

February 26, 2025
ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ በብራንድ ስሙ ‹‹ማማ ወተት›› ካለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ወዲህ በተሻሻሉ የላም ዝርያዎች ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶች እያቀረበ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ አሁን በቀን እስከ 65 ሺሕ ሊትር ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶች እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ሌሎችም የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ለመሰማራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ስለ ድርጅቱ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪው ላይ ስለሚታዩ ችግሮች፣ ስለምግብ ጥራትና ደኅንነት እንዲሀም በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ይመርን የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ አመሠራረትን ቢገልጹልን?
አቶ ሙሉጌታ፡- አግሮ ኢንዱስትሪው በ1986 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡ ሲመሠረት ስያሜው ‹‹ሰበታ ፋርም›› ነበር፡፡ ላሞችና የተለያዩ ዕርባታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነበር፡፡ ከ1996 ዓ.ም. ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ወደሚል መጠሪያ ራሱን ቀይሮ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ በ180 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሥራ የጀመረው ድርጅቱ፣ አሁን ላይ ካፒታሉን ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ ላለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት በወተትና በወተት ተዋጽኦ ምርቱ ላይ የቆየው ድርጅቱ ‹‹ማማ ወተት›› በሚል ብራንድ ስም በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትን አትርፏል፡፡
ሪፖርተር፡- የወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን የማቀነባበር ሥራችሁ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ድርጅቱ አሁን ላይ በቀን እስከ 65 ሺሕ ሊትር ወተትና የወተት ተዋጽኦ እያቀነባበረ ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ የእኛ ኢንዱስትሪ የማምረት አቅሙ በቀን እስከ 150 ሺሕ ሊትር ቢሆንም፣ ከግብዓት እጥረት ጋር ተያይዞ እያመረትን የምንገኘው ከላይ የተጠቀሰውን ቁጥር ብቻ ነው፡፡ ምርቶቻችንም በመላ አገሪቱ ተደራሽ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ከወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶቹ በተጨማሪ ሌሎች የተሰማራባቸው ዘርፎች ይኖሩ ይሆና?
አቶ ሙሉጌታ፡- አግሮ ኢንዱስትሪው ከወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶቹ ውጪ መኖ ወደማቀነባበር ሥራ በቅርቡ ገብቷል፡፡ ጥራት ያለው ወተት ለማምረት ከብቶች የሚመገቡት በቂ መኖ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህን ደግሞ እንደፈለግነው ከአርሶ አደሩ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለሆነም በቀን አስከ አራት ሺሕ አምስት መቶ ኩንታል መኖ የሚያቀነባብር ፋብሪካ አቋቁመናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ በምግብና በመጠጦች፣ በታሸገ ውኃና ሌሎችንም አራት አዲስ ምርቶች ይዘን ወደ ገበያው ለመቀላቀል እየተሠራ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ለአካባቢው ማኅበረሰብ የምታደርጉት ድጋፍ ምንድነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- ድርጅቱ ሰበታ ላይ እንደመገኘቱ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን ያቀርባል፡፡ 95 በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ማኅበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ ሠርተናል፡፡ በድርጅቱ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙና የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ማማ ወተት የዛሬ ትውልድ የነገ አገር ተረካቢ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለሆነም ዕውቀትና ትምህርት ላይ ይሠራል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባት ለመንግሥት አስረክቧል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ድርጅቱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ያበረከታቸው አስተዋጽኦዎች በርካታ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የድርጅቱ የምርት አሰባሰብ ሒደት ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ የራሱ የሆኑ ላሞች አሉት፡፡ እነዚህን ላሞች የሚጠቀመው ዝርያ በማሻሻል ነው፡፡ እነዚህም የተሻሻሉ ዝርያዎች በቀን ከ15 እስከ 20 ሊትር ወተት መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡ በዋጋ ደረጃ እነዚህ ላሞች ገበያ ላይ ከሦስት እስከ አራት መቶ ሺሕ አካባቢ ይደርሳሉ፡፡ እኛ የምናደርገው ለገበሬው የተሻሻሉ ዝርያዎችን መስጠት ነው፡፡ ሌላው ድርጅቱ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን ለብቻው ከማምረት ይልቅ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ከተቋሙ ጋር እንዲተሳሰሩ በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችና ከ15 በላይ በተደራጁ ማኅበራት አማካይነት ወተት የመሰብሰቡን ሥራ እንሠራለን፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ማቀዝቀዣ የገጠምን በመሆኑ፣ ጥራቱ እየተረጋገጠ ወደዚያ ይገባል፡፡ የእኛ መኪኖች ደግሞ ከመስክ የተሰበሰበውን ወደ ድርጅቱ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ይህም ለገበሬው የፈጠርነው ትልቅ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች ላይ የወተት ምርቱን እየሰበሰበ ቢገኝም፣ ከምርት ጥራት ጋር በተያያዘ የምንፈልገውን ዓይነት ወተት በብዛት የማናገኝ ከመሆኑ አንጻር በቀን ለማምረት ካቀድነው በታች እያመረትን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው? እናንተስ እየገጠማችሁ ያሉት ችግሮች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ሙሉጌታ፡- ከአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤትን ማግኘት ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ ትርፉንና ውጤቱን ወዲያው የምታገኘው አይደለም፡፡ የዘርፉና የድርጅቱም ዋና ችግር የምንለው የመኖ አቅርቦት እጥረትን ነው፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ መኖ የሚቀርብበት ሥርዓት የለም፡፡ ይህ ትልቅ ፈተና ሆኖብን ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎች ማግኘት ሌላው ችግር ነው፡፡ የመኖ አቅርቦትና ዝርያ ማስፋፋት ላይ መሥራት የሚቻል ከሆነ ዘርፉ ውጤታማ መሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ አግኝታችኋል፡፡ ምንስ በመሥራታችሁ የተገኘ ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- ድርጅታችን ለምግብ ደኅንነትና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታችን ዓለም አቀፍ የምግብ ደኅንነት ሥርዓት ISO 22000፣ 2018 እና ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO 9001፣ 2015 የብቃት ማረጋገጫ የመለኪያ ወረቀት ሊበረከትለት ችሏል፡፡ የምንመገበው ማናቸውም ምግብ ከየትኛውም ኬሚካል፣ ባዮሎጂካልና ፊዚካል ብክለት ነፃ ሆኖ ለሰው ልጅ ጥቅም መዋል ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ወተትም ከምግባችን አንዱ በመሆኑ ከላሚቷ እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ የምናደርገው የጥራትና የደኅንነት ጥበቃ ሥራ ውጤታማ አድርጎን ዕውቅናና ሽልማት አሰጥቶናል፡፡