
ከ 1 ሰአት በፊት
በመገናኝ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ማኅበራት ተቃውሞ የገጠመው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅ የሚጠበቀው ማሻሻያ ሳይደረግበት እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
ዓለም አቀፉ የፕሬስ ተቋም (IPI) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ላይ የተካተቱን ድንጋጌዎች ውድቅ እንዲያደርጉት ጥያቄ አቅርቧል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በተካሄደ ውይይት ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ጋዜጠኞች ተቃውሞ ያቀረቡባቸው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጁ አንቀጾች ማሻሻያ ሳይደረግባቸው እንዲጸድቅ ለምክር ቤት መቅረቡን ቢቢሲ የተመለከተው ረቂቅ ያመለክታል።
የፕሬስ ነጻነት ላይ የሚሠራው ተቋም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ የአገሪቱ የሚዲያ ሕግ ላይ የተደረገው ማሻሻያ “የሚዲያ ነጻነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል” ብሏል።
ተቋሙ አክሎም የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ማሻሻያው “የሚዲያ ተቆጣጣሪውን ነፃነት ስለሚያዳክም እና በሌሎች ስጋቶች ምክንያት የቀረቡትን ማሻሻያዎች ውድቅ እንዲያደርጉ” አሳስቧል።
ቢቢሲ የተመለከተው እና ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተላከው የውሳኔ ሃሳቡ ቀደም ሲል ተቃውሞ የቀረበባቸው እና ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ተጠየቁ ጉዳዮችን ሳያሻሽላቸው ቀርቷል።
የምክር ቤት አባላት ከአንድ ወር ዕረፍት ሲመለሱ አዋጁን ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በምክር ቤቱ የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።
በዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ “የሃሳብ ነፃነት ባልተገባ መንገድ ሲገለፅ እና ከሕግ ውጪ ሲሆን ደግሞ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚገባ መሆኑ[ን]” ያትታል።
በሥራ ላይ ያለው አዋጅ “በባለሥልጣኑ ተግባር እና ኃላፊነት እንዲሁም የዕለት ተዕለት ሥራዎች አፈጻጸም ላይ ክፍተት የፈጠረ” መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
የብልጽግና ፓርቲ ተወካዩ አቶ እውነቱ አለነ በሰብሳቢነት የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴ በምርመራ ሂደት ሥራ ላይ ያለው አዋጅ፤ “ከመገናኛ ብዙኃን የቁጥጥር ሥልጣን እና ተግባር አኳያ ሲመዘን በርካታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ” መለየቱን በውሳኔ ሃሳቡ ላይ አስፍሯል።
“አዋጁ ሚዲያዎች ጥብቅ የሆነ የኤዴቶሪያል ፖሊስ አውጥተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ አያስገድዳቸውም” ያለው የቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ፤ “የሚዲያ ነፃነት እና የሕግ ተጠያቂነት ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ያላደረገ መሆኑን” ጠቁሟል።
- “እርዳታ ያስፈልገናል”: ከምያንማር የወንጀል ካምፖች የተለቀቁ ኢትዮጵያውያን ስጋት ውስጥ ገብተዋልከ 2 ሰአት በፊት
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከተስማሙ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞቃዲሾን ሊጎበኙ ነውከ 6 ሰአት በፊት
- ዘለንስኪ ወደ ዋሺንግተን አቅንተው ከትራምፕ ጋር የማዕድን ውል ሊፈፅሙ ነውከ 5 ሰአት በፊት
ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በስድስት ገጾች የተዘጋጀው የውሳኔ ሃሳብ ብዙ ተቃውሞ የተነሳበት ረቂቅ አዋጅ ላይ ያሻሻለው ሦስት አንቀጾችን ብቻ ነው።
ከአራት ዓመታት በፊት የወጣውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የሚያሻሽለው ይህ ረቂቅ አዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምክር ቤት የቀረበው ባለፈው ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ነበር።
ረቂቅ ማሻሻያው ለመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ተሰጥተው የነበሩ ሥልጣኖችን ለባለሥልጣኑ የሚሰጡ ድንጋጌዎችን አካትቶ ነው ማሻሻያ የተደረገበት።
ማሻሻያው የባለሥልጣኑ የቦርድ አባላት የሚመለመሉበት እና የሚሾሙበት አኳዃን ላይ ጉልህ ማሻሻያ አድርጓል።
ረቂቅ ማሻሻያው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርን የመሾም ሥልጣንንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጥ ነው። በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ ዋና ዳይሬክተሩ የሚሾሙት በመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ አቅራቢነት ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ወይም ተቀጣሪዎች የቦርዱ አባል እንዳይሆኑ የሚከለክለው የአዋጁ ድንጋጌ በማሻሻያው ተሰርዟል። የቦርድ አባላት ምልመላ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት የሚያትተውን አንቀጽም እንዲሰረዝ ተደርጓል።
በነባሩ አዋጅ ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች በማሻሻያው ለመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑ ተሰጥተዋል።
ዓለም አቀፉ የፕሬስ ተቋም የማሻሻያ ሃሳቦቹ ከአራት ዓመታት በፊት “በ2013 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ የተገኙት ዕድሎች ላይ ወድቀት የሚያስከትል እና በኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኝነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ብሏል።
የጋዜጠኞችን ቅድመ ክስ እስር ያስቀረው በ2013 የወጣው ነባሩ አዋጅ “በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነትን ለማስጠበቅ በጎ እርምጃ ተደርጎ መወሰዱን” ተቋሙ ገልጿል።
የማሻሻያ ረቂቁ “የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ነፃነት ሊያዳክም እና በአስተዳደራዊ ቅልጥፍና ስም የመንግሥት ቁጥጥርን ሊያጠንክር ይችላል” የሚል ስጋት እንዳለው ተቋሙ አስታውቋል።