የፀጥታው ምክር ቤት በዩክሬን ጉዳይ ሩሲያን እንደ ፀብ አጫሪ ቆጥሮ ለማውገዝ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አሜሪካ ከሩሲያ ጎን በመሆን ተቃውማለች (ኢፒኤ)

ዓለም ለሽያጭ የቀረበው የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: February 26, 2025

ዓለም ከትናንት በስቲያ ሰኞ በርካታ አስደማሚ ክንውኖችን አስተናግዳለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በዩክሬን ጉዳይ ሩሲያን እንደ ፀብ አጫሪ ቆጥሮ ለማውገዝ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ከሩሲያ ጎን በመሆን የተቃውሞ ድምፅ በመስጠት አሜሪካ አስደማሚና ሆኖ የማያውቅ አዲስ የኃይል አሠላለፍ ታሪክ ሠርታለች፡፡

ለሽያጭ የቀረበው የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬን ሰላም ማስፈን ዙሪያ በፈረንሳይ መክረዋል (ኢዩሲ

በዕለቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፈረንሣዩን አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮንን በነጩ ቤተ መንግሥት ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ለጋዜጠኞች ከሰጡት የጋራ መግለጫ መረዳት እንደተቻለው፣ በዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታና ለአውሮፓ ደኅንነት ትኩረት ሰጥተው መክረዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አገራቸው ለዩክሬን የደኅንነት ማስተማመኛና ሌሎች ድጋፎች የምትሰጠው፣ ዩክሬን የአሜሪካን ሐሳቦች አሜን ብላ ስትቀበል እንደሆነ አስረግጠዋል፡፡ አሜሪካ ከዩክሬን ማዕድናት እንደምትፈልግ በግልጽ ማስታወቃቸውም፣ ሰውየው እንካ በእንካ ፖሊሲ የሚያራምዱ መሪ ናቸው ተብለው ከሚታሙት በላይ አድርገዋል፡፡ ‹‹አዎን፣ ዩክሬን ሰፊ የሬር ኧርዝ ሀብት አላት፡፡ ያንን ለአሜሪካ ክፍት ማድረግ ይኖርባታል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ አሜሪካን በመጪው አንድ ወይም ሁለት ሳምንታት እንደሚጎበኙም አሳውቀዋል፡፡

በሌላ ወገን በዚሁ ዕለት የሩሲያና የቻይና መሪዎች የስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይታቸው፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ስትራቴጂካዊ እንጂ በዓለም አቀፍ ሁኔታዎችና በሦስተኛ ወገኖች ተፅዕኖ ሥር የሚወድቅ እንዳልሆነ ማስገንዘባቸውን፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የኃይል አሠላለፍ መስመሮች ደምቀው መስተዋል በጀመሩበት በዚህ ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጋር ቀድሞ በስልክ አድርገውት ስለነበረ ውይይት ገለጻ እንዳደረጉላቸው መግለጫው አትቷል፡፡

በምሁራን ዕይታ

ባለፈው ዓርብ ተቀማጭነቱ በአሜሪካ ኒውዮርክ የሆነው ታዋቂው የውጭ ግንኙነቶች ምክር ቤት ‹የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ› በሚል ርዕስ አፀደ ልሂቃን (Think Tank)፣ ምሁራንና ጋዜጠኞች የተሳተፉበት ምክክር አካሂዷል፡፡ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት አሁናዊ ሁነቶች እንዲሁም በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚናዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ትንታኔዎች በቀረቡበት በዚህ ጉባዔ፣ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ማይክ ፍሮማን፣ በድርጅቱ የአውሮፓ ከፍተኛ ልሂቅ የሆኑት (የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰርም ናቸው) ቻርሊ ኩፕቻን፣ በዬል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና የሩሲያ ጉዳዮች ልሂቅ ቶም ግራሃምና በርካታ ሌሎች ምሁራንም ታድመዋል፡፡

በቀደሙት ሁለት ሳምንታት የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ሁኔታዎች፣ የአሜሪካ የአደራዳሪነት ሚናና ተያያዥ ጉዳዮችን ከአውሮፓ ደኅንነት አንፃር ለመዳሰስ የተደረጉ የሙኒክ ጀርመን የደኅንነት ከፍተኛ ጉባዔ፣ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቤተ መንግሥታቸው የጠሩት የአውሮፓ መሪዎችና የአውሮፓ ኮሚሽን ባለሥልጣናት ምክክሮች ምሁራኑ በኒውዮርክ ላደረጉት ውይይት መነሻ ግብዓቶች ነበሩ፡፡

