

የናይል ቀን አከባበር አንዱ ገጽታ የእግር ጉዞ
ማኅበራዊ በአየር ንብረት ለውጥ ሥጋት ውስጥ የታሰበው የናይል ቀን
ቀን: February 26, 2025
‹‹ናይል የሚለው ቃል የሁለቱ አፍሪካውያን ወንዞች የወል ስም ነው፡፡ አንደኛው ናይል ነጭ ናይል የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ዓባይ ብለን የምንጠራው ሰማያዊ ናይል (ጥቁር ናይል) ነው፡፡ ነጭ ናይል ካኔራ የሚባል ወንዝ ከሚመነጭበት ቦታ ፈልቆ፣ የቪክቶሪያን ሐይቅ ቆርጦ ሲመጣ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከጣና ሐይቅ አጠገብ ከሚገኝ አንድ ምንጭ ፈልቆ፣ ሐይቀ ጣናን ሰንጥቆ፣ የሚውዘገዘገው ዓባይ ወንዝ ካርቱም ከተማ ላይ፣ ወንድሙን ነጭ ዓባይ ያገኘዋል፡፡ ከግሪክ ኒሎስ የተገኘው ናይል ፍችውም የወንዝ ሸለቆ ማለት ነው፡፡ ማደርያ ቤቱ በሆነው የሜዲቴራንያን ባሕር እስኪደርስ ድረስ፣ 6,690 ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዝ ማራቶናዊ ወንዝ ነው፡፡››
ይህን ኃይለ ቃል “እናትክን!” በሉልኝ! በተሰኘው ዓባይ ተኮር የግጥም መድበሉ ያሰፈረው ገሞራው በሚል የብዕር ስሙ የሚታወቀው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ ነው፡፡
ገሞራው የተቀኘለትን የዘመረለትን የናይል ወንዝ የሚጋሩ አገሮችን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭን አገሮቹ ከመሠረቱ ሩብ ክፍለ ዘመን ተቆጥሯል፡፡ ተቋሙ በታንዛኒያ ዳሬሰላም የተመሠረተበትን የካቲት 15 ቀን 1991 ዓ.ም. (February 22, 1999) ምክንያት በማደረግም በየዓመቱ የናይል ቀን በየአገሮቹ እያከበረ ይገኛል፡፡
ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የናይል ቀንን ያከበረው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም ሲሆን መሪ ቃሉም ‹‹የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለጋራ ብልፅግና የናይል ትብብርን ማጠናከር›› የሚል ነው፡፡
በሥነ በዓሉ ላይ የተገኙት የናይል ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢው የደቡብ ሱዳን የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ፓል ማይ ዴንግ እንደተናገሩት፣ ‹‹ምናልባት በጣም አሳሳቢው ተግዳሮት እያንዣበበ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ሥጋት ነው፡፡››
ሰብሳቢው አያይዘውም ‹‹የአየር ሁኔታው መለወጥ፣ የዝናብ መጠን መቀነስና ሙቀት መጨመር የውኃ እጥረትን ሊያባብስ እንደሚችል፣ የግብርና ምርታማነትን እንደሚያስተጓጉልና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦችንም ሊያፈናቅል ይችላል፤›› ማለታቸውን ዘፎር ፍሮንት ማግ ዘግቧል፡፡
‹‹በመተባበር እነዚህን ፈተናዎች ማሸነፍ እንደምንችል ግልጽ ነው። ለትብብሩ ዘላቂነትና ዕድገት የተቋሙ የሁሉም አባል አገሮች ባለቤትነት ወሳኝ ነው፤›› ሲሉም አመልክተዋል።
በትብብር ጉዞው ውስጥ ከተከናወኑት ዋና ዋና ክንውኖች አንዱ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ማፅደቁ መሆኑንም ሰብሳቢው ጠቁመዋል። ‹‹ይህ ስምምነት ለናይል ተፋሰስ አገሮች አዲስ ምዕራፍ የሚወክል ሲሆን የጋራ ግቦችን ለማሳካት በጋራ ለመሥራት ያለንን አቅም ያሳድጋል።››
በሥነ በዓሉ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በንግግራቸው የናይል ወንዝ ቋሚ ድርጅትን መመሥረት ላይ አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሠረተ ልማት፣ የመረጃ ልውውጥና የአቅም ግንባታ መርሐ ግብሮችን ለማቀላጠፍ የልማት አጋሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አድርገዋል፡፡
‹‹ለሚያጋጥሙን የውኃና የአየር ንብረት ችግሮች›› የአካዴሚክና የምርምር ተቋማት በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎችን እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
የናይል ተፋሰስ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ለድርቅና ጎርፍ፣ ለአፈር መሸርሸርም ተጋላጭ መሆናቸውን የገለጹት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየሠራች መሆኗን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሯ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከሏን፣ ከነዚህ ውስጥ 11.2 ቢሊዮኑ በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ የተተከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ አገሮች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለመቋቋምና መፍትሔ ለማፈላለግ ተባብሮ መሥራት፣ ልምዶችንም መለዋወጥ ያስፈልጋቸዋል ያሉት የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ ናቸው።
19ኛው የናይል ቀን ከስብሰባ ባሻገር ለማስገንዘቢያ በአዲስ አበባ አውራ ጎዳና የእግር ጉዞ የተደረገ ሲሆን፣ የባህልና የምግብ ምሽት መሰናዶ እንደነበረበትም ተዘግቧል፡፡
በናይል ቀን ዝግጅት የተሳተፉ የተፋሰሱ አገሮች ሚኒስትሮችና ጋዜጠኞች የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ገጹ እንደገለጸው፣ በየካቲት 16 ቀን ጉብኝት የኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ የውኃ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የተፋሰሱ አፈሮች ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል።
የናይል ተፋሰስ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮችና አብሯቸው የመጡ ጋዜጠኞች እንዲሁም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የአገሮቹ አምባሰደሮችና ዲፕሎማቶች ግብፅ ያቀረበችውን የህዳሴውን ግድብ እንዳትጎበኙ ጥሪ፣ ማስጠንቀቂያና ዛቻ ወደ ጎን ትተው የህዳሴውን ግድብ መጎብኘታቸው ተመልክቷል::
አሥራ አንዱ የናይል ተፋሰስ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዑጋንዳ፣ ኤርትራ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው።