ናርዶስ ዮሴፍ

February 26, 2025

ከከሰም የስኳር ፋብሪካ ከሥራ የተሰናበቱ ሠራተኞች

በአፋር ክልል ዱላሳ ወረዳ የሚገኘው ከሰም የስኳር ፋብሪካ፣ በክልሉ እየተከሰተ ባለው ለወራት የቀጠለ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ይፋ ባደረገ በወሩ፣ ከ3,700 በላይ ሠራተኞቹን ከሥራ ማሰናበቱ ታወቀ። 

በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት ተፈናቅለው በካምፕ የተጠለሉ 3,750 ቋሚና ጊዜያዊ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች፣ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ባልጠበቁት ሁኔታ ከሥራ መሰናበታቸው ተገልጿል፡፡ በድርጅቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ስማቸቸው ተለጥፎ ያነበቡበት የስንብት ማሳወቂያ፣ ዕለቱን አስደንጋጭ እንዳደረገባቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሠራተኞች ገልጸዋል።

ሪፖርተር የተመለከተው የሰነድ ማስረጃ እንደሚያስረዳው፣ ከሥራ ገበታቸው የተገለሉት 1,250 ቋሚ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ የተቀሩት 2,500 ሠራተኞች ደግሞ በሸንኮራ እርሻና በፋብሪካው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ አስተዋፅኦ የነበራቸው ጊዜያዊ የሥራ ቅጥር ውል የነበራቸው ሠራተኞች ናቸው። 

ከሥራው የተሰናበቱት ሠራተኞች በአፋር ክልል በገቢ ረሱ ዞን በአሚበራ ወረዳ በአዋሽ አርባ ቀበሌ በሚገኝ አዲስ ራዕይ የሚል ስያሜ በተሰጠው የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የሠፈሩ ናቸው። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የአካባቢው ነዋሪ፣ ‹‹ካምፑ በጣም ትልቅና ሜቴክ ሠርቶት የነበረ ነው። መጋዘኖችም ጭምር ያሉበት ሲሆን፣ ቢያንስ እስከ 5,000 የሚደርሱ አባወራዎች አሉበት። ከከሰም ስኳር ፋብሪካ ተፈናቃዮች ውጪ፣ ቀደም ብሎ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችም በካምፑ እንዲሠፍሩ ተደርጎ ነበር። ፋብሪካው በሚገኝበት አካባቢ አጎራባች ቀበሌዎች ላይ የነበሩ አርብቶ አደሮች ጭምር በካምፑ ውስጥ ክልሉ አስገብቷቸው ነበር፤›› ብለዋል። 

የፋብሪካው ሠራተኞች ባለፉት ሁለት ወራት ከሚጠጋ ጊዜ አንስቶ አዲስ ራዕይ ተብሎ በሚጠራ ካምፕ ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ከሥራቸው ከተሰናበቱ ሠራተኞች መካከል አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት፣ ‹‹የሥራ ስንብት ደብዳቤ እንኳን አልተሰጠንም። የሁላችንንም ስም ዝርዝር አንድ ላይ ለጥፈው ነው ተሰናብታችኋል ያሉን። ከዚያም አልፎ ከሁለት ወራት ደመወዝ ውጪ የሚታሰብልን ክፍያ እንደሌለም አሳውቀውናል፤›› ብለዋል።

ግለሰቡ እሳቸውና የሥራ አጋሮቻቸው አደጋ ላይ መውደቃቸውንና ከስኳር ፋብሪካው አመራሮችም ሆነ ከሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጉዳዩን በተመለከተ የተሰጣቸው ዝርዝር ማብራሪያ አለመኖሩን ገልጸዋል።

የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ የተገኙት ሠራተኞች የሥራ ስንብት ማሳወቂያውን ከተመለከቱ በኋላ ግራ መጋባት መፈጠሩንና በፋብሪካው ውስጥ፣ እንዲሁም በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞችን ለመለየት በነበረው ጥረት የተወሰነ ግርግር እንደነበር ሪፖርተር ከምንጮች መረዳት ችሏል። 

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ ሠራተኛ በዕለቱ ስለተፈጠረው ሁኔታ ምላሽ ሰጥተዋል።

‹‹በእርግጥ ሠራተኞች እየተጯጯሁ ነበረ። የተወሰኑት የአካባቢው ነዋሪዎች ስለሠራተኞቹ ቀጣይ ሕይወት ተጨንቀው ስለነበር፣ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይችላል ብለው ያመኑትን የረድዔት ድርጅት አመጡላቸው። ከዚያ በኋላ ሥራ አለን ብለው የነበሩ ሠራተኞች ድንገት አደጋ ላይ መውደቃቸውን ሲረዱ፣ እርስ በራሳቸው ተሰባስበው ምዝገባ ማካሄድ ነበር የተጀመረው። ምዝገባውም ማንነታቸውን በማረጋገጥ የዕርዳታ ኩፖን ለማግኘት ነበር። እዚያው በቦታው ላይ ዕርዳታው የሚገባቸውን ለመለየት ከሠራተኞች መካከል የተውጣጡ ኮሚቴዎች ነበሩ። ለእነሱ የስም ዝርዝር ለማስገባት በትክክል የሚገባቸውን ለመለየት የነበረ ጥረት ነው። ከሌላው ጋር ሳይቀላቀል የሕይወት ዘይቤያቸው ድንገት አደጋ ላይ የወደቀባቸው ሠራተኞችን እውነተኛ ማንነት ለመለየት ለማጥራት እየተሞከረ ነው፤›› ብለዋል። 

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓሊ ሁሴን ኡመር ከአንድ ወር በፊት የመሬት መንቀጥቀጡ በከፍተኛ ሁኔታ በአካባቢው እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት፣ ጉዳት በደረሰባቸው ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን ለማውጣት ሥጋት ስለሆነባቸው ማውጣት እንዳልቻሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

ኃላፊው በወቅቱ በፋብሪካው ሠራተኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድሞ እንዲለቁ መደረጉን፣ ከተፈጥሮ አደጋ በተጨማሪ በፋብሪካው ንብረት ላይ ስርቆት እንዳይፈጸም ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከዞን ፖሊስ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረው ነበር። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጮች፣ የፋብሪካው ሠራተኞች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚቀርብላቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ከብሔራዊ አደጋና ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ከአፋር አደጋ መከላከል ቢሮና ከተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች መሆኑንና ከፋብሪካው ግን ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ 

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከሥራቸው የተሰናበቱ ሌላ ሠራተኛ በበኩላቸው፣ ‹‹ዕርዳታ በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት ቢሮዎች በኩል ባለፈው ሳምንም ተሰጥቷል፡፡ ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲታደል ነበር። ከዚህ ባለፈ ግን የፋብሪካው አመራርም ሆነ ሥራ አስኪያጅ አንድም ቀን መጥተው እነዚህ ሠራተኞቻችን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት? ምንስ ያስፈልጋል? እንዴት እናግዝ? ብለው መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ለማየት ዕድል አልሰጡም፤›› ብለዋል።

ሪፖርተር የሠራተኞቹን ጉዳይ አስመልክቶ ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓሊ ሁሴን ኡመር በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ጥሪና አጭር መልዕክት (ኤስኤምኤስ) በመላክ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ፋብሪካውን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አንድ የሥራ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ስለጉዳዩ መረጃ እንዳልነበራቸውና ዝርዝር ጉዳዩን በማጣራት መልስ እንደሚሰጡ ቢያሳውቁም፣ ማተሚያ ቤት እስከሄድንበት ሰዓት ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም።