የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀኃፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተ.መ.ድ ዋና ተጠሪና የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ  (ዶ/ር)

ማኅበራዊ ተመድ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ ታወቀ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: February 26, 2025

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለሚደረጉ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡ የሚገኘው የድጋፍ መጠን ዝቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀኃፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተ.መ.ድ ዋና ተጠሪና የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ  (ዶ/ር)፣ ባለፈው የበጀት ዓመት ብቻ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ የሰጠው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ዕርዳታ መቋረጥ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመገምገም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

‹‹ዓለም አቀፍ ለውጦቹ ወደ ምን ያመራሉ የሚለውን ለመረዳት ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄው የተነሳበት አጋራችን በጉዳዩ ላይ ምላሽ ቢሰጥበት የበለጠ የሚሻል ቢሆንም፣ በእኛ በኩል ግን ሁኔታውን እየገመገምን ነው፡፡ አብረውን የሚሠሩ አጋሮቻችንም ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ እንዲደረግላቸው ለማስቻል ጥረት እያደረጉ ነው፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም ከዕርዳታው መቋረጥ ጋር ተያይዞ ያሉ ለውጦችን ተመድ እየተከታተለ መሆኑን፣ በተለይም ከሰብዓዊ መብቶች ጋር ለተያያዙ ዘርፎች የሚሰጡ ድጋፎች በየትኛውም አገር እንዳይቋረጡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን በተመለከተ ከሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ አጋሮች ዕርዳታ ለማግኘት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ጋር በጋራ በመሆን ዕቅድ ለማውጣት በሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ሒደቱ አሁን ከዩኤስኤአይዲ ድጋፍ መቋረጥ ጋር በተለየ ሁኔታ የተያያዘ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም የተመድ ኤጀንሲዎች በየዓመቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ መጠን ለመወሰን የሚከተሉት ሒደት አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በተመድ ኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎች ውስጥ በአንደኛው የሚሠሩ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ዩኤስኤአይዲ ድጋፉን በኢትዮጵያ በማቋረጡ በተለያዩ የሰብዓዊም ሆነ የልማት ዘርፎች ላይ የተፈጠረውን ክፍተት በተመለከተ ግምገማ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2025 ለሚቀርቡ የሰብዓዊ ድጋፎች የሚያስፈልጋት የፋይናንስ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳውቅ ሪፖርት በሁለት ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

‹‹በተመድ ሥር የተለያዩ ኤጀንሲዎች ስላሉ እያንዳንዳቸው በየዘርፋቸው የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ መጠን ካሳወቁ በኋላ፣ ተሰብስቦ የሚጠናቀር ሪፖርት በመሆኑ ነው ይፋ ለመደረግ ጊዜ የወሰደው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ረዳት ዋና ጸሐፊ አልካሮቭ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲውሉ የሚሰጡ የገንዘብ ድጋፎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም በዚህ ዓመት የምታገኘው የፋይናንስ መጠን ካለፈው ዓመት ዝቅ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አሳውቀዋል።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ኃላፊ ፖል ሃንድሊ እንዳስረዱት፣ ባለፈው የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተሟላ ሁኔታ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ እንዲያስችል የተጠየቀው ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የነበረ ቢሆንም፣ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ማግኘት የተቻለው ፋይናንስ ግን በአጠቃላይ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡

የተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ረዳት ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀዳሚ የሰብዓዊና የልማት ዘርፎች ድጋፍ አቅራቢ የሆነችው አሜሪካ፣ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ወደ ማድረግ እንደምትመለስ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዩኤስኤአይዲ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚደረግላቸው አገሮች መካከል ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2024 ብቻ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ተመድቦለት ነበር፡፡ በጀቱም በአብዛኛው ለሰብዓዊ ድጋፎች፣ ለአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ዕርዳታዎች፣ ለልማት፣ ለጤና፣ ለሥነ ምግብ፣ ለውኃና ለአካባቢ ፅዳት ዘርፎች ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች እንዲውል የተሰጠ መሆኑም ታውቋል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዩኤስኤአይዲ ዕርዳታ መቋረጥ በኢትዮጵያ ላይ የከፋ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ባለሙያዎቹ የረድዔት ድርጅቱ ባለፈው በጀት ዓመት ከሰጠው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋው ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከአሜሪካ መንግሥት የውጭ ድጋፍ ዝርዝር መረጃ ማሳያ የመረጃ ቋት የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ባለፈው ዓመት 723.3 ሚሊዮን ዶላር ለአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ድጋፎች፣ እንዲሁም 118.1 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለምግብ ዕርዳታና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ውሏል።

የዕርዳታው መቆም በአገሪቱ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ካሳዩ ሪፖርቶች መካከል ባለፈው ወር የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይፋ ያደረገው፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ዕቅድ አንዱ ሲሆን፣ ሰነዱ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ለ20 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚያስፈልግና ለዚህም ከ299 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘት እንዳለበት ጠቁሟል።

አሜሪካ ለአገሮች የምታደርጋቸው ድጋፎች ላይ ዕገዳ ከጣለች በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት (Malnutrition) ለተጋለጡ ሕፃናት ድጋፍ የሚያደርገው አክሽን አጌንስት ሃንገር (Action Against Hunger) በተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚመራውን ፕሮግራም እንደሚያስቆመው ማስታወቁ ይታወሳል።

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር መጨረሻ ፕሬዚዳንታዊ ቃለ መሃላቸውን በፈጸሙ በሰዓታት ውስጥ፣ አገራቸው በምትሰጣቸው የውጭ ዕርዳታዎች ላይ የጣሉት ዕገዳ ውሳኔ በዘላቂነት ተፈጻሚነት ይኑረው አይኑረው የሚለው ጉዳይ፣ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ባለው ጊዜ እየተገመገመ እንደሚቆይ አስተዳደራቸው ገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዩ ይፋ እንዳደረጉት ሕይወት አድን ለሆኑ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች የሚሰጡ ድጋፎች ከዕገዳው ነፃ ቢደረጉም፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸው እየገለጹ መሆናቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአገር በቀልና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ የድጋፍ ድርጅቶች በኩል ይተገበሩ የነበሩና ዩኤስኤአይዲን ጨምሮ በልማት አጋሮች ፋይናንስ የሚደረጉ 200 ፕሮጀክቶች በዕርዳታ መቋረጥ ተፅዕኖ እንዳደረባቸው መግለጻቸውን፣ በአሜሪካው የተራድኦ ድርጅትና ሌሎችም አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣቸው የነበሩት ፕሮጀክቶች የሚቀርብላቸው ፋይናንስ ዝቅ ሲል በብቸኝነት በዩኤስኤአይዲ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች ግን እየተዘጉ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ዩኤስኤአይዲ ድጋፉን ባቆመበት ወቅት በኢትዮጵያ በምን ያህል የገንዘብ መጠን ስንት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ እንደነበር፣ እንዲሁም ምን ያህል የሥራ ኃይል በፕሮጀክቶቹ ትግበራ ላይ ተሳታፊ እንደሆነ ሪፖርተር በኢትዮጵያ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኤሌክትሮኒክ የመልዕክት ዘዴ (ኢሜይል) ጥያቄ አቅርቦ፣ ኤምባሲው ጥያቄው እንደደረሰውና በተቻለ ፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጥ ቢገልጽም፣ ለኅትመት ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ምላሹን ማግኘት አልተቻለም፡፡