሚና አይተናል። ዛሬም የምናየው ይህንኑ ነው።
በአንድ ወቅት ለነዓምን ዘለቀ ያልኩትን ልድገም። በኢሳያስ መዳን አለ ብሎ ማመን፤ ጥንቸል ከነብር ለማምለጥ የሞተ አንበሳ ጎን እንደመቆም ዓይነት ነው።
አቶ መልስ ዜናዊ እንዳሉት፤ “ኢትዮጵያን ወሮ ታሪኩን ለመናገር የኖረ ማንም ኃይል የለም”። የኢትዮጵያና የኢርትራ ሕዝብ ለሌላ ጦርነት እንዳይዳረግ ፀሎቴ ነው፤ የሚያስፈልገን ትብብር እንጂ ጦርነት አይደለም። አቶ ኢሳያስ ግን እድሜ ልኩን የጥይት ድምጽ ካልሰማ እንቅልፍ ስለማይወስደው፤ ሕይወቱ እያሸለበ ባለበት በዚህ እድሜው ከኢትዮጵያ ጋር ጦነት እገጥማለሁ ካለ፤ አይጥ የሞተችው የድመት አፍንጫን ለማሽተት ስትሞክር የሆነ ታሪክ ይሆናል።
ሰላም ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ፡ ቸሩ እግዚአብሔር የኢትዮጵያና የኢርትራ ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ አብሮ የሚያድግበትን መንገድ ይከፈትልን ያሳይልን።