ኔሊ ናይሱላ ሲሮኒካ
የምስሉ መግለጫ,ኔሊ ናይሱላ ሲሮኒካ

ከ 9 ሰአት በፊት

የ28 ዓመቷ ኬንያዊት ኔሊ ናይሱላ ሲሮኒካ ልጅ መውለድ ዕቅዷ ሆኖ አይያወቅም።

ኔሊ ለዚህ ነው በማህጸኗ ልጅ እንዳይፈጠር የሚያደርገውን ሕክምና ያደረገችው። በዚህ ሕክምና የመጣ መካንነት ፈጽሞ የሚቀለበስ አይደለም።

ባለፈው ጥቅምት ወር በሕይወት ዘመኗ ፈጽሞ እርግዝና እንዳፈጠር በሚያደርገው የሕክምና ሂደት ውስጥ አልፋለች።

ይህ ሂደት ቱባል ሊጌሽን (tubal ligation) የሚሰኝ ሲሆን፣ የዘር እንቁላሎች ወደ ማህጸን የሚሄዱበትን መተላለፊያ የማቋረጥ ቀዶ ሕክምና ነው።

ይህ ማለት አንዲት ሴት በማህ ጸኗ ውስጥ ሽል የሚፈጠርበትን በር እስከ መጨረሻው መዝጋት እንደ ማለት ነው።

“አሁን ነጻነት ተሰምቶኛል” የምትለው እና በአንድ መሥሪያ ቤት ተቀጥራ የምትሠራው ወጣት፣ ሂደቱ “መጪው ጊዜ የራሴ ብቻ እንደሆነ ያረጋገጥኩበት ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሕክምናው የእንቁላል መተላለፊያን በመቁረጥ ሴቶች በቋሚነት መውለድ እንዳይችሉ የሚያደርግ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ “መተላለፊያን የመቋጠር” ሂደት ተብሎ ይገለጻል።

ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2023 ባሉት ሦስት ዓመታት በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር በግርድፉ 16 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች የእንቁላል መተላለፊያቸው እንዲቆረጥ በማድረግ በዘላቂነት የሚያመክነውን ሕክምና እንዳደረጉ የኬንያ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ሆኖም ግን ይህንን ሕክምና ካደረጉት ሴቶች መካከል ምን ያህሎቹ ቀደም ሲል ልጅ ይኑራቸው አይኑራቸው የሚገልጸው ነገር የለም።

በናይሮቢ የጽንስ እና ማህጸን ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኔሊ ቦሳሪ በሕክምና መሃን ለመሆን የሚመጡ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ይናገራሉ።

“በተለመደው መንገድ ይህንን የሕክምና ሂደት የሚወስዱት ብዙ ልጆች ያሏቸው ሴቶች ነበሩ” የሚሉት ሐኪሟ አሁን ግን ይህ መቀየሩን ያስረዳሉ።

“አሁን ላይ ትንሽ የልጆች ቁጥር ያላቸው ሴቶች ለሕክምናው ሲመጡ እንመለከታለን” ይላሉ።

ከዚህ ሕክምና በኋላ ሴቶች መልሰው ልጅ መታቀፍ ቢፈልጉ የመሆን ዕድሉ እጅግ የጠበበ ነው።

በሕክምና ሂደት መካን መሆን ወደፊት ልጆችን መውለድ እንደማይፈልጉ እርግጠኛ የሆኑ ሴቶች ብቻ እንዲያልፉበት የሚመከረውም ለዚያ ነው።

“ሐኪሞች በዚህ መልኩ የሚደረግ መካንነትን አያበረታቱትም። ምክንያቱም አንዴ ከሆነ በኋላ የመቀለበስ ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው” ይላሉ የጽንስ እና ማህጸን ሐኪሟ።

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ኔሊ የመጣችው በርካታ አባላት ካሉት ቤተሰብ ሲሆን፣ በኬንያ ሴት ልጆች እንዲወልዱ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጠበቅም ይህ ጫና አላሳደረብኝም ትላለች።

