
ከ 9 ሰአት በፊት
በፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር እና በካናዳ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ካናዳዊያን የቱጃሩ ኢላን መስክ ዜግነት እንዲሰረዝ ፊርማ እያሰባሰቡ ነው።
ከአምስት ቀን በፊት የተጀመረው ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ መስክ ከካናዳ ብሔራዊ ጥቅም በተፃራሪ እና ሉዓላዊነቷን በሚያንኳስስ መልኩ ተሳትፏል ሲል ይከሳል።
በካናዳ ዜግነት የሚነጠቀው ማጭበርበር ሲፈፀም፣ አንድ ሰው በተሳሳተ መንገድ ራሱን ሲገልፅ አሊያም ለኢምግሬሽን ወይም ዜግነት ማመልከቻ መረጃ ሲደብቅ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የተወለደው መስክ የካናዳ እና አሜሪካ ጥምር ዜግነት አለው።
የካናዳ ዜግነቱ በእናቱ በኩል ያገኘው ነው።
ቢሊየነሩ ስለፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻው በኤክስ ገፁ “ካናዳ እውነተኛ አገር አይደለችም” ብሎ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ልጥፉን አጥፍቶታል።
ፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻው ከበርቴው መስክ “ገንዘባቸውን እና ስልጣናቸውን ምርጫችን ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ተጠቅመዋል” የሚል ሲሆን፤ “የውጭ አገር መንግሥት አባል በመሆን የካናዳን ሉዓላዊነት ለማጥፋት እየሞከሩ ናቸው” በማለትም ይከሳል።
ዘመቻውን እስካሁን ከ250 ሺህ በላይ ካናዳዊያን የፈረሙት ሲሆን እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ ክፍት ነው።
ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻው ተምሳሌታዊ እንጂ በሕግ ማስፈፀም የሚያስችል አይደለም።
- የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትይዩ መንግሥት ለመመሥረት እያደረገ ያለው ጥረት ምን ያመለክታል?26 የካቲት 2025
- የዩክሬን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነት ማድረጋቸውን አስታወቁከ 9 ሰአት በፊት
- እናትነትን ሸሽተው በፈቃዳቸው መካን መሆንን የሚመርጡት ሴቶች26 የካቲት 2025
ይሁን እንጂ በካናዳ 500 ሰዎች የሚፈርሙት ዘመቻ በእንደራሴዎች ምክር ቤት አባል ድጋፍ ካገኘ አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥት ምላሽ ይሰጠዋል።
የአሜሪካ እና የካናዳ ግንኙነት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የተካረረ ሲሆን፤ አዲሱ ፕሬዝዳንት ካናዳን ለመጠቅለል ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ ከመናገር ባለፍ በካናዳ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጣል እየዛቱ ናቸው።
የካናዳ መሪዎችም ለእርምጃው አፀፋ እንደሚሰጡ እየገለፁ ነው።
የአገራቱ መቃቃር በመንግሥታቱ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ካናዳዊያን በተቃውሞ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ መሰረዝ፣ የአሜሪካን ምርቶች አለመጠቀም እና በስፖርታዊ ጨዋታዎች ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር መቃወም ተስተውሏል።
ከበርቴው ኢላን መስክ 18 ዓመት ሲሞላው ከደቡብ አፍሪካ ወደ ካናዳ ጠቅልሎ በመሄድ የኮሌጅ ትምሕርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ወደ አሜሪካ አቅንቷል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጠንካራ ፖሊሲዎች የሚደግፈው መስክ፤ በአሜሪካ የትምሕርት ቪዛ ሕገ ወጥ ሥራ ሠርቷል የሚል ውንጀላም እየቀረበበት ነው።
የቴስላ ስራ አስፈፃሚ ውንጀላውን ያጠጣለ ሲሆን በሕገ ወጥ መንገድ ሥራ አልሠራሁም የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
እ.አ.አ በ2002 ተፈጥሯዊ የአሜሪካ ዜግነት ማግኘቱን የግል ታሪኩ ያትታል።