
ከ 6 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት የቆየውን ውዝግባቸውን በድርድር ከፈቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለይፋዊ ጉብኝት ሞቃዲሾ ገቡ።
ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ጥረት እያደረጉ ባለበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 20/2017 ዓ.ም. በሞቃዲሾ በሚያደርጉት ጉብኝት ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ይወያያሉ ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሞቃዲሾ ከሚገኘው አደን አብዱሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ጉብኝቱን አስመልክቶ ይህ ጉብኝት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃ መሆኑን እንዲሁም ሁለቱ አገራት መሪዎች “በቁልፍ የሁለትዮሽ እና የጋራ በሆኑ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ” እንደሚወያዩ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ እንደግዛቷ አካል የምትቆጥራት እና ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ነጻ አገርነቷን አውጃ ከምትገኘው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰንድ ከፈረመች በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል የተካረረ ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ የሁለቱ አገራት ወዳጅ በሆነችው ቱርክ አቀራራቢነት ከረገበ በኋላ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ነነበር።
ባለፉት ወራት የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሞቃዲሾ እና በአዲስ አበባ በመገናኘት ቱርክ አንካራ ላይ የደረሱትን የትብብር ስምምነት ለማጽናት ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሊያ ከሚያደርጉት ጉብኝት ቀደም ብሎ ጥር 3/2017 ዓ.ም. የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደ አንድ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ምንጭ “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ቡድን” በሞቃዲሾ የሥራ ጉብኝት እንሚያደርግ ቀደም ብለው ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ገልጸው ነበር።
ምንጩ ጨምሮም “ይህ ጉብኝት የአንካራውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች አንድ አካል ነው” በማለት በቱርክ ዋና ከተማ የተደረሰውን ስምምነት ጠቅሰዋል።
- በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ጦር ሁኔታን በተመለከተ አሠራር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ተደረሰ24 የካቲት 2025
- የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትይዩ መንግሥት ለመመሥረት እያደረገ ያለው ጥረት ምን ያመለክታል?26 የካቲት 2025
- የአሜሪካ ዜግነት ያስገኛል የተባለው “የወርቅ ካርድ” ምንድነው? ለእነማንስ ይሸጣል?26 የካቲት 2025

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሌሎች የሶማሊያ የመገናኛ ብዙኃንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት እንደሚካሄድ ያረጋገጡ ሲሆን፣ በጉብኝቱ በቱርክ አንካራ የተደረሰውን ስምምነት የበለጠ ለማጠናከር እና በሌሎች የትብብር ጉዳዮች ላይ ሁለቱ መሪዎች እንደሚወያዩ ዘግበዋል።
የውይይት አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የተዕኮ ጊዜው ባበቃው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ምትክ በሚቋቋመው ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሚኖራቸውን ሚና የሚመለከት እንደሚኖርበት ጋሮዌኦንላይን የተባለው የበይነ መረብ ዜን ምንጭ ዘግቧል።
ሸበሌሚዲያ የተባለው የዜና ምንጭ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የልዑካን ቡድን ከሶማሊያ ባለሥልጣናት ጋር በደኅንነት ጉዳዮች፣ በምጣኔ ሀብት እና ቀጣናዊ ግንኙነትን ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እንሚወያዩ አመልክቷል።
ከአስራ አምስት በላይ በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ ሶማሊያ ከአገሯ እንዲወጣ ወስና ነበር። ነገር ግን በቱርክ አሸማጋይነት ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በአዲሱ ስምሪት ውስጥ እንዲካተት መስማማታቸው ተነግሯል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት አስመልክቶ ከረቡዕ ጀምሮ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ዝግጅት እየተደረገ እንደነበር ተገልጿል።
በጎዳናዎች ላይ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሰንደቅ ዓላማዎች ከመሰቀላቸው በተጨማሪ የሁለቱ አገራት መሪዎች ምሥሎችም ከእንኳን ደህና መጡ መልዕክት ጋር በዋና መንገዶች ላይ ተሰቅለዋል።
ሸበሌሚዲያ የሞቃዲሾ ፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት ቀደም ብሎ በዋና ከተማዋ ያለው የደኅንነት ጥበቃ መጠናከሩን እና ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል መሰማራቱን ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ያደርጉታል ተብሎ ከሚጠበቀው ጉብኝት ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሞቃዲሾ ውስጥ ተገኝተው ስምምነት ፈርመዋል።
ሁለቱ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከሶማሊያ አቻዎቻቸው ጋር በሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁኔታን በተመለከተ አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት መፈራራመቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት እና ከአገሪቱ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በተለያዩ የሶማሊያ ክፍል ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲወጡ ጠይቃ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ይህንን አቋማን ቀይራ የኢትዮጵያ ጦር ስምሪት እንዲቀጥል እንደምትፈልግ እየተነገረ ነው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባታቸውን ለመፍታት ከተስማሙ በኋላ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ የነበረው በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ምንጭ የሆነው ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ አስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም።