

February 26, 2025
በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ፣ የፀጥታና የሰብዓዊ ቀውስ ያስቀራል የተባለ ስምምነት መደረጉን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) እሑድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ስምምነቱን ያደረጉት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ የማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች መሆናቸው በኦፌኮ መግለጫ ተመላክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ኢሊሌ ሆቴል ለአራት ቀናት ተካሂዷል የተባለው ኮንፈረንስ፣ የኦሮሞን የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አንድ ኃይል ለማምጣት፣ ለዘላቂ ሰላም መስመር ለማበጀት፣ ለፍትሕና የኦሮሞ ሕዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚወስኑበት ዕድል ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ኦነግና ኦፌኮ ሁሉንም መንገዶች በመጠቀም የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነትና ሰላም ለማስጠበቅ መስማማታቸውን ያስታወቀው የኦፌኮ መግለጫ፣ ሁለቱ ፓርቲዎች ሁሉን አቀፍ በኦሮሚያ የሽግግር መንግሥት ማቋቋምና አዲስ አበባን ለኦሮሚያ ክልል ተጠሪ እንድትሆን የማድረግ ትልም መያዙን አካቷል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት እያደረጉ እንደሆነ መረጃው ሲወጣ፣ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማቅረብና አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ያሳየበት ክስተት እንደሆነና ከዚያም አልፎ የፌዴራል መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም እየተካረረ ከመጣው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት፣ ከሕወሓት ወቅታዊ ያልተረጋጋ የፖለቲካ ቁመናና ከፋኖ ጋር እያደረገ ካለው ውጊያ ጋር ተጨማሪ አቅም ለመያዝ ነው በሚል አስተያየቶች ሲደመጡ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ኮንፈረንሱ ተጠቃሎ መግለጫ ሲወጣ ብልፅግና ፓርቲ የሌለበት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይ የፌዴራል መንግሥትን በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰውና ኦነግ ሸኔ ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለማቀራረብ እንደሚሠራ ግን ተጠቅሷል፡፡
የፓርቲዎቹ ትብብር የሽግግር መንግሥት በማቋቋም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን በማስፋት ቋሚ የሆነ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በምርጫ እስከመጣ ድረስ እንሠራለን ብሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በአመዛኙ ስማቸው ሲነሳ የሚደመጠው ኦነግና ኦፌኮ ከዓመታት በፊት ጥምረት ለመፍጠር ውይይት መጀመራቸውን አስታውቀው የነበረ ቢሆንም፣ እሳከሁን ምንም የተለየ እንቅስቃሴ አላሳዩም ነበር፡፡
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ አንድነትና ዕድገት ከሚታገል ማንኛውም ድርጅት ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነን በማለት አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ የተባበሩት ኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሚያ ነፃነት አንድነት ግንባርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በ2011 ዓ.ም. መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
በአሁኑ ወቅት እነዚህ ፓርቲዎች ወቅታዊ ቁመናቸው እምብዛም የተቀዛቀዘ ሲሆን፣ ይልቁንም በኦነግ አመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መካሰሳቸው ይታወሳል፡፡ አንደኛው ሕጋዊና በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያለውና ሌላኛውን ሕገወጥ እያለ የሚጠራ ሲሆን፣ ሌላኛው ክንፍ ደግሞ ጉዳዬ በፍርድ ቤት ሒደት ላይ ሆኖ ያላለቀልኝ እንጂ ሕገወጥ አይደለሁም በማለት እስካሁን በፍርድ ቤት ክርክር ላይ መሆኑን በመጥቀስ ሲናገር ይደመጣል፡፡
አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልል ዋና መቀመጫ መሆኗን በማረጋገጥ ለኦሮሚያ ክልል ተጠሪ እንድትሆን፣ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መስመሮችን በመጠቀም ለመሥራት ተነስተዋል፡፡
በተጨማሪም የገዳ ሥርዓት የኦሮሚያ ፖለቲካ መሠረት እንዲሆን የማድረግ፣ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ አናሳ ብሔሮች መብታቸው ተጠብቆ ያለ ፍርኃት እንዲኖሩና እንዲሠሩ፣ ኦሮሚያ ክልል በፍትሕ ሥርዓቱ፣ በአገር መከላከያና በፖሊስ፣ እንዲሁም በሌሎች የፌዴራል ተቋማት ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚሠሩ ኦፌኮ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያነሱት ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል ያሉ ሲሆን፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ውይይት እንፈልጋለን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ማንኛውንም ዓይነት የትግል ስትራቴጂ እየተከተሉ ላሉ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ ትግል ላሉት ትልም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህን በተመለከተ ሪፖርተር ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቃቸው የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ለጊዜው መግባባት ከምንችላቸው አካላት ጋር የጀመርነው ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ለወደፊት ደግሞ ልዩነት ካላቸውና ይህ ነገር ይስማማናል ከሚሉት ጋር አብረን ለመቀናጀትና ለመሥራት በማሰብ፣ በውጊያ ላይ ካሉት ደግሞ ሐሳቦቻችንን በመግለጽና በማሳመን ሁሉን ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በማቀድ የተጀመረ ሒደት ነው፤›› ሲሉ አቶ ሙላቱ አስረድተዋል፡፡
ሒደቱ በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡ መግባትና መውጣት ባለመቻሉና፣ የክልሉ ሕዝብ ነፃነት ያጣበት ወሳኝ የህልውና ጥያቄ ላይ በመደረሱ፣ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል በማለት ከተመረጡ የሃይማኖት አባቶችና ኅብረተሰቡን ከወከሉ ጋር ኮንፈረንስ በማካሄድ ስምምነት የተደረሰበት እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
‹‹ሁለቱ በጦር የሚፋለሙ አካላት በከፍተኛ ሁኔታ ጎድተውናል፡፡ መንግሥት እኔ በሕዝብ የተመረጥኩኝ አካል ነኝ አንተ ምን ያገባሃል? እኔ ለጥ ሰጥ አድርጌ በጠመንጃ አንተን መግዛት አለብኝ በሚል ፉክክር ላይ ነው፡፡ እነዚያኞቹ ተዋጊዎች ደግሞ መንግሥት መብታችንን ለማስከበር ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ባለመዘጋጀቱ እሱ በሚያውቀው ቋንቋ ለመነጋገር እየተፋለምነ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ ሒደት ሰላማዊ የሆነው ሕዝብ መውጣትና መግባት እንደተሳነው፣ ሰው እንደ አውሬ እየተነዳ የሚገደልበት ጊዜ በመሆኑ፣ ክምር የሚቃጠልበትና ሰላም የጠፋበት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር በጣም አሳዛኝ ጊዜ ውስጥ ነን ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአሥር ዓመት ሴት ልጅ ተደፍራ መገደሏና ከተገደለች በኋላ ሕዝቡ ትልቅ የሰቆቃ ሕይወት እየኖረ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
መንገድ ተዘጋግቶ ወጣቱ ተዘዋውሮ መሥራት የማይቻልበት፣ ሁሉም ጠመንጃ ታጥቆ የሚሄድበት ክልል በመሆኑ ይህንን ቁጭ ብለን አናይም፣ ለሕዝብ የሚሆን መንግሥት እናቋቁማለን የሚል ዓላማ መያዙን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ መንግሥትና በጫካ ውስጥ ያለው ታጣቂ ኃይል ለክልሉ ሰላም ለመነጋገር ፈቃደኛ ከሆኑ የሚያቀርቡትን ሐሳብ በማዳመጥ፣ ሁለቱን አካላት የውጭ ገለልተኛ አካል ተፈልጎ እንዲያነጋግርና እንዲያደራድር የሚችልበት መንገድ ለማመቻቸትና ውጊያ የሚያካሂዱ አካላትም የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ዘላቂ ሰላም የሚፈጠርበት ሒደት እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
በሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት መሠረት አዲስ አበባን ለኦሮሚያ ተጠሪ እንድትሆን የማድረግ ዕቅድን በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ሙላቱ፣ ‹‹ኦሮሞ ያልሆኑ ብሔሮች በአዲስ አበባ እንደሚኖሩት ሁሉ በአዳማ፣ በጅማ፣ በነቀምትም ሆነ በሌላው የኦሮሚያ አካባቢ እየኖሩ እያለ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይሁን ሲባል ለምን እንደሚቆጠቁጣቸው አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በመሆኑም አዲስ አበባ በታሪክም በጂኦግራፊም ኦሮሚያ ውስጥ ያለች በመሆኗ እንዴት ሌላ አካል እንዲያስተዳድራት ይደረጋል? ይህ እኮ የፌዴራል ሥርዓቱን የሚቃረን ጉዳይ ነው የሚሆነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹የፌዴራል መንግሥት መሬት የሌለው ተቋም በመሆኑ ከፈለገ ዋና መቀመጫውን መቀሌ ወይም ባህር ዳር ሊያደርግ ይችላል፡፡ የአገሪቱ ዋና ከተማ ለኦሮሚያ ተጠሪ በመደረጓ የዋና ከተማነቱን ሚና ታጣለች ብለው የሚፈሩ አካላት ከፈለጉ የትኞቹ የአገሪቱ ከተሞች መወሰድ ይችላሉ፣ እኛ ችግር የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
ኦፌኮና ኦነግ ወደፊት በሚኖር የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይህ ጉዳይ እንዲካተት እንደሚፈልጉ የገለጹት አቶ ሙላቱ፣ ‹‹አዲስ አበባ በኦሮሚያ ሥር ብትሆን ኢትዮጵያ ትጠቀማለች እንጂ አትጎዳም፤›› ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች አካሄዱት ከተባለው ኮንፈረንስ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በኦነግና በአዲስ የኦሮሞ ፓርቲዎች መካከል የውሸት አቻነት የመፈብረክ ሒደት ነው፤›› ሲል ገልጾታል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም እንደሌላቸው ጠቅሶ፣ ይህ አቅም በሌለበት የሚደረግ ማንኛውም ድርድር በባህሪው ያልተመጣጠነና ሒደቱም በጥቂቱም ቢሆን ለገዥው ፓርቲ ቅቡልነት ማስገኛ የሆነ፣ በኦሮሚያ ውስጥ እየሞተ ያለውን የአገዛዙን ገጽታ እንደገና ለመገንባት የተነደፈ ትወና መሆኑን ከልምድ የምናውቀው ነገር ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ በመግለጫው አክሎም ኦነግና ኦፌኮ ከገዥው ፓርቲ ጋር ሊያካሂዱት የታሰበው ውይይት በሦስተኛ ወገን ሸምጋይነት የሚደረግ ሳይሆን፣ በአገዛዙ ቁጥጥር ሥር የሚደረግ ነው ብሎታል፡፡
‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር እንሠራለን ማለት በእርግጥም የኦሮሞን መንግሥት ይመራል ብሎ ማረጋገጫ እንደ መስጠት መሆኑን፣ የኦሮሞ ፖለቲካ የሚመራው በጥላቻ እንጂ በተቆጠሩ ሕዝባዊ አጀንዳ አለመሆኑን እንደ መቀበል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደ ታማኝ አጋር መቁጠርና በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ እየተፈጸመ ያለውን ተግባር ተቀባይነት እንዳለው አድርጎ ማፅደቅ ተደርጎ ይቆጠራል፤›› ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ኦነግ ሸኔ በመግለጫው ገዥው ፓርቲ ከኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ነው ባለው ንግግር፣ የሰሜን ኃይሎች ጥረቶቻቸውን አጠናክረው በመንግሥት ላይ ሥጋት እየፈጠሩ በመሆኑ፣ ኦሮሞ ተባብሮ መንግሥትን ሊጠብቀው ይገባል እያለ መሆኑ ማሳያ ነው ብሎታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ውጥረት መጨመሩን ከሁለቱም አገሮች አመላካች ጉዳዮች እየታዩ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ውጥረቱን ካባባሱት ጉዳዮች መካከል የኤርትራ ፕሬዚዳንት በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ከፋኖ ታጣቂዎችና በትግራይ ክልል ከሕወሓት አንደኛው ክንፍ ጋር የፈጠሩት ያልተለመደ ዓይነት መቀራረብ፣ ለፌደራል መንግሥቱ ሥጋት ሳይፈጥር እንዳልቀረ በመግለጽ፣ የአሮሞ ኃይሎችን ወደ አንድ የማሰባሰብ ትልም ነው የሚል መላምት ከተለያዩ አካላት ይሰማል፡፡
ኦነግ ሸኔ በመግለጫው በዚህ ጊዜ ሊጠበቅ የሚችል የኦሮሞ ሥልጣን የለም በማለት ሒደቱ ከመንግሥት ተሳትፎ ውጪ ነው ቢባልም፣ ሁለቱ ፓርቲዎች አካሄዱት በተባለው ውይይትና የመጨረሻ ስምምነት ተሳተፉ የተባሉት የአገር ሽማግሌዎች የተመረጡት በገዥው ፓርቲ አማካይነት ነው ብሏል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ከገዥው ፓርቲ ዕውቅና ውጪ የተከናወነ ስምምነት መሆኑን ቢገልጹም፣ ኦነግ ሸኔ ግን በመግለጫው ከ11 ያላነሱ የአገር መከላከያና የደኅንነት ተቋም ተወካዮች በኢሊሌ ሆቴል በተካሄደው ኮንፈረንስ መሳተፋቸውን ገልጿል፡፡
የተካሄደውን ውይይት በተመለከተ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባል አቶ ጀቤሳ ጋቢሳ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹በአጠቃላይ በኦሮሞ ማኅበረሰብ መሰባሰብ የማይደሰቱ ሰዎች፣ እንዲሁም የኦሮሞ ተወካዮች በልዩነት ውስጥ ሲኖሩ የሚያተርፉ አካላት የተደረሰውን ስምምነት ያጣጥሉታል፤›› ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የቆየ ታሪክ ያለው እንጂ እንደ ገዥው ፓርቲ የጥቂት ዓመታት ታሪክ ያለው ፓርቲ እይደለም ያሉት አቶ ጀቤሳ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እዚህ አገር ካሉ ፓርቲዎች ነፃና ከማንኛውም ጫና የፀዳ መሆኑን ማንም ያውቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብ የሚያሳፍራቸው ዘርፈው ያካበቱት ሀብት ስለሚጋለጥ ፈርተዋል፣ በመፍራታቸውም ስምምነቱን ውኃ እየረጩበት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በኦፌኮ፣ በኦነግና በሌሎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ውይይት መደረጉን በተመለከተ፣ ‹‹በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ስም ሄዶ የተለጠፈው ቡድን እንደ ድርጅት ካለበት ቁመናና ካለው ፍራቻ፣ ምናልባት ከኦፌኮ ጋር አንድ ላይ ቢቆም ዕውቅና ለማግኘት ይጠቅመኛል በሚል የተያዘ እንቅስቃሴ አድርገን እንመለከተዋለን፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደገሞ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመሩት የኦነግ ክንፍ ጋር በፍርድ ቤት የክስ ሒደት ላይ መሆናቸው ነው፡፡
ሁለቱ በአንድ ላይ ሆነው በድብቅ ያደረጉት ምክክር ሲሉ የገለጹት አቶ ቀጄላ፣ ለብቻው አፈንግጦ እየሄደ ያሉት ኦነግ ከኦፌኮ ጋር ሽርክና ከገባ አራት ዓመታት የተቆጠረ በመሆኑ አዲስ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹የሁለቱ አንድ ላይ መምጣት አዲስ ነገር አይደለም፣ አብረው ቡና ሲጠጡ የነበሩ፣ አብረው ሲበሩ የቆዩ ናቸው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የታሰበው ከአራት ዓመት በፊት በተለይም ሕወሓት ጦርነት ሲጀምር አዲስ አበባ ይመጣል በሚል በኦፌኮና በሌላኛው ኦነግ ክንፍ መሪነት እንደነበር የገለጹት አቶ ቀጄላ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ ካቢኔና ግለሰቦችን የሽግግር መንግሥት አካል እንድትሆኑ በሚል ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አሁን እያሽከረከሩት ያለው አጀንዳ አዲስ አይደለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹በመሆኑም ዕውቅና ለማግኘትና አለን ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ እነሱ ይዘውት የመጡት አጀንዳ ተቀባይነትም እርባናም የሌለው ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ቀጄላ የኦሮሞን ፖለቲካ በሽሽግር መንግሥት መምራት በሚል የቀረበው ዕቅድ በክልሉ የሚገኙ ፓርቲዎች በአንድ መድረክ ተገኝተው ሁነኛ በሆኑና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በሚያቀራርቡ አጀንዳዎች ላይ መምከር ካልተቻለ፣ ለይስሙላ ተናግረን ነበር እንዲህ ብለን ነበር ለሚል ዓላማ ብቻ እየተሰበሰቡ መግለጫ ማውጣት የትም አያደርስም በማለት አብራርተዋል፡፡
በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሁለቱ ፓርቲዎች የጋራ አጀንዳ ገዥው ፓርቲ በሰሜን ኢትዮጵያ የመጣውን ጫና ለመቀልበስ ያቀደው ነው መባሉን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አቶ ቀጄላ፣ ‹‹ከጅምሩ ገዥው ፓርቲ ቢኖርበት የሽግግር መንግሥት የሚል ዕሳቤ መስማት አይቻልም ነበር፡፡ መንግሥት ምናልባት ፓርቲዎቹ በአዲስ አበባ ተገናኝተው እንዲመክሩ አዳራሽ ሊፈቀድላቸው ይችል ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች የተሳተፉበት ኮንፈረንስ በክልሉ ያሉትን ችግሮች ተረድቶ አቅጣጫ ለመያዝ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን መንግሥት ፈቅዶ የተከናወነ ኮንፈረንስ እንደሆነ ቢነገርም፣ መንግሥት በኮንፈረንሱ ላይ ስለነበረው ሚና ግን አልገለጹም፡፡.