

ዘታቦር ትሬዲንግ ማኅበር ለደንበኞች የሚያቀርባቸውን ምርቶች ሲያስተዋወቅ
ማኅበራዊ የአገር ውስጥ ምርቶችን የማስለመድ ተግዳሮት
ቀን: February 26, 2025
ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ውጤት የሆኑ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ሥራ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ከሚፈለገው ደረጃ አልተደረሰም፡፡
በትልልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶችን ጨምሮ፣ በሌሎች ፋብሪካዎች የሚመረቱ ምርቶች ከውጭ አገር ከሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር የሚወዳደር ጥራትና አገልግሎት ቢኖራቸውም፣ በሸማቾች ዘንድ ጥርጣሬን ማጫራቸው አልቀረም፡፡ ሸማቾች ከውጭ የገቡትን መግዛት ይመርጣሉ፡፡
የአገር ውስጥ ምርቶች በተጠቃሚው ዘንድ አመኔታ እንዲኖራቸው በሚል አንዳንድ አምራቾች በዝቅተኛ ዋጋ ለማስተዋወቅ ሲሞክሩ፣ የዕቃውን ጥራት በዋጋው ብቻ በመለካት የአገር ውስጥ አምራቾችን ተስፋ ሲያስቆርጡም ይስተዋላሉ፡፡
የጫማ፣ የአልበሳት፣ የቤት ዕቃዎች፣ የግንባታ ግብዓቶችና ሌሎችም በርካታ ምርቶች በአገር ውስጥ እየተመረቱም ነው፡፡ ከአነስተኛና ጥቃቅን ጀምሮ እስከ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች በመንግሥት ፖሊሲዎችና እንደ ኢትዮጵያ ታምርት ባሉ ንቅናቄዎች የሚታገዙበትና ምርታቸውን ለገበያ የሚያቀርበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን የገበያው ሁኔታ ገና ይቀረዋል፡፡
በዚህም አምራቾች ብቻ ሳይሆኑ ከፋብሪካ ምርቶችን ተረክበው ለሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል ለሚያከፋፍሉ አካላትም ጭምር ፈተና እንደሆነባቸው ይነገራል፡፡
አቶ ሰለሞን አወቀ የዘታቦር ትሬዲንግ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ማኅበራቸው በአገር ውስጥ የሚመረቱ የግንባታና የማስዋቢያ ዕቃዎች በማከፋፈል በግንባታው ዘርፍ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ከውጭ የሚገቡ ምርቶችና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በጥራት ሲወዳደሩ ተመሳሳይ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ ምርቶቹ በአገር ውስጥ ባለሙያዎችና ጥሬ ዕቃዎች ሲመረቱ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረትና ለዜጎች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ ያለው ከፍተኛ ሚና መዘንጋት እንደሌለበት ያክላሉ፡፡
ቤቶች ከተገነቡ በኋላ እንደ ቀለም፣ ጂብሰም፣ ሴራሚክና ሌሎች መሰል ዕቃዎችን ለመግጠም የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛና ከቤቱ መሥሪያ ያልተናነሰ ወጪ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
በግንባታው ዘርፍ እየታዩ ያሉ የግብዓት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ችግሮችን ለመፍታት የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም አንዱ አማራጭ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና የአገር ውስጥ ምርቶችን ተደራሽነት ለማስፋት እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ማኅበራቸው ለቤት ዋጋ ንረት እንደ አንድ ምክንያት የሆነውን የግንባታ ግብዓት አቅርቦትና እጥረቶች ለመፍታት፣ በተለይ በብዛት ከውጭ የሚገባውን የሴራሚክ ምርትን በመተካት ለብዙዎች ጠቀሚታ ይኖረዋል ያሉትን ምርት ለተጠቃሚዎች እያቀረቡ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ማኅበሩ የሚያቀርበው ዕቃ ከውጭ ከሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ ዋጋ እንዳለው የሚያስረዱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ብዙ ጊዜ ዋጋቸው የማይቀመሰው የተሻለ ጥራት ስላላቸው ሳይሆን ብዙ ሰዎች ከውጭ የሚገባ ዕቃን ተመራጭ ስለሚያደርጉ ነው ብለዋል፡፡
ማኅበራቸው ታቦር ትሬድንግ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ዕቃዎችን የትራንስፖርት አገልግሎት ጭምር በመስጠት ለግለሰቦች፣ ለሆቴሎች፣ ለአፓርትመንትና ለሌሎች ተጠቃሚዎች በማከፋፈል እየሠራ እንደሚገኝ፣ 95 በመቶ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም የሚመረተውንና ‹‹ኤስፒሲ›› የተሰኘውን ሴራሚክ ለተለያዩ ተቋማት እያከፋፈሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አገር ውስጥ የተመረቱ የኮንስትራክሽን ጥሬ ዕቃዎችን ከአምራቾች በመረከብ ሲያከፋፍሉ መቆየታቸውን፣ በተለይ ለፊኒሺንግ ሥራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ያሏቸውንና ሴራሚክን ሙሉ በሙሉ ተክተው ለወለል ምንጣፍ፣ ለመፀዳጃ ቤትና ለሌሎች ማስዋቢያዎች የሚውሉ ዕቃዎችን በስፋት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መጀመሩን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡
ኤስፒሲ ከወለል ምንጣፍነት ባሻገር ለጣሪያና ግድግዳ ለመታጠቢያ ቤትና ለመፀዳጃ ቤት ምንጣፍ እንደሚያገለግል ያስረዱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ሥሪቱ የድንጋይና የፕላስቲክ ውህድ በመሆኑ ውኃ እንዳያስገባና እንዳያዳልጥ እንደሚያደርገው ያክላሉ፡፡
ኤስፒሲ 90 በመቶ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃን በመጠቀም የሚመረት ሲሆን፣ ለአገጣጠም ቀላል ከመሆኑም ባሻገር፣ ተጠቃሚዎች ቤታቸው ካስገጠሙ በኋላ ቤት መቀየር ቢፈልጉ እንኳን ነቃቅሎ በመውሰድ በድጋሜ መጠቀም ይቻላል ብለዋል፡፡
አዳዲስ ምርቶችን አምርቶ ወደ ገበያ ሲያቀርቡ እንደ ችግር የሚነሳው የባለሙያዎች እጥረት ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ባለሙያዎችን ማሠልጠኑን ያስረዱት አቶ ሰለሞን፣ በዚህም ከ50 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከዋስትና ጀምሮ የአገጣጠምና ሌሎች ሙያዊ ድጋፎችን ለማድረግ አመቺ እንደሚሆኑ የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ከተጠቃሚዎች የሚመጡ አስተያየቶችን እንደ ግብዓት በመጠቀም የጎደለውን ለመሙላት ጥሩ አጋጣሚን እንደሚፈጥርም ያክላሉ፡፡
የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም ለተጠቃሚውና ለአገር ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳለውና ሁሉም ሰው ለአገሩ ምርት ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ጥራቱም ቢሆን ከውጭ ከሚገባው ምርት ጋር ሲነፃፀር በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያስረዱት አቶ ሰለሞን፣ ነገር ግን ሁሉም ሰውየ አገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀምና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ተገልጋዮች ስለሚጠቀሙት ምርት የሚሰጡትን አስተያየት በማሰባሰብ የሚያነሱትን ቅሬታና ሌሎች ቢስተካከሉ የሚሉትን ሐሳብ በመቀበል ለአምራቾች እንዲያስተካክሉ እንደሚጠይቁና አምራቾችም አስተያየቶችን ተቀብለው በየጊዜው ምርታቸውን እንደሚያስተካክሉ ተናግረዋል፡፡