
ከ 6 ሰአት በፊት
አሜሪካዊ ያልሆኑ ባለሃብቶች ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የመሥራት እና የመኖር መብት የሚሰጣቸውን “የወርቅ ካርድ” በአምስት ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸጡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።
አሜሪካ የዶናልድ ትራምፕን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ አገሯ በሚገቡ ሰዎች ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር እያጠበቀች ባለበት ጊዜ ይፋ የተደረገው ይህ ካርድ በሂደት ዜግነት ለማግኘት በር የሚከፍት መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል።
ይህንን ካርድ ከጽህፈት ቤታቸው ሆነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባስተዋወቁበት ጊዜ “የወርቅ ካርድ እንሸጣለን” ሲሉ አሜሪካ መክፈል ለሚችሉ የመኖሪያ የተለየ ፈቃድ ማዘጋጀቷን አመልክተዋል።
“ግሪን ካርድ አለ። ይኼኛው የወርቅ ካርድ ነው። ካርዱ ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ይኖረዋል። ካርዱ ግሪን ካርድ ሚሰጠውን ልዩ መብቶችን ይሰጣል። በተጨማሪነትም ዜግነት ለማግኘት በር የሚከፍት ይሆናል። እናም ሃብታም ሰዎች ይህንን ካርድ በመግዛት ወደ አገራችን ይመጣሉ” ብለዋል።
“ሃብታም እና ስኬታማ ይሆናሉ። በርካታ ገንዘብ ያፈሳሉ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በታክስ ይከፍላሉ፤ በርካታ ሰዎችን ይቀጥራሉ፤ በመሆኑም ውጤታማ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።
ሕጋዊ ነው ያሉት የካርዶቹ ሽያጭ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ካርዶች ሊሸጡ እንደሚችሉ ትራምፕ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ካርዶቹን ለሩሲያ ባለሃብቶች ለመሸጥ እንደሚያስቡ የተጠየቁት ትራምፕ “በትክክል። በጣም ጥሩ የሆኑ አንዳንድ የሩሲያ ባለሃብቶችን አውቃለሁ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የንግድ ሚንስትሩ ሃዋርድ ሉትኒክ ከትራምፕ ጎን ቆመው በሰጡት አስተያየት ካርዱ ኢቢ-5 የስደተኛ ኢንቨስተር ቪዛ ፕሮግራምን የሚተካ መሆኑን ጠቁመዋል።
- በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ካናዳዊያን የኢላን መስክ ዜግነት እንዲነጠቅ ፊርማ እያሰባሰቡ ነውከ 9 ሰአት በፊት
- የኳታር አየር መንገድ ከጥንድ ተጓዦች አጠገብ ሬሳ በማስቀመጡ ይቅርታ ጠየቀከ 9 ሰአት በፊት
- እናትነትን ሸሽተው በፈቃዳቸው መካን መሆንን የሚመርጡት ሴቶች26 የካቲት 2025
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ኢቢ-5 የውጭ ባለሃብቶች ሥራ በሚፈጥሩ የአሜሪካ ፕሮጀክቶች ላይ ገንዘብ እንዲያፈሱ እና ወደ አሜሪካ የሚያስገባቸውን ቪዛ እንዲያመለክቱ የሚያስችላቸው ነው።
“በእርግጥ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዓለም አቀፍ ዜጎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ በማጣራት ሂደት ማለፍ አለባቸው” ሲሉም ሉትኒክ አክለዋል።
በአውሮፓውያኑ 1992 በአሜሪካ ኮንግረስ ይፋ ተደረገው ኢቢ-5 በተሰኘው መርሃ ግብር መሠረት ለአሜሪካ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቢያንስ አንድ ሚሊዮን 50 ሺህ ዶላር ወይም ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ 800 ሺህ ዶላር ለሚያፈሱ ስደተኞች ግሪን ካርድ ይሰጣል።
ከትራምፕ እና ከቤተሰቡ ጋር የተገናኙ ንግዶችም መርሃ ግብሩን በመጠቀም የቤቶች ልማት ለመደገፍ ተጠቅመውበታል።
ፕሮግራሙ በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በኮንግረስ ውስጥ ካሉ የሕግ አውጪ አካላት ብዙዎች ከዓላማው ያፈነገጠ እና ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው በማስጠንቀቅ ትችት ተሰንዝሮበታል።
በ 2019 የትራምፕ አስተዳደር ክፍያውን ዝቅተኛ ኢንቨስትመንት ባለባቸው አካባቢዎች 900 ሺህ ዶላር እና በሌሎች ቦታዎች ደግሞ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ሙከራ አድርጎ ነበር።
ሕጉን የፈቀደው የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ በትክክል አልተሾመም በሚል የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ ለውጡን በ2021 ውድቅ አድርጎታል።
ፕሮግራሙ ለመጨረሻ ጊዜ ማሻሻያ ተደረገበት በ2022 በጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት ሲሆን፣ የኢንቨስትመንት መስፈርቶቹ አሁን ባሉበት እንዲሆኑ ተደርገዋል።
ሄንሊ ኤንድ ፓርትነርስ እንደተባለው ተቋም ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የስፔን፣ የግሪክ፣ የማልታ፣ የአውስትራሊያ፣ የካናዳ እና የጣሊያንን ጨምሮ ወደ 100 የሚጠጉ የዓለም አገራት “ወርቃማ ካርድ” ለባለሃብቶች ይሸጣሉ።
ኢቢ-5 ቪዛ በቁጥር ተገደ ቢሆንም ትራምፕ ግን እስከ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ “ወርቃማ ካርድ” በመሸጥ የአገሪቱን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ማሰባቸውን ታይም ዘግቧል።
የዜግነትን መስፈርቶችን በተመለከተ የአገሪቱ ኮንግረስ የሚወስን ቢሆንም “ወርቃማው ካርድ” የኮንግረሱን ይሁንታ እንደማይፈልግ ትራምፕ ገልጸዋል።