ዜና ሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክር ቤትን ለመቀላቀል ወሰነ

ልዋም አታክልቲ

ቀን: February 26, 2025

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ‹‹ጊዜያዊ አማካሪ ምክር ቤት›› በሚል አቋቁሞት የነበረውን አሻሽሎ የመወሰን ሥልጣን እንዲኖረው ማድረጉን ተከትሎ፣ በምክር ቤቱ እንደማይሳተፍ ከአንድ ወር በፊት አስታውቆ የነበረው ክልላዊው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ፓርቲ፣ ሐሳቡን ቀይሮ በምክር ቤቱ ለመሳተፍ መወሰኑን አስታወቀ።

ሳወት ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አሉላ ኃይሉ፣ ‹‹የጊዜያዊ ምክር ቤቱን ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መንገድ ለመታገልና ምክር ቤቱን እንደ መታገያ መድረክ ለመጠቀም ለመሳተፍ ወስኗል፤›› ብለዋል።

በጊዜያዊ ምክር ቤቱ ውስጥ መካተት ያለባቸው ጉዳዮችን በሚመለከት በርካታ አስተያየቶችን ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት የፓርቲው የሕገ መንግሥትና የሕግ ክፍል ኃላፊ አቶ የማነ ካሳ በበኩላቸው፣ ፓርቲው በዋነኛነት እንዲካተቱ አንስቷቸው የነበሩ ጉዳዮች በምክር ቤቱ መቋቋሚያ ደንብ ውስጥ መካተታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሳልሳይ ወያነ ፓርቲ በጥር ወር አጋማሽ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በተቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት አባል መሆን ያልፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዳም፣ ‹‹የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ቀደም ሲል ምክር ቤቱን ለማቋቋም የተደረሰበትን ስምምነት የሚፃረር ደንብ በማፅደቁ ነው፤›› ማለቱ ይታወሳል፡፡

ፓርቲው በወቅቱ ምክር ቤቱ ‹‹የትግራይ ጊዜያዊ ምክር ቤት›› ተብሎ እንዲሰየም ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ጠቅሶ፣ አዲሱ ደንብ ግን ‹‹የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት›› በማለት ስያሜውን ቀይሮታል የሚል ተቃውሞ ማሰማቱም ይታወቃል።

በተጨማሪም አስቀድሞ ተደርጓል በተባለው ስምምነት መሠረት ‹‹በምክር ቤቱ ውስጥ የሠራዊት አባላት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ እንዲሁም የተፈናቃዮች ተወካዮች እኩል ቁጥር ያለው አባል አዋጥተው እንዲሳተፉ መደረግ ቢኖርበትም፣ አሁን ግን ምክር ቤቱ ከፍተኛው መቀመጫ በገዥው መደብ እንዲያዝ ወስኗል፤›› ብሎ ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈም አዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ እንዲሁም የትግራይ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት የሚወከሉ ሰዎች እንዲካተቱ ይደረጋል መባሉ፣ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚፈልጋቸውን ሰዎች እንደ ልቡ እያካተተ እንዲፈነጭ የሚያደርግ ነው፡፡ ምክር ቤቱም ለብሔራዊ ጥቅም ያልቆመ ከማደንዘዣ የማይተናነስ ተቋም ነው፤›› በማለትም ወቀሳ አቅርቦ ነበር፡፡

ሳወት የተቃውሞውን መነሻ በዝርዝር ካሳወቀ በኋላ ከሁለት ሳምንታት በፊት የመጀመሪያ አስቸኳይ ጉባዔውን በመቀሌ ከተማ ያካሄደው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት፣ የተቋቋመበትን ደንብ ቁጥር 10/2016 አሻሽሎ አጽድቋል፡፡

በጉባዔውም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት ይልቅ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት መባል እንዳለበት በአባላቱ ተጠይቋል፡፡ በዚህም ምክር ቤቱ የማቋቋሚያ ደንቡ ላይ የቀረበውን ማሻሻያ በ53 ድጋፍ፣ በአንድ ተቃውሞና በሁለት ድምፀ ተዓቅቦ አጽድቋል፡፡

ተሻሽሎ የፀደቀው አዲሱ ደንብ የጊዜያዊ ምክር ቤቱ ለፕሬዚዳንቱ የነበረውን ተጠሪነት ‹‹ለሕግ፣ ለህሊና፣ እንዲሁም ለሕዝብ›› ተጠሪ እንደሆነ በሚገልጽ ድንጋጌ ተክቷል፡፡

የምክር ቤቱ ዓላማዎች ተብለው ከተቀመጡት ጉዳዮች መካከል የሕዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ ፍትሐዊ ምርጫን ማካሄድና የትግራይ ፖለቲካ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የመንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመለያየት መርህ በተሟላ መንገድ እንዲረጋገጥ መሥራት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ማድረግና የትግራይ ሕዝብ ህልውና፣ ደኅንነት፣ መብትና ጥቅምን ማስከበር ነው።

በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ  ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ከተወጣ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግና ዴሞክራሲን ለማስፈን ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የሕወሓት ክንፍ የምክር ቤቱን ምሥረታ እንደሚቃወም መግለጹን መዘገባችን አይዘነጋም።