
* ያልተዘመረላቸው የነጻነት ሰማዕቱ ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ ! [ከፋሽስት ጣሊያን ኮሎኔል ማልታ ወታደሮች እና ከአርበኞች ጋር በተደረገ ውጊያ በ1929 ዓ.ም ጎሬ ውስጥ ተማረኩ]
በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ሞተው ሀገር የሚያጸኑ፣ ተናግረው ጠላትን የሚያሳምኑ እና አስተምረው ትውልድን የሚያቀኑ አባቶች ትናንት ነበሩ፤ ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ ሀገር እንዲጸና ትውልድ እንዲቀና ብራና ፍቀው ቀለም ፈቅፍቀው የሀገራቸውን ታሪክ ከትበው ለትውልድ አሻግሯል፡፡ እነዚያ አባቶች ሀገራቸው በተወረረ፣ ሕዝባቸው በተሸበረ ጊዜ የመከራው ዘመን ብርታት፣ የፈተና ጊዜ ጽናት ኾነው ዘልቀዋል፡፡
በየዘመናቱ ውጣ ውረዶችን አልፋ በነጻነት የዘለቀችው ኢትዮጵያ፣ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ሀገር ያቀኑት ቀናዒ አባቶች ውለታ አለባት፡፡ ፈተናን በትዕግስት፣ መከራን በጽናት ማለፍን የተካኑት ቀደምት ኢትዮጵያዊያን አባቶች በዘመኑ ሀገርን የሚያሻግር፣ ሕዝብን የሚያስከብር መሪ በመቅረጽ በኩል ድርሻቸው የላቀ ነበር፡፡
በዘመነ ምኒልክ በዓድዋ ተራሮች ግርጌ ቅስም ሰባሪ፣ ታሪክ ዘዋሪ ሽንፈትን ያየችው ጣሊያን ለበቀል ዝግጅት አርባ ዘመናትን ወስዳለች፡፡ በሁለተኛው የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ለሀገራቸው ነጻነት ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያዊያን አያሌ ናቸው፡፡ ከሴት እስከ ህጻን፣ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር፣ ከመኳንንቱ እስከ ሹማምንቱ፣ ከቀሳውስት እስከ ነገስታት፣ ከጳጳሳት እስከ መነኮሳት ለፋሽሽት ጣሊያን መገዛት ባርነት ብቻ ሳይኾን ውግዘትም ኾኖባቸው ውድ ህይዎታቸውን ያለስስት ሰጥተዋል፡፡
ብዙ ጊዜ በአምስቱ ዓመታት የአርበኝነት ዘመን ለሀገራቸው አኩሪ ገድል ከፈጸሙ አባቶች መካከል ስማቸው ደጋግሞ የሚነሳው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከአቡነ ጴጥሮስ ስምንት ወራት ቀድመው “እንኳን ሕዝቡ መሬቷ ለጣሊያን መንግስት ቢገዛ የተወገዘ ይኹን” ማለታቸውን ተከትሎ አደባባይ ላይ በጥይት ተደብድበው ሰማዕትነትን የተቀበሉት የነጻነት ሰማዕቱ አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ለመኾኑ ያልተዘመረላቸው የነጻነት ሰማዕት አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ ማን ናቸው?