አባቷ ትምህርት ላይ እድታተኩር እና የንባብ ፍቅር እንዲኖራት ትልቅ አስተዋጾ ማበርከታቸውን በመግለጽ ታመሰግናቸዋለች።

እንደ ቶኒ ሞሪሰን፣ አንጄላ ዴቪስ እና ቤል ሁክስ ያሉ የአሜሪካ ‘ፌሚኒስት’ ፀሐፊያን ‘ዓይኗን እንደከፈቱላት’ ትናገራለች።

“ከልጆች ጋር ያልተያያዙ የሴቶች ሕይወት ታሪክ ይመስጠኛል። እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ሊኖር እንደሚችል ተረድቼበታለሁ” ትላለች።

ይህንን በሕክምና መካን የመሆን ዕቅድ ለዓመታት ስታውጠነጥን ብትቆይም በቂ ገንዘብ እና የተረጋጋ ሥራ እስክታገኝ ድረስ ቆይታለች።

ይህ ሕክምና በግል የሕክምና ተቋማት 30 ሺህ የኬንያ ሽልንግ ወይም 230 ዶላር ይጠየቅበታል።

ኔሊ በዓለም ዙሪያ የሴቶች መብት እየተሸረሸረ እንደሆነ ታምናለች።

ለዚህም በአውሮፓውያኑ 2022 በአሜሪካ ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መነሳቱን አስታውሳ ይህ ለውሳኔዋ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ትናግራለች።

ሴቶች የራሳቸውን ሰውነት ራሳቸው የመቆጣጠር መብታቸው ሌላም ቦታ ሊነካ ይችላል የሚለው ስጋት በሕክምና ሂደቱ እንድታልፍ አድርጓታል።

ውሳኔውን ለቤተሰቦቻቸው ስትነግራቸው ብዙም አልተገረሙም። ምክንያቱም ሁልጊዜም ልጆች የሌሉበት ሕይወትን መምራት እንደምትፈልግ ትነግራቸው ስለነበር ነው።

ስለ ፍቅር ግንኙነትስ ምን ታስቢያለሽ ተብላ ስትጠቅ ትከሻዋን በመስበቅ “ስለእሱም እስካሁን እያሰብኩበት ነው” ብላለች።

ሕጻናት የሌሉበትን ሕይወት እፈልጋለሁ የምትለው ኔሊ ብቻ አይደለችም። በልማድ ሴትነትን ከእናትነት ጋር የማገናኘት እሳቤ እየተገዳደሩ ያሉ ሌሎች ሴቶችም አሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከመውለድ ይልቅ በሕክምና መምከንን እንደሚመርጡ በአደባባይ የሚናገሩ ሴቶች ይታያሉ።

ከእነዚህ መካከል የንድፍ ባለሙያዋ እና የፖድካስት አዘጋጇ ሙቶኒ ጊታው ትግኝበታለች።

ሙቶኒ ጊታው
የምስሉ መግለጫ,ሙቶኒ ጊታው

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በሕክምና መካን የሆነችበትን ሂደት እና ስለውሳኔዋ የሚገልጽ 30 ደቂቃ ቪዲዮ በዩቲዩብ ላይ አጋርታለች።

“ልጅ አልፈልግም ብዬ ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጽኩት 10 ዓመቴ አካባቢ ይመስለኛል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

እናቷ ያኔ ድርስ እርጉዝ ነበረች። እናም ያንን ስትመለከት “የእኔ መጪ ጊዜ ምን ሊመሰል ይችላል?” የሚል ጭንቀት የወለደው ጥያቄ ተፈጠረባት።

“ምርጫዬን የሚያከብር አጋር ሳገኝ፣ ዓለምን እየተጓዝኩ ስመለከት እና ልጆች የሌሉበትን ሕይወት በወደፊቱ ሕይወቴ ውስጥ እመለከታለሁ” ትላለች።

