
February 26, 2025
በትግራይ ክልል የተሰጡ ብድሮች ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየተባባሰ በመምጣቱ የክልሉ ንግድ ማኅበረሰብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡበት ጥያቄ ማቅረባቸው ተገለጸ፡፡
በትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል በተቋቋመው አዲስ ኮሚቴ አስቸኳይ ምላሽ ያሻቸዋል ያላቸውን ሰባት ዋና ዋና ጉዳዮችን ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጽሑፍ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት በአካባቢው በነበረው ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ ባንኮች ያገኙትን ብድር መክፈል ባለመቻላቸው የተነሳ በዋናው ብድር ላይ ወለድና ቅጣት ታክሎበት ያለባቸው አጠቃላይ የዕዳ መጠን ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ታውቋል።
በትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል የተቋቋመው ኮሚቴ አስቸኳይ ምላሽ ያሻቸዋል ያላቸውን ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማቅረቡ በፊት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት ተቋማት አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከአንድ ጥያቄ በቀር ሌሎቹ ምላሽ እንዳላገኙ ታውቋል። በመሆኑም ለጉዳዩ ዕልባት ለማግኘት ጥያቄዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲቀርቡ መደረጉን የኮሚቴው አስተባባሪና የኢኮኖሚ ባለሙያው አታክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል።
አስተባባሪው እንደገለጹት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ጥያቄዎች አፈጣኝ መልስ የማያገኙ ከሆነ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፡፡
እነዚህ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲቀርቡ የተደረገውም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ፅዮን ገብረ መድን (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ ኃላፊዎች ጉዳዩን እንዲያውቁት ከተደረገ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ብዙ ነገሮች ይለወጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ባለመሆኑ አሁን በክልሉ የሚታዩ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየተባባሱ መሆናቸውን የገለጹት አትክልቲ (ዶ/ር)፣ በተለይ ከባንክ ብድር ጋር የተያያዘው ችግር ዘላቂ የሚሆን ባለማግኘቱ መፍትሔ ችግሮቹን እንዳወሳሰባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ካላገኙ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከመንግሥት ተቋማት ጋር በተደረገ ንግግር ኮሚቴው ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል እስካሁን ምላሽ የሰጠው ብሔራዊ ባንክ ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት አስተባባሪው፣ በዚህም ባንኮች በክልሉ ለሚገኙ ተበዳሪዎች የሰጡት ብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙ መደረጉን፣ ሌሎች ጥያቄዎች ግን እስካሁን መልስ እንዳላገኙ አስረድተዋል።
ባንኮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ለክልሉ ተበዳሪዎች የሰጡት የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ ወይም የዕፎይታ ጊዜ የፕሪቶሪያው የሰላም ውል ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ ለ18 ወራት ብቻ የተፈቀደ መሆኑን ያስታወሱት አታክልቲ (ዶ/ር)፣ ይህ የዕፎይታ ጊዜም ከሁለት በፊት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የዕፎይታ ጊዜው መጠናቀቁን ተከትሎም ባንኮች የበርካታ ተበዳሪዎችን የብድር መያዣ ንብረቶች ለመሸጥ ጨረታ ማውጣት በመጀመራቸው ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩን፣ በዚህም የተነሳ በድጋሚ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቀርቦ የብድር መክፍያ ጊዜው ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም በመደረጉ ለጊዜውም ቢሆን ዕፎይታ መገኘቱን አታክልቲ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በዚህ ረገድ የሚወሰደው ዕርምጃ የሚያስመሰግን ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ግን አታክልቲ (ዶ/ር) ያምናሉ፡፡
