

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
ዜና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች የኮንጎ ሰላም አመቻች ሆነው ተሰየሙ
ቀን: February 26, 2025
በአዲስ ጌታቸው
ሁለት ክልላዊ የትብብር ተቋማት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣውን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የእርስ በርስ ጦርነት በአስቸኳይ ይገታ ዘንድ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎችን ለሰላም አመቻቺነት መሰየሙን፣ ሰኞ የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በወጣ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የዕርቅ ሒደት አመቻች በመባል ተሰይመዋል፡፡
አዲሱ የሰላም ጥረት በቀደሙ ዓመታት ተጀምረው ያልሰመሩ የሉዋንዳ (አንጎላ) እና የናይሮቢ ኬንያ የሰላም ጥረቶች ውጤት ባለማምጣታቸው፣ በአንድ የሰላም ድርድር ሒደት ሥር ተጣምረው እንዲከናወኑ በማስፈለጉ እንደሆነ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
በዚህ መሠረት ሦስቱ መሪዎች በደቡባዊ አፍሪካ የልማት ኮሚሽን (SADC) እና በምሥራቃዊ አፍሪካ ማኅበረሰብ (EAC) የሚመራውን አዲስ የሰላም ሒደት በማመቻቸት፣ እየተባባሰ የመጣው ቀውስ እንዲገታ ይሠራሉ ተብሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት በሩዋንዳ እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የኤም 23 ታጣቂዎች ጎማንና ባኪቩ ከተሞችን ጨምሮ፣ የሰሜንና ደቡብ ኪቩ አውራጃዎች ዋና ዋና ከተሞችን ሲቆጣጠሩ ግጭቱ እየሰፋና እየተወሳሰበ መጥቷል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የናይሮቢውን የሰላም ድርድር ሲመራ የቆየ ሲሆን፣ የሉዋንዳው የዕርቅ ሒደት ደግሞ በአንጎላው ፕሬዚዳንት ያዎ ሎሬንሆ ሐሳብ አመንጪነት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተመሠረተ ነበር፡፡
ሚሊዮኖችን ከቀያቸው እያፈናቀለ የሚገኘውን ግጭት የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 17 ከመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው፣ በእጅጉ ሲያወግዝ፣ የሩዋንዳን መንግሥት የኮንጎን አማፂያን ከመርዳት እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡
በማዕድናት፣ በደንና በውኃ ሀብቶቿ እጅግ በምትታወቀው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተስፋፋ የመጣውን ጦርነት በመሸሽ፣ ሴቶችና ሕፃናትን ጭምሮ 400,000 ዜጎች ወደ ቡሩንዲ የተሰደዱት በዚሁ አንድ ወር ውስጥ ነው፡፡
ባለፈው ወር ብቻ 500,000 ሰዎች ከሰሜናዊ ኪቩ አውራጃ ቀዬአቸውን ጥለው መሰደዳቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ባለፈው ዓርብ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ካውንስል የሁለቱ የክልላዊ ተቋማት አባል አገሮች መሪዎች ሽምግልና ለመመሥረት የደረሱትን አቋም በማፅደቅ፣ ተፋላሚ ወገኖች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ፣ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ቢማፀኑም ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ካውንስሉ ባወጣው መግለጫ፣ የመካከለኛ አፍሪካዋ አገር ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱና የማኅበረሰብ ውይይቶች ይደረጉ ዘንድ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እንዲተባበሩ አሳስቧል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1996 ጀምሮ በምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተካሄደ በሚገኘው የትጥቅ ግጭት ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል፡፡
የመጀመሪያው የኮንጎ የእርስ በርስ ጦርነት የተካሄደው እ.ኤ.አ. ከ1996 እስከ 1997 ሲሆን፣ የ1994 የሩዋንዳ ጄኖሳይድን ተከትሎ ነበር፡፡ በፍጅቱና ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የሁቱ ጎሳ አባላት ከሩዋንዳ ድንበር አቋርጠው ወደ ምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንደገቡ የዳራ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር በሰሜንና ደቡብ ኪቩ አውራጃ ከሰፈሩ የሁቲ ስደተኞች ውስጥ ጥቂት የሚባሉ አክራሪዎች ነፍጥ በማንሳት የትጥቅ ትግል የጀመሩት፡፡ በፍጅቱ በእጅጉ ተጠቂ የነበሩት ቱትሲዎች ደግሞ እነዚህን የሚሊሻ ቡድኖች ለማጥፋት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አሁን ዴሞክራቲክ ኮንጎን እያመሰ ላለው የእርስ በርስ ጦርነትም እርሾ የሆነው ያ አጋጣሚ እንደነበር በሰፊው ይነገራል፡፡
አሁን እንደ አዲስ በተጀመረው አዲስ የሰላም ጥረት አመቻች ተደርገው ከተሰየሙ የቀድሞ መሪዎች መካከል ኦሉሴጉን ኦባሳንጆና ኡሁሩ ኬንያታ፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የተደረገውንና በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረገውን የፕሪቶሪያ የሰላም ድርድርና አፈጻጸም በመምራት፣ የዕርቅ ተሞክሮ ያካበቱ ናቸው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከስድስት ዓመታት አመራር በኋላ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