ልክ እንደ ኔሊ ሁሉ ሙቶኒም ይህ ውሳኔ የመጣው ሕይወትን በራሷ መንገድ ለመኖር ከመወሰን ነው።

የእርግዝና መቆጣጠሪያ እንከብል ስትወስድ የሚፈጠረባትን ጥሩ ያልሆነ ስሜት ለማስቀረት እና ቋሚ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ ነው ይህንን የሕክምና ሂደት ያገኘችው።

ሕክምናውን አውቃ ሐኪም ስታናግር ያጋጠማት ግን ተቃውሞ ነበር። ሐኪሙ ልጆች ከፈጣሪ የሚሰጡ በረከቶች እንደሆኑ አስረዳት።

“ልጆች የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥምሽስ?’ ብሎ ጠየቀኝ” ትላለች።

“ሐኪሙ ፊት ለፊቱ ካለሁት ታካሚ ይልቅ በምናቡ ያለውን ሰው ከግምት አስገብቷል” ስትል ትናገራለች።

ሙቶኒ ፍላጎቷ ተቀባይነት አላገኘም። ይህም ልቧን ሰብሮታል። ዳግም ይህንን ፍላጎቷን ለማሰካት ሌላ 10 ዓመታት አስፈልጓታል።

የማህጻን እና ጽንስ ሐኪሟ ቦሲሬ በኬንያ ያለው ትልቁ ችግር ታካሚዎች በራሳቸው ጤንነት ላይ የሚያሳልፉትን ውሳኔ አለመቀበል ነው።

“ይህ ከባህላችን ጋር የተሳሰረ ነው። በሕክምና መካን መሆን እንደ ትክክለኛ ነገር አይቆጠርም” ይላሉ።

ሌላኛው ኬንያዊ የማህጸን እና ጽንስ ሐኪም ዶክተር ኪሬኪ ኦማናዋ ጉዳዮ በሥራ ባልደረቦቹ እና ከፍ ሲልም በሕክምና ማኅበረሰብ ውስጥ አከራካሪ እንደሆነ ይናገራል።

“እልባት ሳይገኝለት እስካሁን ያለ ጉዳይ ነው” ሲል አክሏል።

በሕክምና መካን የመሆን ውሳኔዋ ውደቅ የተደረገባት ሙቶኒ ተስፋ አላስቆረጣትም። ባለፈው ዓመት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሚሰጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ወደሚገኝ ሐኪም አምርታለች።

ስለውሳኔዋ በሚገባ ለማብራራት እና ጥያቄዎችን ለመጋፈጥ ተዘጋጅታ ብትሄድም ተቃውሞ አልገጠማትም። “ሐኪሙ መልካም ሰው ነበር” ብላለች።

አሁን ላይ የፍቅር አጋር የሌላት ዲዛይነሯ በውሳኔዋ ደስተኛ እንደሆነች እና የራሷን ሕይወት ሯሷ ብቻ እየተቆጣጠረች እንደሆነ እንደሚሰማት ተናግራለች።

የ34 ዓመቷ ሴት ከዓመት በፊት ሰለ ሕክምና ሂደቷ ከሠራቸው ቪዲዮ ያገኘችው ግብረ መልስ እንዳስደሰታት ገልጻለች።

በዚህ ቪዲዮ ትልቅ የሚባል አሉታዊ አስተያየት ባለመቀበሏም ደስተኛ መሆኗን ትጠቅሳለች።

በርካታ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚያበረታቷት እና ይህም በራስ መተማመኗን እንዳሳደገውም ትናገራለች።

“ሴቶች በብዙ መንገድ ለዓለም አበርክቶ ማድረግ ይችላሉ። ይህ አበርክቶ ሁሉንም የሰው ልጆች በማሳደግ አይደለም። ምርጫ ባለበት በዚህ ጊዜ በመፈጠሬ ፈጣሪን አመሰግነዋለሁ” ስትል ትገልጻለች።