

የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ
ኪንና ባህል የዓይነ ሥውር ድምፃውያን ትሩፋት
ቀን: February 26, 2025
ዓይነ ሥውራን ድምፃውያንና ሙዚቀኞች በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ማኖራቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በእነ ሮሃ፣ አይቤክስ፣ ዋልያና ኤክስፕረስ ባንዶች ውስጥ በመቀላቀል ዘመን የማይሽራቸውን የሙዚቃ ሥራዎች ስለመሥራታቸውም ይነገራል፡፡

በዓይነ ሥውራን የተመሠረተው ‹‹ሬንቦ›› ባንድም በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የታዋቂ ድምፃውያንን የሙዚቃ ሥራዎች በመሥራት ከፍ ያለ ስም ያተረፈ ነበር፡፡ ድምፃዊ ተሾመ አሰግድ፣ ዘመድ ገብረ አምላክ፣ በቀለ ኃይለ ሥላሴና ሌሎችም የባንዱ ፈርጥ የነበሩ ስለመሆናቸውም ይወሳል፡፡
ድምፃዊ ባልከው ዓለሙ እንደሚገልጸው፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ዓይነ ሥውራን የሙዚቃ ሰዎች በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በሙዚቃ ሕይወቱ ላይ መሠረት የጣሉለትና ፈለጋቸውን በመከተልም ሥራዎቹን ለሕዝብ እንዲያበረክት መንገድ የሆኑት መሆኑን ይናገራል፡፡
በሰበታ መርሐ ዕዉራን ትምህርት ቤት ሙዚቃ መጫወት መጀመሩን የሚገልጸው ድምፃዊው፣ በትምህርት ቤቱ ያገኘው የንድፈ ሐሳብና የተግባር ትምህርት የሙዚቃ ሙያን እንዲቀላቀልና በዘርፉ የራሱን ቀለም ይዞ እንዲወጣ አግዞታል፡፡
በድምፃዊነቱና በኪቦርድ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነቱ የሚታወቀው ተሾመ አሰግድ፣ ዘመድ ገብረ አምላክ፣ ንጉሤ ኃይሉ፣ በቀለ ኃይለ ሥላሴና ሌሎችም በስም ያልተጠቀሱ ድምፃውያን፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች፣ የዜማና የግጥም ደራስያን ዛሬ ጎልተው ለወጡ ወጣት ዓይነ ሥውራን የሙዚቃ ሰዎች አርዓያና ምሳሌ ሆነዋል፡፡
‹‹ዓይነ ሥውራን ሙዚቀኞች፣ የአካል ጉዳት አልባ ሙያተኞች ከሚገጥማቸው ችግር በተለየ የሚደርስባቸው ችግር አለ ብዬ አልገምትም፤›› የሚለው ባልከው፣ እንደ አጠቃላይ በሙዚቃ ሥራው ላይ ያለው መቀዛቀዝና ዘርፉ ዲጂታል በሆነ መልኩ እየተቃኘ መምጣቱ ለድምፃውያን ፈተና መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ድምፃዊው እንደሚገልጸው፣ ዓይነ ሥውራን የሙዚቃ ሰዎች በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ምትክ የሌለው አሻራ አኑረዋል፡፡ በተለይ በዓይነ ሥውራን ሙዚቀኞች የተመሠረተው ‹‹ሬንቦ ባንድ›› በወቅቱ የእነ ጥላሁን ገሠሠን፣ ፀሐይ እንዳለና የሌሎችንም ታዋቂ ድምፃውያን የሙዚቃ ሸክላ ለማሳተም የቻለ ነው፡፡
‹‹በሰላም ኢትዮጵያና በሙዚቃዊ በኩል የግሉን፣ ከስንታየሁ በላይ ጋር በጥምረት የሙዚቃ ሥራዎችን ለሕዝብ ማድረሱን የሚናገረው ባልከው፣ ‹‹ፈልጌ፣ ዘውዲቱና ለፍቅር ብላ›› በግል የሠራቸው ሲሆኑ፣ ‹‹በሐሳቤ›› እና ‹‹ይገርማል›› የተባሉ ሁለት ሙዚቃዎችን በጥምረት ለመሥራት ችሏል፡፡ እነኚህ የሙዚቃ ሥራዎቹና በተለይ ደግሞ በባላገሩ አይዶል የሙዚቃ ውድድር ላይ የነበረው ተሳትፎ ከሕዝብ ጋር እንዲተዋወቅ መንገድ የጠረጉለት መሆኑንም አስታውሷል፡፡
ስንታየሁ በላይ ሌላዋ ዓይነ ሥውር ድምፃዊት ናት፡፡ ‹‹ፋና ራያ›› በሚባል የባህል ቡድን ውስጥ በድምፃዊነት ሙዚቃ የጀመረችው ስንታየሁ፣ ተሰጥኦና ችሎታዋን እንድታዳብር የባህል ቡድኑ ረድቶኛል ብላለች፡፡
‹‹ሰላም ኢትዮጵያ›› በተባለ ድርጅት አማካይነት በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል አምስት የሙዚቃ ሥራዎችን በተናጠልና በጋራ ለአድማጭ ማድረስ ችያለሁ፤›› የምትለው ድምፃዊቷ፣ ‹‹ይገርማል›› እና ‹‹ከሐሳቤ›› የተሰኙ ሙዚቃዎች ከድምፃዊ ባልከው ጋር በቅብብሎሽ የተጫወተቻቸው መሆኑን ተናግራለች፡፡
