
Saturday, 22 February 2025 11:22
Written by Administrator

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ለመነጋገር ከመንግሥት አቅጣጫ እንዳልተሰጠው ገልጿል። ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ ውስጥ ያልተካተቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማካተት ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ከትላንት በስቲያ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል የሦስት ዓመታት የስራ ክንውኑንና ወቅታዊ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጠው ኮሚሽኑ፤ በ10 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በርካታ ስራዎች እንደተጠናቀቁ አመልክቷል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለጹት፤ አካታችና አሳታፊ የሆነ አገራዊ ምክክር ለማከናወን በተሰራው ሥራ ከ1 ሺሕ 333 ወረዳዎች ውስጥ 1 ሺሕ 231 ወረዳዎች ላይ የተሳታፊ ልየታ ተከናውኗል፡፡
ይህ ስራ በተለያዩ ተባባሪ አካላት አማካይነት መከናወኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ከዲያስፖራው ማሕበረሰብ ጋር ደግሞ በርካታ የበይነ መረብ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ “በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱ መድረኮች ላይ ሕዝቡ በነጻነት ሃሳቡን ገልጿል” ሲሉም አስረድተዋል።
በምክክር ጉባዔ የውክልና መድረኮች ወደ 57 ገደማ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ስራዎች ከ1 ሺሕ 260 በላይ የጥቃቅንና ንዑስ ቡድኖች አጀንዳ ሰነዶችን፣ በተጨማሪም 120 የተጠቃለሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳ ሰነዶችን እንደተረከበ ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅሰዋል። 12 የተጠቃለሉ የክልልና የከተማ አስተዳደር አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ መቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
“በሚቻለው መጠን የምክክር ሂደቱን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ተችሏል” ሲሉ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ የገጠሙ ፈተናዎች በዋናነት አገሪቱ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት እየተናጠች መገኘቷና በኮሚሽኑ ነጻነትና ገለልተኝነት ዙሪያ የተዛቡና የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሰራጩ መቆየታቸው ተጠቃሽ እንደሆኑ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የተሟላ አለመሆን በኮሚሽኑ ያለፉት ሦስት ዓመታት የስራ ክንውን ላይ ጥላውን ያሳረፈ ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነ ፕሮፌሰር መስፍን አልሸሸጉም።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተደጋጋሚ ዝግጁነቱን በይፋ ቢያስታውቅም፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖችን ለማሳተፍ አስቻይ ሁኔታ አለመፈጠሩን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ከጋዜጠኞች ስለታጣቂዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ኮሚሽነሩ፤ “አንድ የታጣቂ ቡድን መሪ በስልክ ደውሎ በግል አነጋግሮኝ ነበር። እርሱና የሚመራው ቡድን ወደ ጫካ እንዲወጡ ያስገደዳቸው ጥያቄ ትኩረት ካገኘ፣ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ነግሮኛል። ይህንን ጉዳይ ለአገራዊ ምክክር ምክር ቤት አሳውቄያለሁ። እንዲሁም ከደህንነትና ጸጥታ አካላት ጋር ለታጣቂ ቡድኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ አጀንዳ የመቀበል ሂደት እንዲኖርና ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል። ይሁንና የታጣቂው ቡድኑና መሪውን ማንነት በይፋ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ጥያቄ የቀረበው ከኮሚሽኑ ሳይሆን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፣ “ምክክር በአንድ ዓመት የሚጠቃለል አይደለም” በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል። በአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች ላይ ከአገር ምስረታና ሌሎች ከሕገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውጭ “ናቸው” ተብለው የሚለዩ ጥያቄዎች ከቀረቡ ወደ አጀንዳ ውስጥ የመካተት ዕድሉ “ጠባብ ነው” ሲሉ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለተፈቀደው ተጨማሪ አንድ ዓመት ሲናገሩ፣ “ሁሉም ነገር በትክክል ከተካሄደ ጊዜው ይበቃናል” ብለዋል። አክለውም፣ “ምክክር በዚህ ሰዓት ውስጥ ተመካክራችሁ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ‘ስጡ’ የሚባልበት አይደለም። ሕዝቦች ቁጭ ብለው፣ ጊዜ ወስደው ተመካክረው የሚወስኑት ነው፡፡ በቀላሉ የሚወሰኑ አጀንዳዎች ይኖራሉ፤ጊዜ የሚፈጁም ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከአገራዊ ምክክር ራሳቸውን ስላገለሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማብራሪያ የሰጡት ወይዘሮ ሂሩት፣ “ፓርቲዎችን በግልም ሆነ በተለያየ መንገድ በማነጋገር፣ በዚህ ሂደት እንዲሳተፉ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል” ብለዋል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሂደቱ እንዲሳተፉ አሁንም ጥረቱ እንደሚቀጥል ጨምረው ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አያይዘውም፣ “ከዚህ ቀደም ለመናገር ዕድል ያላገኙ ማሕበረሰቦች ዕድል እንዲያገኙ ተደርጓል። በዚህም ስኬታማ ስራ ተሰርቷል” ብለዋል። ለአስፈጻሚ አካላት ተጠቃልለው የሚቀርቡ አጀንዳዎች በመንግሥት በኩል፣ “ይፈጸማሉ የሚል ዕምነት በእኛ በኩል አለ” ሲሉ ገልጸዋል።
ከታጣቂዎች ጋር ንግግር ለማድረግ መንግሥት ለኮሚሽኑ አቅጣጫ አለመስጠቱን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት፤ “ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች አሉ” ብለዋል።