ኑድልስ

ከ 1 ሰአት በፊት

በአንድ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት የሚቀርበው ኑድልስ የተሰኘው ምግብ ጣፋጭ መሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ መናኘቱን ተከትሎ ቻይናውያን ምግብ አፍቃሪዎች ለቀስተኛ መስለው ወደ ማዕከሉ እየጎረፉ እንደሆነ ተነገረ።

ኤርሎንግ የተሰኘው የቀብር አስፈጻሚ በደቡባዊ ምዕራባዊ ግዛት በምትገኘው ጊዝሁ ግዛት ይገኛል።

የቀብር አስፈጻሚው በማዕከሉ ምግቡን የሚያቀርበው ለኃዘንተኞች ቢሆንም የኑድልሱ ጣፋጭነት ዜና መናኘቱን ተከትሎ በርካታ ተመጋቢዎች ሐዘንተኛ በመምሰል ምግቡን ለመሞከር እየመጡ እንደሆነ ተገልጿል።

ኤርሎንግ በበኩሉ እውነተኛ ኃዘንተኞችን እስካልረበሹ ድረስ አንዳንድ የህብረተሰቡ ክፍሎች በግቢው እንዲመገቡ እንደሚፈቅድ አስታውቋል።

የቀብር አስፈጻሚው በቁርስ፣ እና እራት ሰዓት የተለያዩ የኑድልስ አይነቶችን ያቀርባል። የአንድ ሰሃን የኑድልስ ዋጋ 1. 38 ዶላር ነው። በጣም ታዋቂው ኑድልስ የደቀቀ የአሳማ ስጋ እና ኦቾሎኒ ጋር ተቀላቅሎ የተሰራው ነው።

አንድ የኤርሎንግ ሰራተኛ እስካሁን ባለው አገልግሎት የሚሰጡት ለኃዘንተኞች እንደሆነ ጂዪፓይ ኒውስ ለተሰኘው የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በርካቶች አንድ ሰሃን ኑድልስ ለማግኘት ተደብቀው እየገቡ እንደሆነ የተናገሩት ሰራተኛ በኤርሎንግ ያሉ ወረፋዎች በጣም ከመርዘማቸው የተነሳ ምግብ ለማግኘት ለሁለት ሰዓታት ያህል መጠበቅ እንዳለባቸው ተገልጿል።

“የሟች ዘመዶች መስለው የሚመጡ ሰዎች አሉ። ሲጨናነቅ መለየት ከባድ ነው። ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ፈታኝ ነው” ብለዋል።

በርካቶች መጉረፋቸውን ተከትሎ የቀብር አስፈጻሚው ድርጅት “ኃዘንተኞችን እስካልረበሹ 50 ሳህን ኑድል ለህብረተሰቡ በየቀኑ በነጻ ለመስጠት መወሰኑን የኤርሎንግ ሼፍ ከኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

ኑድልሱ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ቢሆንም ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ጓደኛውን ለመጠየቅ ሄዶ ስለ ምግቡ ያጋራው ልጥፍ ታዋቂ ሆኗል።

“ጓደኛዬ በዚህ የቀብር አስተናባሪ ድርጅት የሚያቀርበው ምግብ በጣም ጣፋጭ ነው። የምግብ ወረፋው ለሟቾች አበበቦች ለማስቀመጥ ካለው ወረፋ ይረዝማል” ሲል ግለሰቡ ሺያሆንግሱ ወይም ሬድ ኖት በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፏል።

ከዚያን ጊዜ ጀምር በርካታ ቻይናውያን ኑድልሱን የተመገቡ ሲሆን ስለ ምግቡም የሚሉትን በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው አጋርተዋል።

የቻይናው ቲክቶክ በሚባለው ዱዩን አንድ ተጠቃሚ የመመገቢያ አዳራሹን ቲኬት ፎቶ አጋርቶ ለምግብ የተሰለፈውን ህዝብ ለማሳየት አጋርቷል።

“እዚህ ያለው ኑድልስ በጣም ጣፋጭ እንደሆነ ሰምቻለሁ። ህይወት አጭር እንደሆነ አስቤ፤ ሌላ ኑድልስ አዘዝኩ” ሲሉ አስፍረዋል።