ጦርነቱ በክልሉ ያደረሰውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች አስመልክቶ የተደረጉ ጥናቶች አብዛኞቹ የቢዝነስ ተቋማት እስካሁን ድረስ ቢዝነሳቸውን መልሰው ለማስቀጠል እንዳልቻሉ ያመለክታሉ።
በተለይ በክልሉ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከባንኮች የወሰዱትን ብድር ለመመለስ አለመቻላቸውና ተጨማሪ ብድር አግኝተው ሥራቸውን መቀጠል አለመቻላቸው የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ እየጎዳው ነው፡፡
በተለይ ተበዳሪዎች ብድር እንዲራዘምላቸው ሲደረግ አብሮት መቅረብ የነበረበት ብድር ባለመቅረቡ ብድራቸውን ለመክፈል ባለመቻላቸው ከአምስት ዓመት በፊት የነበረባቸው 32 ቢሊዮን ብር የብድር መጠን ወለዱ እየጨመረ በመምጣት በአሁኑ ወቅት ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ መቻሉን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ይህንን ብድር አሁን ባለው ሁኔታ ወለዱንና ቅጣቱን አይደለም ዋናውን ብድር ለመመለስ የሚያስችል ምንም ሁኔታ ባለመኖሩ ጉዳቱ ለተበዳሪዎቹ ለባንኮችና ለሁሉም በመሆኑ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ የመጀመርያው የብድር ማራዘሚያ ገደብ ጊዜ እንዳለቀ ባንኮች ወደ ጨረታ ሲገቡ የተፈጠረው ችግር በተለይ መኖሪያ ቤቶችና የሕንፃ ዋጋ በአንዴ እንዲወርድ ያደረገ ሲሆን ማን የማንን ንብረት ይገዛል በሚል በኅብረተሰቡ ውስጥ ያልተገባ ስሜት ፈጥሮ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ይህ ሁኔታም የሥነ ልቦና ችግር ፈጥሮ እንደነበር ተብራርቷል፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከፋይናንስ ዘርፍ ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን የማይክሮ ኢኮኖሚ ችግር እየሆነ መምጣቱን አትክልቲ ገልጸዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ጥያቄዎችም እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር በተመለከተ አታክልቲ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ አብዛኞቹ ተበዳሪዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ማሽኖችና ሌሎች ንብረቶች በጦርነቱ የወደሙ በመሆናቸው ያለባቸውን ብድር ለመክፈል የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ጠቁመዋል።
‹‹በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽንና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ያሉ ቢዝነሶችም መሣሪያዎቻቸውና ተሽከርካሪዎቻቸው ተዘርፈዋል ወይም ወድመዋል፡፡ ስለዚህ ይህ በሌለበት ሁኔታ እነዚህ ተበዳሪዎች በምን አቅማቸው ብድሩን ሊከፍሉ ይችላሉ? በተለይ ብዙዎቹ ባንኮች ወለዱን ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ቅጣት ሁሉ አክለው ነው የመጡት ስለዚህ የብድሩ ሁኔታ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ተበዳሪዎቹ የሚከፍሉት ነገር አይኖራቸውም፤›› ብለዋል፡፡
ከክልሉ የብድር ቀውስ ጋር በተያያዘ እያንዳንዱን የብድር ዓይነት እንደየሁኔታቸው በመፈተሽ በልዩ ሁኔታ መስተናገድ አለባቸው የሚሉት አታክልቲ፣ ሙሉ በሙሉ ንብረት የወደመባቸውን ለብቻ፣ በከፊል የተጎዱትን ለብቻ ሌሎችንም እንዲሁ በማየት በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ ማድረግ ካልተቻለ ችግሩን እንደሚያባብሰው ገልጸዋል፡፡
ከብድር ሁኔታው ጋር የተያያዘ ሌላው ችግር የሆነው ብዛት ያላቸው ተፈናቃይ ተበደሪዎች ወደ ነበሩበት ባለመመለሳቸው ንብረታቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ማወቅ እንዳልተቻለና ይህም በራሱ ትልቅ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች አሁን በተረጂነት የተቀመጡ በመሆኑ እንዴት ብድሩን ለመመለስም ሆነ ድጋፍ አግኝተው ቢዝነሳቸውን ለመቀጠል ዕድል የሌላቸው በመሆኑ ይህ ችግር በልዩ ሁኔታ ታይቶ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ተበዳሪዎቹ ምንም ማድረግ በማይችሉበት ሁኔታ ያለባቸው ብድር ብቻ ማስላት የዕዳ መጠናቸውን ከማሳበጥ ያለፈ ብድሩን ከመክፈል አኳያ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም እንዲህ ያሉ ጉዳዮች የሚመለከቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሌላው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ምንም ዓይነት የማቋቋሚያ ሥራ አለመሠራቱ ችግሮችን እያባባሰ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተጎዱ ተቋማት መልሰው የሚቋቋሙበት ሥራ ባለመሠራቱ እንዲህ ያሉ ተበዳሪዎች ብድር መልሱ ቢባሉ ሊመልሱ ስለማይችሉ ይህም መልስ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኖ መቅረቡን ጠቁመዋል።