ድምፃዊት ስንታየሁ እንደምትገልጸው፣ አካል ጉዳተኛ መሆኗ በሙዚቃ ሕይወቷ ላይ ያሳደረባት ተፅዕኖ የለም፡፡ ለሙዚቃ ያላትን ፍላጎትና ችሎታዋን የተረዱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከህልሟ ጋር እንድትገናኝ በብዙ የደገፏት መሆኑንም ታክላለች፡፡
‹‹የሠራሁት የሙዚቃ አልበም ግማሽ አልበም በሚባል ደረጃ የተዘጋጀ ነው፤›› የምትለው ድምፃዊቷ፣ አልበሙ በሕዝብ ዘንድ እንድትታወቅና ተቀባይነት እንድታገኝ ረድቷታል፡፡ ለቀጣይ ሥራዋ ስንቅ የሚሆን አስተያየቶችንም አግኝታበታለች፡፡
እንደ ድምፃዊቷ፣ ከቀደምት ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ዓይነ ሥውራን ሙዚቀኞች በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ላይ ደማቅ አሻራ አኑረዋል፡፡ ድምፃውያኑ ተሾመ አሰግድ፣ ይርዳው ጤናውና ከዘመነኞቹ ድምፃዊ በኩረ አማኑኤልና ሌሎችም ወጣት ሙዚቀኞች ያበረከቱትና እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ዋጋው በቀላል የሚተመን አይደለም፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው ዳዊት ይፍሩ እንደሚገልጹት፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ዓይነ ሥውራን ድምፃውያን የነበራቸው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ ለየት ያለና የሚገርም ሥራ ከሠሩ ዓይነ ሥውራን ሙዚቀኞች መካከል ከአይቤክስ ባንድ ጋር ይሠራ የነበረውና በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ የሚጫወተው ኃይለ ማርያም የሚጠቀስ ነው፡፡
ድምፃዊና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቹ ተሾመ አሰግድ፣ አብዱቄ ከፈኔና ሌሎችም አሁን የዘነጋኋቸው የሙዚቃ ሰዎች በተለያዩ ባንዶች ውስጥ በመታቀፍ የላቀ የሙዚቃ ሥራ ማበርከት ችለዋል፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው እንደተናገሩት፣ ሰበታ መርሐ ዕዉራን የሚማሩ ተማሪዎች በተጓዳኝ የሙዚቃ ትምህርት እንዲማሩ ይደረግ ነበር፡፡ ‹‹ወጋገን›› የሚባል ባንድም ነበራቸው፡፡፡ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነታቸውም ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስመ ጥር ድምፃውያንን ለማጀብ የቻሉ ናቸው፡፡
‹‹በዚህ ዘመን የሚገኙ ወጣት ዓይነ ሥውራን የሙዚቃ ሰዎች የቀደምቶቻቸውን ፈለግ በመከተል ጥዑም ዜማ እያስደመጡን ይገኛሉ፤›› የሚሉት ባለሙያው፣ እነ ይርዳው ጤናው፣ በኢትዮጵያ አይዶል የሙዚቃ ውድድር ላይ የምናውቃቸውና በቅርቡ ሥራዎቻቸውን ለአድማጭ በማቅረብ ላይ የሚገኙት ድምፃውያን ለአብነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቀደም ሲል ለዓይነ ሥውራን ተማሪዎች አገልግሎት አይሰጥም ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዓይነ ሥውራን በኖታ የተጻፈውን ማንበብ አይችሉም የሚል ዕሳቤ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የዓይነ ሥውራን ማኅበር ‹‹ትምህርት ቤቱ ለዓይነ ሥውራን ክፍት መሆን አለበት›› የሚል ንቅናቄ በመፍጠር ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለዓይነ ሥውራን ተማሪዎች ሊፈቀድ ችሏል፡፡ በተቋሙ ገብተውና ሠልጥነው የወጡ ድምፃውያንና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች በተለያዩ ባንዶች ውስጥ በመታቀፍ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ዘመን አይሽሬ ሥራዎችን ለማበርከት መቻላቸውን የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ ገልጸዋል፡፡