ማይክ ፍሮማን ሲናገሩ እንደተደመጡት፣ ያለፉት ሁለት ሳምንታት ለዩክሬንና ለዩክሬናውያን ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን፣ ለአውሮፓ ደኅንነት ብሎም ለዓለም አቀፍ ደኅንነት ውቅር (International Security Architecture) መሠረታዊ የሆኑ ሁነቶች፣ ለውጦችና መናጋቶች የተስተዋሉበት ነበር፡፡ ይህ ምክክር ከመደረጉ ከወራት በፊት ምክር ቤቱ በዩክሬን ሰላም ስለሚሰፍንበት፣ ዩክሬንን መልሶ መገንባት በሚቻልባቸው ሁኔታዎችና የዚህች አገር የኢኮኖሚ ዕድገትን በማምጣት ቀጣይ ህልውናዋ በሚረጋገጥበት ጉዳይ ላይ የሚመክር ከፍተኛ ኢንሼቲቭ ተቋቁሞ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በምክክሩ ላይ እንደተገለጸው፣ ጦርነቱን ዩክሬን ማሸነፍ እንደማትችል ቀድሞውኑ የታወቀ ነበር፡፡ ቻርሊ ኩፕቻን በምሁራኑ ፊት እንደተናገሩት፣ የትራምፕ አስተዳደር የሩሲያንና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የወሰዱትን ውሳኔ እንዲሁም በትራምፕና በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተደረገውን የስልክ ውይይት ተከትሎም፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ በሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በማርኮ ሩቢዮና ሰርጌ ላቭሮቭ በአካል የተደረገ ምክክር፣ በአጠቃላይ በዋሽንግተንና በሞስኮ መካከል የተደረገውን ግንኙነት በመርህ የሚደግፉት ነው፡፡ ‹‹ይህ እንዲያውም የዘገየ ይመስለኛል፡፡ ዩክሬን ጦርነቱን እንደማታሸንፍ ካወቅን ውለን አድረናል፡፡ በመሆኑም ምክንያታዊ ሰዎች ጦርነቱ በሰላም እንዲቋጭ ያስችላል ተብለው የተወሰዱ ትርጓሜዎችን በመከለስ፣ ውጤታማ የሰላም ምክክር እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ማለት በአሁኑ ጊዜ 80 በመቶ ነፃ የሆነውን የዩክሬን ግዛት እንዴት መከላከልና የጎለበተ ዴሞክራሲ በዚያ ምድር ማስፈን እንደሚቻል መፍትሔ ማምጣት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሆኖም ከሳምንታት በፊት ሙኒክ ተገኝቼ ጄ ዲ ቫንስ፣ ኪዝ ኬሎግ እንዲሁም ሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሲናገሩ ከሰማሁ በኋላ የአሜሪካ ስትራቴጂ በጉዳዩ ላይ ምን እንደሆነ ማየት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ስትራቴጂ የለም፡፡ ይህ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩና የአገር ደኅንነት አማካሪው ዊትኮፍ ከአንድ ምንጭ እየጠለቁ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ያ ምንጭ የለም፤›› ብለዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚቀርበው ትችት፣ የትራምፕ አስተዳደር የዩክሬን ድርድር ከመጀመሩ አስቀድሞ የዚያች አገር የኔቶ አባልነት አጀንዳን ከድርድሩ ጠረጴዛ የሰወረበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ዩክሬን ግዛቷን እ.ኤ.አ. በ2014 ወደ ነበረው የመመለስ ውጥኗን እንድትተውና አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን እንደማትልክ ቀድመው አቋም የያዙበት ጉዳይ ነው፡፡

‹‹ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሳይነሳ ስለንግድ ትብብር የመነሳቱ ጉዳይም ጋሪውን ከፈረሱ እንደማስቀደም ይቆጠራል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ምሁሩ ከላይ የተገለጹ ትችቶቻቸውን ቢሰነዝሩም፣ በሩሲያና በአሜሪካ ቀጥተኛ ንግግር የመደረጉን አስፈላጊነት ይደግፋሉ፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ደግሞ አገራቸው ያልተሳተፈችበት ንግግር ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል በመናገር የፕሬዚዳንት ትራምፕን ቁጣ ቀስቅሰዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፉት ሳምንታት ባንፀባረቁት አቋም፣ ዩክሬንን ‹‹የተወሰነልሽን ተቀበይ›› ዓይነት አካሄድ ከመምረጣቸው ባሻገር፣ ዘለንስኪን ‹‹አምባገነን›› ብለው ከመጥራት አልፈው አሜሪካ ከዩክሬን ወሳኝ የሆኑትን ሬር ኧርዝ ማዕድናት እንደምትሻ (Rare Earth Minerals) ተናግረዋል፡፡