የብድር ማራዘሚያ ሲሰጥ የፋይናንስ ዘርፉ ተጨማሪ ፋይናንስ አብሮ ማቅረብ የነበረበት ቢሆንም ይህ ባለመሆኑ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ በመሆኑም ባንኮች ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ ተጨማሪ ፋይናንስ ማቅረብ እንዲችሉ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በሁለት ዓመት ውስጥ ለክልሉ ከባንኮች የተሰጠው የብድር መጠን 6.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፣ ይህም በፋይናንስ አቅርቦት ዙሪያ ያለውን ችግር ያሳያል። የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትም ሌላው ተግዳሮት ነው፣ ይህም ጉዳይ መልስ ይፈልጋል፤›› አትክልቲ አስረድተዋል።
በክልሉ የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ በመሆናቸው የአገልግሎት ዘርፉ መዳከም ሌላው እንደ ትልቅ ችግር ሆኖ የተለየው ከክልሉ ከነበረው ቁጠባ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ሁኔታ ነው፡፡
ይህም በጦርነቱ ወቅት በክልሉ ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ የነበረ ቁጠባ ሳይንቀሳቀስ መቆየቱና እንዲንቀሳቀስ ከተፈቀደ በኋላ ደግሞ የብር መዳከም የፈጠረው ተፅዕኖ በራሱ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን ማባባሱን ገልጸዋል፡፡
ከታክስ ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለውም ችግር ትልቅ ሥጋት ሆኖ እየመጣ በመሆኑ ይህ ጉዳይ ተፈትሾ መልስ ሊያገኝ ይገባል በሚልም የቀረበ ጥያቄ መኖሩ ታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም ሊስተካከል ባለመቻሉ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ አስፈልጓል ተብሏል፡፡ በክልሉ ያሉ ተበዳሪዎች አለባቸው የሚባለውን ታክስ ለመክፈልም ቢሆን ከባንኮች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ እንዲሁም ሠርተው ለመክፈል የሚያስችላቸው ሁኔታ ያለመኖር ጉዳዩን አወሳስቦታል ብለዋል፡፡
ይህ ጉዳይ የተወሰነ ፋይናንስ አግኝተው ሥራቸውን ለማስቀጠል ይችሉ የነበሩ ቢዝነሶችን እንቅስቃሴ ገድቧል፡፡ ከዚህ ሌላ አንዳንድ ባንኮች የዕፎይታ ጊዜ ሲሰጡ ቅጣት አስቀርተው እያሰሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ቅጣቱን ጭምር በመጨመር ዕዳውን ከፍ እያደረጉ መሄዳቸው በራሱ ችግር እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በክልሉ በሒደት ላይ የነበሩ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የተስተጓጎሉ በመሆኑ የብድር ወለዳቸው እንዲነሳ ቅጣት ተብሎ እየቀረበ ያለውንም ጥያቄ ሊመልስ ላይችል ይህ ሁሉ እንዲነሳላቸው ጥያቄ እንደቀረበ ተገልጿል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያያዥነት አላቸው የሚባሉ ጥያቄዎች ስለመቅረባቸው የገለጹት አቶ አታክልቲ እንዲህ ያሉ ችግሮች መፈጠራቸው በክልሉ ውስጥ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በርካታ ወጣቶች ያለ ሥራ ተቀምጠው እንዲቆዩ ከማድረጉም በላይ ለማኅበራዊ ቀውሶች መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ እየዳረገ ነው፡፡
ወደ ክልሉ የሚገባው በአፋር ክልል ብቻ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የምርት የአቅርቦት ዋጋ ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖም ሊታይ የሚገባ ስለሆነ ጉዳዩ ከፋይናንስ ጋር የተያያዘ ብቻ ባለመሆኑ በፖሊሲ ደረጃ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡ ለችግሩ የመጨረሻው የመፍትሔ የሚገኘው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋግሩናል ብለው እየጠበቁ መሆኑን አታክልቲ ገልጸዋል፡፡