የዩክሬን ማዕድን

ከ 8 ሰአት በፊት

ዩክሬን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ግዙፍ የማዕድን ስምምነት ለማድረግ መስማማቷን ኪየቭ የሚገኙ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለሥልጣኑ እንዳሉት ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር የገባችው የመጀመሪያ ዙር ስምምነት ሲሆን “መልካም ውጤት ሊያስገኝ የሚያስችል” ነው።

ዩክሬናዊው ባለሥልጣን ስለስምምነቱ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አሜሪካ ከማዕድን ሽያጭ የሚገኝ 500 ቢሊዮን ዶላር የግሏ ለማድረግ አቅርባው የነበረውን ጥያቄ ብትተውም በጦርነት ለተጎዳችው ዩክሬን ጥበቃ ለማድረግ ቃል አልገባችም።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑ አቻቸው ቮለድሚር ዘለንስኪ በያዝነው ሳምንት ወደ ዋሺንግተን መጥተው ስምምነት እንደሚፈርሙ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ሳምንት የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው እንደነበር አይዘነጋም።

ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ንግግር ሲያሰሙ ከዩክሬን ጋር ስምምነት መደረሱን ባይናገሩም በስምምነቱ መሠረት ዩክሬን “ጦርነት የመቀጠል መብቷን ታገኛለች” ብለዋል።

“በጣም ጀግና ናቸው” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ትራምፕ ነገር ግን “ያለ አሜሪካ ገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ይህ ጦርነት በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቅ ይችል ነበር” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው የጦር መሣሪያ ድጋፍ ይቀጥል ይሆን ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ “ምናልባት ከሩሲያ ጋር ከስምምነት እስክንደርስ. . . ስምምነት ሊኖረን ይገባል። ካልሆነ ግን ይቀጥላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በዩክሬን “የሰላም አስከባሪ ኃይል” እንደሚሰማራም ጠቁመዋል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ነው የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪን “አምባገነን” ሲሉ የዘለፏቸው። አክለው ለጦርነቱ መጀመር ሩሲያ ሳትሆን ዩክሬን ናት ተጠያቂ የሚል ወቀሳ አሰምተዋል።

ይህ የሆነው የአሜሪካን ከማዕድን ሽያጭ የሚገኝ 500 ቢሊዮን ዶላር ይገባኛል ጥያቄ ዩክሬን ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ ነው።

ዘለንስኪ በበኩላቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንት “በተሳሳተ መረጃ ዓለም” የሚኖሩ ሰው ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ከዩክሬን ማዕድን የሚገኘው ገቢ ይገባናል የሚል ሐሳብ የሚያነሱት አሜሪካ በጦርነቱ ወቅት ለዩክሬን ከፍተኛ ገንዘብ መጠን ያለው ድጋፍ ማድረጓን አስመልክቶ ነው።

ትራምፕ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የሰጠችው ድጋፍ ከ300 እስከ 350 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ሲሉ ማክሰኞ ተናግረዋል።

ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው በዩኤስ እና በዩክሬን መካከል የማዕድን ስምምነት ቢደረስም ጉዳዩ ገና ጅማሮ ላይ ያለ ነው።

ዩክሬን ያሏት ማዕድኖች የትኞቹ ናቸው?

ከዓለማችን “ወሳኝ ጥሬ ማዕድናት” ውስጥ 5 በመቶ ያህሉ በዩክሬን ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል።

ይህ 19 ሚሊዮን ቶን የተረጋገጠ የግራፋይት ክምችትን ያጠቃልላል።

የዩክሬን የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ግዛት ኤጀንሲ እንዳለው ከሆነ አገሪቱ በግራፋይት ክምችት “ከአምስት ዋና ዋና መሪ አገሮች መካከል አንዷ ነች።”

ግራፋይት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎችን ለመሥራት ያገለግላል።

በተጨማሪም ዩክሬን ለባትሪዎች ቁልፍ ግብዓት የሆነው ሊቲየም፣ ከጠቅላላው የአውሮፓ ክምችት መካከል አንድ ሦስተኛው ይገኝባታል።

ከሩሲያ ወረራ በፊት ደግሞ ከአውሮፕላን ጀምሮ እስከ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ የሚውል ቀላል ክብደት ለማምረት የሚያገለግለው ቲታኒየም የምርት ድርሻዋ የዓለም 7 በመቶ ነበር።

በተጨማሪም ዩክሬን እጅግ በጣም ብዙ ብርቅዬ የማዕድናት ክምችት አላት።

እነዚህም የጦር መሳሪያዎች፣ የንፋስ ኃይል ተርባይኖች፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ሌሎች በዘመናዊው ዓለም አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን ለማምረት የሚያገለግሉ የ17 ንጥረ ነገሮች ስብስብ ናቸው።