ቶም ግራሃም በበኩላቸው፣ ጉዳዩን ከሩሲያ አቋም አንፃር ለመፈተሽ ሞክረዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ውይይቶች ዩክሬንን ብቻ የሚመለከቱ ሳይሆኑ የአውሮፓን ደኅንነት ጭምር የሚያካትቱ ነበሩ፡፡ በትራምፕና በፑቲን መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት ከዩክሬን ባለፈ የመካለለኛው ምሥራቅ፣ የኃይል ደኅንነት (Energy Security) የአርክቲክ አካባቢ ጉዳዮችና ስትራቴጂካዊ መረጋጋት ተነስቷል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዩክሬንን በተመለከተ ብቻ ያለውን ስንመለከት፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን በተደጋጋሚ እንደተናገሩት፣ የአገራቸው ፍላጎት በተኩስ አቁም ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ እንደ ፑቲን፣ ድርድሩ የግጭቱን ሥረ መንስዔዎች መፈተሽ፣ መፍትሔ ማፈላለግና ከስምምነት መድረስ ይኖርበታል፡፡ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት አማካሪ ዊትኮፍ ሞስኮ በነበሩበት ቀናት ከፑቲን ጋር ይህንን ጉዳይ በጥልቀት መክረዋል፡፡ ይህንኑ የሩሲያ አቋምም ለትራምፕ በጥልቀት ያስረዳሉ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ትራምፕ ለመሥራት እየሞከሩ ያሉትን በመርህ ደረጃ ባደንቀውም፣ በተግባር ግን የጨረባ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

እኚሁ ምሁር እንደሚሉት፣ ይህ የሩሲያ አቋም በአሜሪካ መነፅር ሲፈተሽ ሰፊ ልዩነቶች ይንፀባረቁበታል፡፡ ‹‹እኛ (አሜሪካውያን) ለዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተለየ ራዕይ አለን፡፡ ግባችን በትንሹ የዩክሬንን ሉዓላዊነት በማስቀጠል በምዕራባዊ እሴቶች የተቃኘች ነፃ ዩክሬን እንድትኖር ማረጋገጥ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ እሑድ ዕለት በተደረገ የጀርመን አስቸኳይ ምርጫ (Snap Election) የወግ አጥባቂ ዕጩ ፍሬድሪሽ መርዝ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝን ማሸነፋቸው፣ አውሮፓ ቀስ በቀስ በቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች እየተያዘች እንደምትመጣ የሚያመላክት ከመሆኑ ባሻገር፣ የአውሮፓ ኅብረት በዩክሬን ጉዳይ ሲያራምድ የቆየውን አቋም የሚለውጥ ባይሆን እንኳን የሚሸረሽር እንደሚሆን አንዳንድ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲጭን የቆየውን ማዕቀቦች በመቀጠል፣ ባለፈው ሳምንት 16ኛ የተባለውን ማዕቀብ አስተዋውቋል፡፡ የአውሮፓ መሪዎች በፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጥሪ በፓሪስ ያደረጉትን ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ የነበረ ስብሰባ ተከትሎ፣ የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ የጣለው ማዕቀብ በ45 ሰዎችና በ35 ተቋማት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ዘገባዎቹ ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ማዕቀብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰነው ከሩሲያ ውጭ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት የሩሲያን የገንዘብ ዝውውር መልዕክት ማስተላለፊያ (Russian System for Transfer of Financial Messages) እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ነው፡፡ እንደ ዩሬዥያ ዴይሊ፣ ሌንታና ቲቪዚቬዝዳ ያሉ የሩሲያን የወታደራዊና ኢንዱስትሪያል ‹‹ፕሮፓጋንዳ›› የሚያሠራጩና የሚደግፉ ድርጅቶችንም ሳይቀር ነው አዲሱ የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ዒላማ ያደረገው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ የጣላቸው ማዕቀቦች ግን ምን ያህል ውጤታማ እንደነበሩ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡

ትራምፕ በዩክሬን ላይ ፊታቸውን ማጥቆር በጀመሩበት በዚህ ወቅት የአውሮፓ ኅብረት ክፍተቱን የመሙላት አቋም ላይ ነው? የሚል ጥያቄ በፖለቲካና በወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኞች ዘንድ በተደጋጋሚ ሲነሳ የሚደመጥ ሲሆን፣ በርካቶች አሁናዊው የአውሮፓ አቋም በአሜሪካ የአቋም ለውጥ ሳቢያ የመጣውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል እንዳልሆነ ይስማማሉ፡፡

ትራምፕ በኤክስ ገጻቸው በግልጽ እንዳመለከቱት፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ፈጥነው የአሜሪካን ጥያቄዎች ለመመለስ የማይንቀሳቀሱ ከሆነ፣ አገር የሚኖራቸው አይሆኑም፡፡ እነዚህ የተባሉት የአሜሪካ ጥያቄዎች ዩክሬን ማዕድኗን ለአሜሪካ ክፍት እንድታደርግ የሚያሳስበውን ያካትታሉ፡፡ በዚህም ዘለንስኪ የአገርን ነፃነት በአገራቸው ማዕድናት ገዝተው የማዳን ውሳኔ የተጋረጠባቸው ይመስላል፡፡ እሳቸው ደግሞ ሰሞኑን አገራቸው ዩክሬን የኔቶ አባልነትን የምታገኝ ከሆነ የፕሬዚዳንትነት ሥልጠናቸውን ለማስረከብ ፈቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸው ሌላ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