ከሲመተ ጵጵስና ቀድሞ በነበረ ስማቸው መምህር ኃይለ ሚካኤል ይባሉ ነበር፡፡ በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሀገር በጌምድር እስቴ ወረዳ ልጫ መስቀለ ኢየሱስ በተባለች ቦታ በ1858 ዓ.ም ይህችን ምድር እንደተቀላቀሉ ይነገርላቸዋል፤ አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ፡፡ መሰረታዊውን የመንፈሳዊ ትምህርት ከዳዊት እስከ ጾመ ድጓ ስማዳ ወረዳ ግንዳጠመም ሚካኤል ተሻግረው ከመሪጌታ ዋሴ ዘንድ ተምረዋል ይባላል፡፡ በመቀጠልም ወደ መካነ ሰማያት ቅዱስ ገላውዲዎስ ተመልሰው ድጓን እንደተማሩ ይነገራል፡፡
ከግብጻዊ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ዘንድ ማዕረገ ዲቁናን የተቀበሉት አቡነ ሚካኤል ዘገቦ ጽዮን ቤተ መቅደስ ውስጥ በዲቁና የተወሰነ ጊዜ አገልግለዋል የሚሉት ሊቀ ጉባኤ መሃሪ ጥበቡ ናቸው፡፡ ሊቀ ጉባኤ መሃሪ እንደሚሉት አቡነ ሚካኤል ትምህርታቸውን አጠናክረው የመቀጠል ጽኑ ፍላጎት ስለነበራቸው መካነ ሰማያት ቅዱስ ገላውዲዎስ ደብር ውስጥ ወንበር ተክለው፤ ጉባኤ አስፋፍተው ያስተምሩ ከነበሩት ከመሪጌታ ወልደ ሩፋኤል ዘንድ በመሄድ ድጓን በሚገባ ተምረዋል ይሉናል፡፡
የዜማውን ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ጎንደር አቅንተው ከመምህር ተስፋየ ዘንድ የብሉያት እና ሃዲሳት ትርጓሜዎችን የተማሩት አቡነ ሚካኤል በመቀጠልም ወደ ወሎ ቦሩ ሜዳ ቅድስት ሥላሴ ወርደው ከሊቁ መምህር አካለ ወልድ የሃዲሳት እና የብሉያት ትርጓሜን በሚገባ ተምረዋል፡፡ በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሰፊ ጉባኤ ዘርግተው ያስተምሩ ከነበሩት ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ዘንድ 14ቱን ቅዳሴ ተምረው በወቅቱ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ግብጻዊ አቡነ ማቴዎስ ዘንድ ማዕረገ ቅስናን ስለመቀበላቸው ዶክተር መርሻ አለኽኝ “ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያዊያውያን” በሚል ርእስ 2012 ዓ.ም ላይ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ከማዕረገ ቅስናቸው በኋላ መምህር አባ ኃይለ ሚካኤል የዝቋላ እና የዜና ማርቆስ ገዳማት አበምኔት ኾነው እንደተሸሙ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ የተጣለባቸውን መንፈሳዊ ኅላፊነት በቅንነት ሲወጡ የቆዩት አባ ኃይለ ሚካኤል በአዲስ አበባ ደብረ ፅጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን በልቅና ተሹመው ምዕመናንን ሲያስተምሩ እና ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
በቀደመው ልማድ ለ1 ሺህ 600 ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያ ጳጳሳት የሚመጡት ከሀገረ ግብጽ በአሌክሳንድሪያ ፓትሪያርክ ተሹመው ነበር፡፡ ምንም እንኳን የበቁ እና የላቁ ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ቢኖሩም ከ1922 ዓ.ም በፊት በኢትዮጵያ የሚሾሙት ጳጳሳት ግብጳዊያን እንጂ ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም፡፡ በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሌክሳንድሪያ መንበረ ፓትሪያርክ ጋር ብዙ ጊዜ የፈጀ ድርድር ካደረጉ በኋላ በ1921 ዓ.ም አራት ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ተመርጠው ወደ አሌክሳንድሪያ ተልከው የጵጵስና ማዕረግ እንዲቀበሉ ተደርጓል፡፡
