በታይላንድ መጠለያ ክፍል ጨለማ ውስጥ ተደርድርው ወደ ውጭ እያዩ የቆሙ ወንዶች
የምስሉ መግለጫ,ከወንጀል ካምፖች ወጥተው በታጣቂዎች እጅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስለ ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ስጋት ውስጥ ገብተዋል

28 የካቲት 2025

በምያንማር በሚገኙ የወንጀል ካምፖች በግዳጅ ሠራተኝነት ተይዘው የነበሩ ቢያንስ 800 ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሁለት ታጣቂዎች እጅ ላይ እንደሚገኙ በታይላንድ ያሉ የእርዳታ ድርጅት ምንጮች እና በታጣቂዎቹ ስር ያሉ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከምያንማር ወጥተው ወደ ታይላንድ የገቡ 138 ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችል የአውሮፕላን ትኬት ለመቁረጥ የእርዳታ ድርጅቶች ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑ ተገልጿል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ምያንማር ውስጥ፤ የሳይበር ማጭበርበር የሚከናወንባቸው ከ150 በላይ የወንጀል ካምፖች ይገኛሉ።

በእነዚህ ካምፖች ውስጥ “የስራ እድል ታገኛላችሁ” በሚል የተታለሉ የተለያዩ አገራት ዜጎች የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያውያኑ ቁጥር ሦስት ሺህ ገደማ እንደሚሆን ይገመታል።

በግዳጅ የማጭበርበር ተግባር እንዲያከናውኑ የሚደረጉት ኢትዮጵያውያኑ፤ድብደባ እና በኤሌክትሪክ ሾክ መደረግን ጨምሮ የተለያዩ የስቅይት ተግባራት ይፈጸሙባቸዋል።

የምያንማር ጎረቤት የሆነችው ታይላንድ፤ በድንበሯ አቅራቢያ በሚገኙ ካምፖች ውስጥ የሚፈጸመውን ይህንን የወንጀል እንቅስቃሴ ለማስቆም ባለፉት ሳምንታት እርምጃዎችን ወስዳለች።

የአገሪቱ መንግሥት ከታይላንድ ተነስተው ወደ ምያንማር የሚገቡት የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮች እንዲሁ የነዳጅ አቅርቦት እንዲቆም አድርጓል።

የዚህ እርምጃ ጫና፤አካባቢውን የሚቆጣጠሩት የተለያዩ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ከለላ ሲሰጧቸው በነበሩት ካምፖች ላይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ አድርጓቸዋል።

ታጣቂዎቹ በካምፖቹ ውስጥ በግዳጅ ሠራተኝነት የተያዙ ተጎጂዎችን ማስወጣት የጀመሩ ሲሆን፣ ከሁለት ሳምንት በፊት የካቲት 5/2017 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹን 261 ሰዎችን ወደ ታይላንድ ልከዋል።

“ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” በተባለው ታጣቂ ቡድን ከተለቀቁት ከእነዚህ ተጎጂዎች ውስጥ ከግማሽ በላዩ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

የተለቀቁ ኢትዮጵያውያን ሻንጣዎቻቸውን ይዘው ሰልፍ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ከሁለት ሳምንት በፊት ከተለቀቁት የ19 ሀገራት ዜጎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ኢትዮጵያውያን ናቸው

ካረን በተባለው የምያንማር ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሱት “ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” (DKBA) እና “ቦርደር ጋርድ ፎርስ” (BGF) የተባሉት ታጣቂ ቡድኖች ባለፈው እና በዚህ ሳምንት በካምፖቹ ውስጥ በግዳጅ የተያዙ ሰዎችን አስወጥተዋል።

የምያንማር ወታደራዊ መንግሥት አጋር ሆነው “ቦርደር ጋርድ ፎርስ” የተባለው ታጣቂ ቡድን ከ29 አገራት የተወጣጡ ከሰባት ሺህ በላይ የግዳጅ ሠራተኞችን ከካምፖቹ ማስወጣቱን ገልጾ ነበር።

ከምያንማር ካምፖች ወጥተው በሁለቱ ታጣቂዎች ስር የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ብዛት በድምሩ 818 እንደሆነ የግዳጅ ሠራተኞቹን ወደ አገራቸው ለመላክ የሚሰሩ በታይላንድ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በ”ቦርደር ጋርድ ፎርስ” ስር 430 ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ የገለጹት ምንጮቹ፤ “ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” ስር ደግሞ 430 የአገሪቱ ዜጎች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሁለቱ ታጣቂዎቹ ስር የሚገኙ አምስት ኢትዮጵያውያን፤ ከዚሁ ጋር ተቀራራቢነት ያለው ቁጥር ጠቅሰዋል።

