የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ምክትል አዛዥ አብድል ራሂም ዳጋሎ እና የሱዳን ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ - በሰሜን ቡድን መሪ አብደላዚዝ አል ሂሉም እጆቻቸውን እያውለበለቡ
የምስሉ መግለጫ,የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ምክትል አዛዥ አብድል ራሂም ዳጋሎ እና የሱዳን ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ – በሰሜን ቡድን መሪ አብደላዚዝ አል ሂሉም በኬንያ ናይሮቢ የሰላም እና አንድነት መንግሥት ቻርተርን ከመፈረማቸው በፊት

26 የካቲት 2025, 07:01 EAT

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) እንዲሁም አጋሮቹ የሆኑ የፖለቲካ እና የታጠቁ ቡድኖች፤ በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር በሚገኙ የሱዳን ግዛቶች ውስጥ ትይዩ መንግሥት ለመመሥረት የተዘጋጀ ፖለቲካዊ ቻርተር ተፈራርመዋል።

ራሱን “የሱዳን መሥራች ኅብረት” (Sudan Founding Alliance) እያለ የሚጠራው ይህ ቡድን የሚመሠርተው ሥርዓተ መንግሥት ከሃይማኖት የራቀ (ሴኩላር)፣ ዴሞክራሲያዊ እና ያልተማከለ አስተዳደር ያለው እንዲሆን እንደሚፈልግ ይናገራል።

ይህ ሥርዓተ መንግሥት “በነጻነት፣ በእኩልነት እና በፍትሕ” ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ፍላጎቱ መሆኑን ይገልጻል።

ይህ የቡድኑ እንቅስቃሴ በግጭት በወደመችው ሱዳን ላይ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ ከአሁኑ ስጋት እየፈጠረ ነው።

የአገሪቱ ሠራዊት እና ጠንካራ የሆነው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለሥልጣን የተፋጡባት ሱዳን፤ ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ደም አፋሳሽ የሆነ የእርስ በእርስ ጦርነት እየተካሄደባት ነው።

ትይዩ መንግሥት ለመመሥረት የተዘጋጀው ቻርተር ፊርማ የተካሄደው በኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥ በተካሄደ ዝግ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።

የሱዳን ሠራዊት መሪ ጄኔራል አብድል ፋታህ አል ቡርሐን ያሰሙት ተቃውሞ ቡድኖቹን ከመፈራረም አላስቆማቸውም።

ከተፈራራሚዎቹ መካከል የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወንድም እንዲሁም የኃይሉ ምክትል አዣዥ የሆኑት አብድል ራሂም ዳጋሎ አንዱ ናቸው።

የሱዳንንን ደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል ግዛት ክፍሎችን የሚቆጣጠረው የሱዳን ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ – በሰሜን የተሰኘው ቡድን መሪ የሆኑት አብደላዚዝ አል ሂሉም ከፈራሚዎቹ አንዱ ናቸው።

ታድያ ትይዩ መንግሥት መመሥረት ምን ማለት ነው?

ቀውስ ውስጥ ያለች ሀገር

አርኤስኤፍ የተመሠረተው፤ ከዚህ ቀደም የሱዳን መንግሥትን ወክሎ ሲዋጋ ከነበረው አመጸኛው የጃንጃዊድ ሚሊሺያ ሲሆን፣ የሚመራውም ሄሜቲ ተብለው በሚታወቁት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ነው።

ኃይሉ ዳርፉር፣ የካርቱም የተወሰኑ ክፍሎች፣ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል አካባቢዎችን ጨምሮ ብዙ የሱዳን ግዛቶችን ይቆጣጠራል።

ይሁንና፤ እስካሁን 60 ሺህ ሰዎችን የገደለው ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በምን ዓይነት መንገድ እንደ ደመወዝ መክፈል፣ ታክስ መሰብሰብ፣ ውሃ እንዲሁም የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን ማቅረብ ያሉ መሠረታዊ የመንግሥት ኃላፊነቶችን እንዴት ሊወጣ እንደሚችል ግልፅ አይደለም።