የመጀመሪያዎቹ አራቱ ኢትዮጵያዊያን ጳጳሳት አቡነ ሚካኤል፣ አቡነ አብርሃም፣ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ይስሃቅ ይባሉ ነበር፡፡ መንግሥት በ1923 ዓ.ም ሀገሪቱን በስድስት ክልሎች በመክፈል ለእነዚህ ጳጳሳት ሀገረ ስብከት ሰጣቸው፡፡ አቡነ ሚካኤልም ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ ተብለው ተሾሙ፡፡ የአዜብ ኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክልል የዛሬዎቹን ኤሊ አባ ቦራን፣ ወለጋን እና ከፊል ከፋን ያጠቃልል ነበር፡፡
አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ ተላዊየ አሰሩ ለአቡነ ሃራ ድንግል ተብለው በኢሊባቦር እና ደቡብ ምዕራብ ጠቅላይ ግዛቶች ተሾሙ፡፡ በጎሬ እና አርጆ እንዲሁም በከፋ በመዘዋወር ስብከተ ወንጌልን እያስፋፉ ሃዋሪያዊ ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል፡፡ አቡነ ሚካኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1923 ዓ.ም ጎሬ ሲገቡ ሕዝቡ በደማቅ አቀባበል እንደተቀበላቸው ይነገራል፡፡
ብጹዕነታቸው ሃዋሪያዊ እና መንፈሳዊ ተልዕኳቸውን በእግራቸው እና በከብት ጫንቃ እየተጓዙ ወንጌልን እየሰበኩ እና ቤተ ክርስቲያናትን እያስፋፉ ያስተምሩ ነበር፡፡ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በሀገረ ሰብከታቸው እየተዘዋወሩ ሃዋሪያዊ እና መንፈስ ቅዱሳዊ አገልግሎት እየሰጡ ባሉበት ወቅት የጣሊያን ወራሪ ኃይል ለድጋሚ ወረራ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገባ፡፡
አቡነ ሚካኤል የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን መውረሩን ሲሰሙ እና የኢሊባቦር ሠራዊት ወደ ምሥራቅ ግንባር ኡጋዴን ሲዘምት ብፁዕነታቸው ለሀገር ፍቅር እና ለሀገር ክብር የሚደረግ ተጋድሎ መኾኑን አስተምረው እና አጽንተው ሸኟቸው፡፡ እርሳቸውም ከደጀኑ ጦር ጋር በፆም፣ በጸሎት እና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እየማለዱ ምዕመናንን ሲያጽናኑ ቆዩ፡፡
የጣሊያን ጦር መሃል ሀገር ተነስቶ በብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከት ጎሬ ደረሰ፡፡ የጎሬ እና የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ አቡነ ሚካኤልን አብዝቶ ይወዳቸው እና ያከብራቸው ነበር፡፡ በ1928 ዓ.ም ፋሽሽት ጣሊያንም ኢትዮጵያን ሲወር አቡነ ሚካኤል ሕዝቡ ለጠላት እንዳይገዛ እና ለሀገሩ ክብር እንዲጸና በብርቱው አስተምረዋል፡፡
በዚያን ወቅት ልጅ ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል በጣሊያን ጦር መወጋቱን እና ጠላት ጎንደርን መያዙን ሲሰሙ ከጎጃም ሠራዊታቸውን ይዘው በግንደ በረት በኩል ወደ ሸዋ በመሻገር በወለጋ አድርገው በሰኔ ወር 1928 ዓ.ም ጎሬ ገቡ፡፡ የራስ እምሩ ዓላማ ጎሬ ላይ ጦራቸውን ካደራጁ እና ካጠናከሩ በኋላ ተመልሰው ጣሊያንን በመውጋት አዲስ አበባን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡
ራስ እምሩ ለአራት ወራት በጎሬ ከቆዩ በኋላ በ1929 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ሲነሱ አቡነ ሚካኤልም አብረው ከራስ እምሩ ጦር ጋር ለመዝመት ተነሱ፡፡ ነገር ግን ነጋድራስ ወልደ ሰማያት አቡነ ሚካኤል እድሜያቸው በመግፋቱ ምክንያት እና በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲያግዙ በማበረታታት እንዲቀሩ አደረጓቸው፡፡ የራስ እምሩ ጦርም ያሰበው ሁሉ ሳይሳካለት ወለጋ ላይ በጣሊያን ጦር በመፈተኑ ወደ ኋላ ለመመለስ ተገደደ፡፡
በኮሮኔል ማልታ የተመራው የፋሽሽቱ ጣሊያን ጦርም በሕዳር ወር 1929 ዓ.ም ጎሬን ተቆጣጠረ፡፡ የጣሊያን ጦር ጎሬን ሲቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግሥት እንደራሴ የነበሩት ቢትወደድ ወልደ ጻድቅ እና ሹማምንቱ ጎሬን ለቀው ወደ ካፋ አቀኑ፡፡ አቡነ ሚካኤል ግን በጎሬ ያሉትን ምዕመናን ትቼ አልሄድም በማለት በጎሬ ከሕዝቡ ጋር ቀሩ፡፡
