ትራምፕ እና ዘለንስኪ

ከ 5 ሰአት በፊት

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አርብ ወደ ዋሺንግተን አቅንተው ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚገናኙ ተነግሯል።

ዘለንስኪ ትራምፕን የሚያገኟቸው የሀገራቸውን ማዕድን ለአሜሪካ ለማጋራት መሆኑን ትራምፕ ተናግረዋል።

ዘለንስኪ ስምምነቱ ገና ጅማሮ ላይ ያለ ነው ብለው አሜሪካ ከአዲስ የሩሲያ ጥቃት እንምትከላከላቸው ማስተማመኛ እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል።

ነገር ግን ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ ምንም ዓይነት ማስተማመኛ እንደማታቀርብ ተናግረው ኃላፊነቱ መሆን ያለበት የአውሮፓ ነው ብለዋል።

በተጨማሪ ትራምፕ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን (ኔቶ) አባል የመሆኗ ነገር የማይታሰብ ነው ሲሉ የዘለንስኪ የረዥም ጊዜ ዕቅድን አጣጥለዋል።

ረቡዕ በካቢኔያቸው ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ አሜሪካዊያን ማዕድን አውጭዎች በዩክሬን ተገኝተው ውድ የሚባሉ የመሬት ማዕድናትን ማውጣታቸው ለዩክሬን “ትልቅ ደኅንነት ያጎናፅፋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለው ኪየቭ ኔቶን መቀላቀል የሚለውን ሐሳብ “እንድትረሳው” ተናግረው ይህ ጉዳይ ለሩሲያ ጦርነት መጀመር ምክንያት ነው ሲሉ የሞስኮውን አቋም አንፀባርቀዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረግ መቃረቡን ጠቁመው “የሰዎች መገደል እንዲቆም ከሩሲያ እና ዩክሬን ጋር ስምምነት እንፈፅማለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ቢሆንም ዘለንስኪ የዩክሬን ደኅንነት የሚረጋገጥበት ማስተማመኛ ከሌለ “የተኩስ አቁም ስምምነት አናደርግም። ምንም ሊሳካ አይችል። ምንም” ብለዋል።

“በኔቶ በኩል አሊያም በተመሳሳይ መንገድ መፍትሔ መፈጠር አለበት” ብለዋል ዘለንስኪ።

ሩሲያ፤ ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል ይገባል የሚለውን ሐሳብ አጥብቃ የምትቃወመው ሲሆን ይህ ከሆነ የኔቶ ኃይሎች ወደ ድንበሬ ይቀርባሉ የሚል ስጋቷን ትገልፃለች።

በአውሮፓውያኑ 2008 ነው የጦር ቃል-ኪዳኑ ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል ትችላለች የሚል አስተያየት የሰጠው።

ትራምፕ የአውሮፓ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በዩክሬን ይሰፍራሉ የሚል ጥቆማ ቢሰጡም ሩሲያ ግን ይህን አትደግፍም።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሩሲያ ጋር በምታደርገው የተኩስ አቁም ስምምነት የአውሮፓ ተወካዮች አለመካተታቸው አውሮፓውያንን ያስቆጣ ይመስላል።

የአውሮፓው የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ልዑክ ካጃ ካላስ “በአውሮፓ ምድር ላይ ለሚፈፀም የትኛውም ስምምነት አውሮፓውያን ሊካተቱ ይገባል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልዑኳ አክለው ዩክሬን ማዕድኗን በተመለከተ የምታደርገው ውል የግሏ ቢሆን የሰላም ስምምነቱ “አውሮፓውያንን ማካተት አለበት” ብለዋል።

ካጃ ካላስ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ረቡዕ ሊያደርጉ የነበረው ውይይት በጊዜ መጣበብ ምክንያት ተሰርዟል።

ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር በያዝነው ሳምንት መገባደጃ የሚያደርጉት የማዕድን ውል ከትራምፕ ጋር በሚኖራቸው ውይይት ላይ የሚመሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕድን ውል የሚለውን ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት የዩክሬኑ መሪ ዘለንስኪ ሲሆኑ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል ያሰበ ዕደቅ ነው።