
February 26, 2025

የብሔራዊ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው ወርቅ ከፍ ማለቱን ተከትሎ፣ ብሔራዊ ባንክ ለወርቅ ግዥ ብቻ ወደ ኢኮኖሚው የሚያስገባው የብር ገንዘብ አቅርቦት በሌላ በኩል የዋጋ ንረትን መልሶ የማባባስ ክስተት እንደሚፈጥር ተለገጸ፡፡
ክስተቱን ለመቆጣጠር፣ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢኮኖሚው የገባውን የብር ገንዘብ አቅርቦት ለመቀነስ ዕርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን አሳውቋል፡፡
የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ብሔራዊ ባንኩ 60 ሚሊዮን ዶላር ለግል ባንኮች ለመሸጥ ጨረታ አውጥቷል፡፡ በጨረታው 27 ባንኮች የተሳተፉ ሲሆን በአማካይ 135.6 ብር ለአንድ ዶላር በማቅረብ ጨረታውን አሸንፈዋል፡፡
ይህም ማለት ባንኮች 60 ሚሊዮን ዶላሩን ለመግዛት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚያስገቡ ሲሆን፣ ይህም በገፍ ወደ ኢኮኖሚው የተሠራጨውን ብር ለመቀነስ እንደሚረዳ የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አብዱልመናን ሞሐመድ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መግለጫም ይኼንን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ ‹‹ከቅርብ ወራት ወዲህ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው ወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ የዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያና ክምችት እጅግ አበረታች ሆኗል፡፡ ይህ አዎንታዊ ውጤት ቢሆንም፣ የማዕከላዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲና ዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር ይገባል፡፡ በመሆኑም ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማለዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት፣ በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ ወስኗል፤›› ይላል፡፡ የብሔራዊ ባንክ መግለጫ፡፡
እንደ አብዱልመናን (ዶ/ር) ትንተና፣ የዶላር ሽያጩ ጨረታ ሁለት ግብ ያለው ሲሆን፣ እነሱም ‹‹ለወርቅ ግዥ ተብሎ በገፍ ወደ ኢኮኖሚ የገባውን ብር መቀነስ፣ እንዲሁም የንግድ ባንኮችን የዶላር አቅርቦት ከፍ ማድረግ›› ናቸው፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወርቅ ወደ ውጭ መላኩን የንግድ ሚኒስቴር ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ወርቁን ከአገር ውስጥ ሲገዛ በትንሹ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ኢኮኖሚ ተሠራጭቷል፡፡
በሌላ በኩል የዚህ ሳምንቱ 60 ሚሊዮን ጨረታ ውጤት ብዙ ነገር እንደሚገልጽ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
በተለይ ባንኮች ጨረታውን ያሸነፉበት 135.6 ብር፣ ለአንድ ዶላር ማለትም፣ ባንኮቹ ላለፉት ሦስት ወራት አካባቢ አንድ ዶላርን ሲገዙ ከነበረበት 126 ብር አካባቢ በ10 ብር ከፍ ያለ ነው፡፡
‹‹ይህ ብዙ ጉዳዮችን ይጠቁማል፤›› ይላሉ አብዱልመናን (ዶ/ር)፣ ‹‹ባንኮች ዶላሩን በ10 ብር ጭማሪ መጫረታቸው ዶላር እንዳጠራቸው ያሳያል፡፡ ላለፉት ሦስት ወራት ምንዛሪ 126 ላይ ቆሞ ቆይቶ በዚህ ጨረታ 135.6 ገባ፡፡ ይህ ማለት የምንዛሪ ገበያው ጤናማ እንዳልሆነና በገበያ እየተመራ እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ ወይም ባንኮች በድብቅ እየተነጋገሩ ከንግድ በምንዛሪ ሽርፍራፊ እየጨመርን አንወዳደርም ብለው ወስነዋል፡፡ ወይም ደግሞ መንግሥት የምንዛሪው ዋጋ ከ126 በላይ እንዳይጨምር ወስኖ ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት ምንዛሪ እየጨመረ በሔደ ቁጥር
መንግሥት ከውጭ የሚያመጣቸው እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ፣ እንዲሁም የውጭ ዕዳ ክፍያ ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚያመጣ ሊሆን ይችላል፤››፡፡
በተጨማሪ የምንዛሪ የጨረታ የዶላር ዋጋን ከ126 ወደ 135.6 ማስገባት የጥቁር ገበያውን ከፍ ሊያደርግ ይችላል ተብሎም ተሠግቷል፡፡ ከባለፈው ወር ወዲህ የጥቁር ገበያ የተነቃቃ ሲሆን፣ ይህም የሚከሰተው ባንኮች በበቂ ሁኔታ ዶላር ማቅረብ ሳይችሉ ሲቀሩ እንደሆነ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