በዳርፉር የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሙስባህ አይሳ፤ “በዳርፉ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ትይዩ መንግሥት ስለመቋቋሙ እርግጠኛ አይደሉም። ምክንያቱም ቡድኑ የሲቪል ጉዳዮችን ወይም የሕዝብ አገልግሎቶችን ማስተዳደርን በተመለከተ ቅርፅ ያለው ፕሮግራም የለውም” ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ሠራተኞች፤ ግጭት 12 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ባፈናቀለባት ሱዳን ስላለው ሁኔታ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ ሲሆን፣ ሁለቱም የአርኤስኤፍ እና የሠራዊቱ ኃይሎች አሰቃቂ ተግባራትን በመፈጸም ተከስሰዋል።

ሙስባህ፤ “አርኤስኤፍ የሚቆጣጠራቸውን አካቢዎች የማስተዳደር አቅም ይጎድለዋል፤ ለዚህም ማሳያው አስተዳደር ለማቋቋም ሙከራ ባደረጉባቸው ግዛቶች ደኅንነትን ለማስጠበቅ አለመቻላቸው ነው” ይላሉ።

በገበያ ስፍራ ላይ እየተቀጣጠለ ያለ እሳት

ፖለቲካዊ ስሌት ወይስ ተስፋ መቁረጥ

የትይዩ መንግሥቱ ዕቅድ ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ አራት ደረጃዎች ያሉት የፌደራል መንግሥት ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት የፌደራል፣ የክልል፣ የግዛት እና አካባቢያዊ መንግሥታትን የሚይዝ ነው።

በተጨማሪም የሴኔት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ብሔራዊ ፓርላማ እንዲቋቋም እንዲሁም የሽግግር ጊዜ ሕገ መንግሥት የሚያረቅ ሕገ መንግሥታዊ ኮሚሽን እንዲመሠረት በዕቅዱ ውስጥ ተካትቷል።

ቻርተሩ፤ ከአውሮፓውያኑ 1956ቱ የሱዳን ነጻነት አዋጅ በስተቀር በአሃዳዊው የመንግሥት ሥርዓት የተላለፉ ውሳኔዎችን በሙሉ ይሽራል።

አርኤስኤፍ፤ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ቁልፍ ፖለቲካዊ ቡድኖች ድጋፍ አግኝቷል።

ድጋፋቸውን ከሰጡት ቡድኖች መካከል፤ በሀገሪቱ የሚገኙ አነስተኛ ፓርቲዎችን የሚወክለው የዴሞክራሲያዊ ሲቪል ኃይሎች ትብብር (Coordination of Democratic Civil Forces) አንዱ ነው።

በአገሪቱ ደቡባዊ እና ምዕራባዊ ግዛቶች ታሪካዊ ተፅዕኖ ያለው የሱዳን ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ – በሰሜን እንዲሁም በሱዳን ጥንታዊ እና የበዚያ ተፅእኖ ከሚፈጥሩ ተቃዋሚ ቡድኖች አንዱ የሆነው ኡማ ፓርቲ (National UMMA Party) ድጋፋቸውን የቸሩ ሌላኛዎቹ ቡድኖች ናቸው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይህ እንቅስቃሴው ፖለቲካዊ መሠረቱን ለማስፋት እንዲሁም በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ለማግኘት እንደሚያግዘው ያምናል። ነገር ግን በቀጣናው የሚገኙ ተንታኞች ይህ እርምጃ ኃይሉን አይጠቅምም ባይ ናቸው።

ሙስባህ አይሳ፤ “ለአርኤስኤፍ ድጋፍ የሰጡት ፓርቲዎች እና እንቅስቃሴዎች በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ይላል።

እርዳታ ለማግኘት የተሰለፉ ሰዎች

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ሱዳን፤ የትይዩ መንግሥቱ ምሥረታ የተካሄደባትን ኬንያ፤ አርኤስኤፍን በመደገፍ የከሰሰች ሲሆን፣ ከሀገሪቱም አምባሳደሯንም ጠርታለች።

ኬንያ በበኩሏ፤ ሰላም ለማምጣት ለሚደረግ ጥረት ብቻ በገለልተኝት የንግግር መድረክ ማመቻቸቷን በመግለጽ ራሷን ተከላክላለች።

ከዚህ ቀደም ያላትን በቀጣናው የሚደረጉ ንግግሮችን የማስተባበር ልምድንም በማሳያነት ጠቅሳለች።

ይሁንና ኬንያ ተቃውሞ ከማስተናገድ አላመለጠችም። ብዙዎችም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በመደገፍ ሱዳንን ይበልጥ አለመረጋጋት ውስጥ እየከተቱ ነው በሚል ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን ከስሰዋል።

የአሜሪካ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሴናተር ጂም ሪች በኤክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ባለፈው ዓመት ለ150 ሺህ ሰዎች ሞት አስተዋፅኦ የነበረው በአርኤስኤፍ የተመራ አሰቃቂ ድርጊት የዘር ጭፍጨፋ ተብሎ በኮንግረስ እንዲጠራ የተደረገውን ጥረት ስመራ ነበር። ባለፈው ጥር ይህ ጉዳይ የአሜሪካ ፖሊሲ ሆኗል።

“አሁን ደግሞ የአሜሪካ አጋር የሆነችው ኬንያ፤ ሰላም መፍጠር በሚል ስም የአርኤስኤፍ ዘር ጨፍጫፊ አገዛዝ በሱዳን ተቀባይነት እንዲያገኝ እያገዘች ነው። ይህ እውነቱን ለማድበስበስ የሚደረግ የማይታሰብ ሙከራ ነው፤ ጭፍጨፋውንም አያስቆምም” ሲሉ ናይሮቢን በብርቱ ወቅሰዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁልፍ በሆኑ አካባቢዎች፤ በተለይም በካርቱም አካባቢ ከሚገኙ ሦስት ከተሞች ሁለቱ በሆኑት ሰሜን ካርቱም እና ኦምዱራማን ሽንፈት አጋጥሞታል።

የሱዳን ሠራዊት መዲናዋን እንደገና ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እና የራሱን መንግሥት መመሥረት ይፈልጋል።

እነዚህ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ያሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ያለውን ቁጥጥር ለማጠናከር እንዲሁም ጦርነት የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች በተለይም ኃይሉ የያዛቸውን ግዛቶች ለማጠናከር እየሠራ ነው።

በሱዳን ተመራማሪ እና የፖሊሲ ተንታኝ ሆነው ሃሚድ ካላፋላ፤ “ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተለይም በቅርብ ሳምንታት በስትራቴጂክ አካባቢዎች ከተሸነፈ በኋላ፤ ስትራቴጂውን መቀየር እንዳለበት አስተውሏል። አሁን ድርድር ውስጥ የሚገቡ ከሆነ የመደራደር አቅማቸው ተዳክሟል። ይህም ለእነርሱ የማያደላ ውጤት ሊያመጣባቸው ይችላል” በማለት ያብራራሉ።

ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቁልፍ የሀብቶች ላይ ያለው ቁጥጥር አሁንም በሱዳን ለቀጠለው ተጽዕኖው እና የኃይል ተለዋዋጭነት ዋነኛ ምክንያት ነው።

ኃይሉ ካሉት ትላልቅ ሀብቶች መካከል አንዱ በዳርፉር የሚገኘው የወርቅ ማውጫ ነው።

ሱዳን፤ ከአፍሪካ ዋነኛ ወርቅ አምራች ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን እነዚህ ማዕድናት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ ናቸው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወርቅ ማውጫ ቦታዎች መቆጣጠሩ ወታደራዊ እንቅስቃሴያቸውን ለመደገፍ የሚያስችል ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ይሰጣቸዋል።

አርኤስኤፍ ከወርቅ በተጨማሪ በተወሰኑ የሱዳን ነዳጅ በሚገኝባቸው አካባቢዎችም ይገኛል፤ በተለይም በደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል ግዛቶች።

ምንም እንኳ የሱዳን ሠራዊት የአገሪቱን ትላልቅ ነዳጅ አምራች አካባቢዎችን የሚቆጣጠር ቢሆንም፤ አርኤስኤፍ በእነዚህ አካባቢዎች መገኘቱ ከነዳጅ ኤክስፖርት እንዲያተርፍ ያደርገዋል።

ሃሚድ ካላፋላ፤ ይህ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ያለው ቁጥጥር ሱዳንን ለበለጠ ብዝበዛ እንደሚዳርግ ይናገራሉ። “ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን የማውጣት ሥራ ተስፋፍቷል” ይላሉ።

በስተመጨረሻም ግን ይላሉ ሃሚድ፤ “ሁለቱም ወገኖች የኢኮኖሚ ኢምፓየር እየፈጠሩ ነው። እውነተኛ ተጎጂው ግን ሀብቱ በሕገ ውጥ መንገድ ባሕር ማዶ እየተሸጠበት ያለው የሱዳን ሕዝብ ነው።”

የተሰበሰቡ ሰዎች፤ ሰዎችን የጫነ መኪናን ከበው

ቀጣናዊ መዘዝ

ከዚህም ቀደም ግጭት ባለባቸው የተለያዩ ዞኖች ትይዩ መንግሥታት ተመሥርተው ያውቃሉ።

ለምሳሌ በሊቢያ በአውሮፓውያኑ 2011 ከሙአመር ጋዳፊ መውደቅ በኋላ ሁለት ባላንጣ መንግሥታት ተመሥርተው ነበር።

በወቅቱ አገሪቱ፤ ትሪፖሊ ከተማ በሚገኘው እና በታጣቂ ቡድኖች እና ሚሊሺያዎች በሚደገፈው መንግሥት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተዋንያን በተለይም በግብፅ እና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በሚደገፈው በቶብሩክ የሚገኝ መንግሥት መካከል ተከፍላ ነበር።

ሰላም ለማምጣት ዓለም አቀፍ ጥረቶች ቢደረጉም ሁለቱ ባላንጣ መንግሥታት በቅጡ ለመምራት አልቻሉም ነበር። ሁኔታው ተባብሶም ሀገሪቱን ወደተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነት የከተታ ሲሆን፣ ይህም አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት እንዲቀጥል አድርጓል።

በሱዳን ተመራማሪ እና የፖሊሲ ተንታኙ ሃሚድ፤ “አርኤስኤፍ፤ የውጭ ኃይሎች ተቃራኒ ወገኖችን ሲደግፉ ከታየበት የሊቢያ ሁኔታ ልምድ ወስዶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እንደ ሊቢያ ሁሉ ይህ አካሄድ መረጋጋትን አያመጣም፤ ክፍፍሉን ይበልጥ ያጠናክራል እንጂ። ሱዳን ከእንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ አትጠቀምም” ሲል ስጋቱን ይገልጻል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትልቁ የቤት ሥራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘት ይሆናል። በናይሮቢ ስብሰባ የማድረግ ውሳኔ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ የማሰባሰብ ሙከራ እንደሆነ ባለሙያዎች የሚናገሩ ሲሆን፣ ያለእንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ሊመሠረት ያለው መንግሥት መቀጠል እንደማይችል ያሰምሩበታል።

አሁን ባለው ሁኔታ የተለያዩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች በተለይም ዳጋሎ፤ በቀጠለው ግጭቱ ውስጥ ላላቸው ተሳትፎ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እየተጣለባቸው ነው።

ከእነዚህ ማዕቀቦች መካከል በአሜሪካ የተጣለው የጉዞ ዕቀባ እና በአገሪቱ የሚገኝ ማንኛውም ንብረት ላይ የተጣለው እገዳ ይገኝበታል። የአውሮፓ ኅብረትም በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች ላይ የጉዞ እና የሀብት እገዳ ጥሏል።

ሁለት ዓመት ሊደፍን የተቃረበው ግጭት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማፈናቀሉ በአገሪቱ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ እያባባሰው ነው።

ውጥረቱ እየጨመረ ሲመጣ የሱዳን አለመረጋጋት ወደ ጎረቤት አገራትም ሊዛመት ይችላል። የትይዩ መንግሥት መመሥረትም ውጥረቱን ይበልጥ እንደሚያቀጣጥል ተመራማሪ እና የፖሊሲ ተንታኙ ሃሚድ ይናገራሉ።

“ወደ ሱዳን ድንበር የሚደረግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አሁንም ተመልክተናል። አገሪቱ ይበልጥ ከተከፋፈለች ይህ ጉዳይ፤ እንደ ግብፅ ያሉ ጎረቤት አገራት እና ሌሎች አገራት ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ ጣልቃ እንዲገቡ ሊያደርግ እና በፍጥነት ወደ ቀጣናዊ ግጭት ሊለወጥ ይችላል” ሲል ስጋቱን ይገልጻል።