ብፁዕነታቸው በሕዝቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን መከራ ሁሉ ለመካፈል ወስነው በዚያው በጎሬ እንዳሉ የፋሽሽቱ ጣሊያን ጦር የጎሬ ከተማን ተቆጣጠረ፡፡ ብፅዑነታቸው ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ታምቤ በሚባል ኮረብታ ላይ ኾነው ሕዝቡን ሲያስተባብሩ ጠላት እነ አቡነ ሚካኤል በዚያ እንዳሉ መረጃው ደረሰው፡፡ ሠራዊቱን አከታትሎ ወደ አካባቢው በመላክም ውጊያ ከፈተ፡፡ በውጊያውም እረዳታቸው የነበሩት አጋፋሪ ቀለ መወርቅ የመጀመሪያውን ሰማዕትነት ተቀበሉ፡፡ ውጊያው ቀጥሎ ብፁዕነታቸው እና ሌሎች አርበኞችም በጠላት እጅ ወደቁ፡፡
አቡነ ሚካኤል እና አርበኞቹ ወደ ጎሬ ከተማ እንዲወርዱ ተደርገ፡፡ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ላይ አቁመው ለኃያሉ የጣሊያን መንግሥት መገዛት አለብዎት፤ ሕዝቡም እንዲገዛልን ይስበኩልን፤ ይህንን ካደረጉም አብረን በሠላም እንሰራለን በማለት ለማግባባት ጥረት አደረገ፡፡ ነገር ግን አቡነ ሚካኤል ከሀገራቸው ጠላት ጋር አብረው ለመሥራት ፈቃደኛ አለመኾናቸውን አረጋግጠው በድፍረት ፊት ለፊት ተናገሩ፡፡
አስተርጓሚ ተመድቦ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ የተደረጉት አቡነ ሚካኤል “እኔ የማምነው በእግዚአብሔር ነው፤ የማስተምረውም ወንጌልን ነው፤ የምቀበለውም የነጻነት ምልክት የኾነውን የኢትዮጵያን ባንዲራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እና ሕዝብ ዘንድ ጣሊያን የሚባል መንግሥት እኔ አላውቅም፡፡ ለወንበዴ ጣሊያን ወራሪ ጠላት የተገዛ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ አሪዮስ የተወገዘ ይኹን፡፡ እንኳን ሕዝቡ ምድሪቱም እንዳትገዛላችሁ” በማለት በተሰበሰበው ሕዝብ እና ሠራዊት ፊት ውግዘታቸውን አሰሙ፡፡
ንግግራቸውን ወደ ጣሊያንኛ ቋንቋ እየተረጎመ እንዲገልጽ የተመደበው ሰው የአቡኑን ንግግር ሙሉ በሙሉ ለኮሎኔል ማልት ቢናገር ይገድላቸዋል የሚል ሃሳብ ስለገባው ለጥቂት ጊዜ ዝምታን መረጠ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን ንግግራቸውን አለባብሶ ለማለፍ እና አለዝቦ ለመተርጎም ሲሞክር አቡነ ሚካኤል ንግግሩን አስቁመው የተናገርኩትን ሁሉ ሳታዛባ ግለጽ በማለት አስጠነቀቁት፡፡ ይህን ተከትሎም ተርጓሚው የጳጳሱን ንግግር ሙሉ በሙሉ በትክክል ተርጉሞ አሰማቸው፡፡
ኮሎኔል ማልት የብፁዕነታቸውን የዓላማ ፅናት እና ቁርጠኝነት ከተመለከተ በኋላ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ወሰነ፡፡ አቡኑ ለመረሸን ሲቆሙ ለጥቂት ደቂቃዎች ጸሎት ለማድረስ ፋታ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ፈቃድ አገኙ፡፡ ጸሎታቸውን እንደጨረሱም ግንባራቸውን በመስቀላቸው ላይ እንደደፉ “በል እንግዲህ የፈለከውን ፈጽም” ብለው በመናገር ጸጥ አሉ፡፡ በሕዝቡ ፊት በአደባባይ እንዳሉ ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሰማዕትነትን ከአቡነ ጴጥሮስ ስምንት ወራትን ቀድመው ተቀበሉ፡፡
አቶ ዘውዱ ዱባለ የኢሊባቦርን የተጋድሎ ታሪክ ባሰፈሩበት ማስታወሻቸው እንደሚነግሩን ኮሎኔል ማልት የብፁዕነታቸው አስከሬን እንዲቀበር ባለመፈለጉ በብዙው ከተጉላላ በኋላ በልመና በአምስት ካህናት ብቻ በጎሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማሪያም እንዲያርፍ ተደረገ፡፡
ኢትዮጵያዊያን የነጻነቱን ሰማእት ጳጳስ ዘ አዜብ ኢትዮጵያ አቡነ ሚካኤል እና የሌሎችን መንፈሳዊ አባቶች አኩሪ እና አስተማሪ የተጋድሎ ታሪክ ሲዘክሩም፡-
“ጣና ዘገሊላ ተሰጠው ሥልጣን፣
እኛን ለነጻነት ውኃውን ለወይን።
አርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው፣
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው፣
ሚካኤል ቀድሞ መንገድ ቢመራቸው፣
በኦሜድላ በኩል ብርሃን ወጣላቸው” ይሉ ነበር፡፡