በ”ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” እጅ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ብዛታቸው ከ300 እስከ 350 እንደሚደርስ ገልጸዋል።

የምያንማር ወታደራዊ መንግሥት አጋር በሆነው “ቦርደር ጋርድ ፎርስ” ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው ብዛታቸው ከ600 በላይ እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህ ታጣቂ ቡድን ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወጡት “ኬኬ 1″፣ “ኬኬ 2” እና “ኬኬ 3” ከተባሉት የወንጀል ካምፖች እንደሆነም ተናግረዋል።

ስጋት እና ተስፋ በታጣቂዎች እጅ

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

በ”ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” እጅ የሚገኙት 450 ገደማ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ከካምፑ የወጡት ከሁለት ሳምንት በፊት ቅዳሜ የካቲት 8/ 2017 ዓ.ም. ሌሊት እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

በዕለቱ በካምፑ ውስጥ የነበሩት ከ400 በላይ የግዳጅ ሠራተኞች “አንሰራም” ብለው በማመፅ በኅብረት ወደ ግቢው መውጫ ማምራታቸውን ተናግረዋል።

የግዳጅ ሠራተኞቹ ነጻ ለመውጣት ያመፁት፤ ከሶስት ቀናት አስቀድሞ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 261 ሰዎች ነጻ ወጥተው ወደ ታይላንድ መላካቸውን በመስማታቸው እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በካምፑ ነበሩ ሦስት ኢትዮጵያውያን አስረድተዋል።

“ግቢው ውስጥ ያለ ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ በአንድ ድምፅ ተነሳ። ከቁጥጥር ውጪ ሲሆንባቸው ለቀቁን። ተያይዘን ወደ ፓርኩ በር ነው የሄድነው። ግቢው በር ላይ እንደወጣን የ DKBA [ታጣቂ ቡድን] አመራሮች መጡ። ከዚያ ቦታ ያስወጡን እነሱ ናቸው” ሲል አንድ ኢትዮጵያዊ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከግቢው በር ላይ የተቀበሏቸው ታጣቂዎች በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ “ትምህርት ቤት በሚመስል” ግቢ ውስጥ እንዲቆዩ እንዳደረጓቸው ገልጸዋል።

በቀጣዮቹ ቀናትም ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ በግቢው ውስጥ የቀሩ ሌሎች ሰዎች እያስወጡ ወደዚሁ ስፍራ ማምጣታቸውን አስረድተዋል።

ታጣቂ ቡድኖቹ፤ ነጻ ለወጡት የግዳጅ ሠራተኞች ምግብ እንደሚያቀርቡ ኢትዮጵያውያኑ ተናግረዋል።

በመጀመሪያዎቹ ቀናት በቀን ሦስት ጊዜ ይቀርብ የነበረው ምግብ ባለፉት ቀናት ወደ ሁለት ዝቅ ማለቱንም አክለዋል።

በተጨናነቁ ክፍሎች ውስጥ ወለል ላይ የሚተኙት 450 ገደማ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች፤ ያሉት መጸዳጃ ቤቶች ሁለት ብቻ መሆናቸውን እና ባለፉት ቀናት ወረርሽኝ በሚመስል ሁኔታ ግቢው ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ የቆዳ በሽታ እየተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

“የቆዳ እብጠት፣ መላላጦች ዓይነት ‘ኢንፌክሽኖች’ ተፈጥረዋል። ይህ የተከሰተው በሚናደፉ እንደ ወባ ዓይነት ትንኝ፣ ቢንቢዎች እንደሆነ ራሳቸው ሰዎቹ ነግረውን ነበር። አሁን ግን ይህ ነገር እየከበደ መጣ። ልጆች ሰውነታቸው እያበጠ መጣ። ትናንት ራሱ ከ10 በላይ የሚሆኑ ልጆች ለሕክምና ተጭነው ሄደዋል” ሲል ሌላ ኢትዮጵያዊ ስለ ሁኔታው ገልጿል።

በተጨናነቀ የመጠለያ ክፍል ውስጥ ያሉ እና ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን የሆኑ ወንዶች ጨርቅ በተነጠፈበት ወለል ላይ ተኝተው

ኢትዮጵያውያኑ ያሉበት ሁኔታ የማያመች ቢሆንም ዋነኛ ስጋታቸው፣ ቀጣይ ሁኔታቸውን እርግጠኛ ሳይሆኑ ለረዘመ ጊዜ ከመቆየታቸው ጋር የተያያዘ ነው።

የግዳጅ ሠራተኞችን ከካምፖቹ ያስወጡት የ”ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” ሆነ “ቦርደር ጋርድ ፎርስ” ታጣቂዎች በእጃቸው ያሉትን የግዳጅ ሠራተኞች ወደ ታይላንድ የመላክ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይሁንና ከሁለት ሳምንት በፊት ከተላኩት የመጀመሪያዎቹ ተጎጂዎች በኋላ እስካሁን ድረስ ሌሎች የግዳጅ ሠራተኞች ወደ ታይላንድ አልተላኩም።

ኢትዮጵያውያኑ መቼ ወደ ታይላንድ እንደሚላኩ በመጠየቅ ለታጣቂ ቡድኖቹ የሚያቀርቡት ጥያቄ፤ “በቅርብ ትሄዳላችሁ፤ ጠብቁ” ከሚል መልስ ውጪ ግልፅ የሆነ ምላሽ እንዳላገኘ ይገልጻሉ።

ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያውያኑ ላይ “መልሰው ወደ ካምፑ ሊልኩን ይችላሉ” የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ከኢትዮጵያውያኑ አንዱ “የ DKBA ወታደሮች ከዚህ በፊትም ካምፑ ውስጥ ሰው ሲደበድቡ የነበሩ ናቸው። ምናልባት [ከካምፑ አለቆች ጋር] ተደራድረው ይመልሱን ይሆን ወይ የሚል ስጋት አለን። ጊዜ በሄደ ቁጥር ቻይናዎቹም [የካምፑ አለቆች] ተኝተው አያድሩም። እዚህ ያለው አብዛኛው ሰው ልምድ ያለው ነው። ለእነሱ ሀብት ነን፤ አንድ ሰው ለእነሱ ገንዘብ ነው” ሲል የስጋቱን ምንጭ አስረድቷል።

የቻይናውያኑ የካምፑ አለቆች የግዳጅ ሠራተኞቹ ወደ ተጠለሉበት ግቢ መጥተው መመልከቱን ስጋቱን እንደጨመረውም ተናግሯል።

ታጣቂ ቡድኖቹ በእጃቸው ላይ ያሉትን የግዳጅ ሠራተኞቹ ወደ ታይላንድ ላለመላካቸው በምክንያትነት የሚነሳው አንዱ ጉዳይ፤ ወደ አገሪቱ የገቡ ተጎጂዎችን ወደ አገራቸው ለመላክ የሚታየው መጓተት ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ታይላንድ ከገቡት ተጎጂዎች ሙሉ በሙሉ ወደ አገራቸው አልተሸኙም።

ከ19 አገራት ከተወጣጡት 261 ተጎጂዎች መካከል የሦስት የአፍሪካ አገራት ዜጎች እስካሁን ድረስ ወደ አገራቸው እንዳልተላኩ በታይላንድ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እነዚህ አገራት 138 ዜጎች ያሏት ኢትዮጵያ እንዲሁም በጣት የሚቆጠሩ ዜጎች ያሏቸው ኡጋንዳ እና ናይጄሪያ ናቸው።

“በፍጥነት ምላሽ የማይሰጠው” የኢትዮጵያ መንግሥት

ከሁለት ሳምንት በፊት 138 ኢትዮጵያውያን የግዳጅ ሠራተኞች ወደ ታይላንድ በገቡበት ወቅት፤በህንድ ኒው ደልሂ የሚገኘው እና ታይላንድን የሚሸፍነው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለ ጉዳዩ እንደሚያውቅ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ኤምባሲው፤ ቀደም ብሎ ለዚሁ ጉዳይ ከተቋቋመ “ብሔራዊ ኮሚቴ” እና ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያኑን እንደሚመልስም አስታውቆ ነበር።

ይኹን እንጂ አብዛኛዎቹ አገራት በኤምባሲዎቻቸው በኩል ዜጎቻቸውን ሲመልሱ እና የተቀሩትም መጥተው ሲጎበኙ፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ብቻ እስካሁን ዜጎቹን እንዳልጎበኘ እና እንዳልመለሰ የእርዳታ ድርጅት ምንጮች እና በታይላንድ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወታደራዊ ካምፕ ውት በሚገኝ አዳራሽ ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን መካከል ሁለቱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከኢትዮጵያውያን ውጪ ወደ አገራቸው ሳይመለሱ በመጠለያው ውስጥ የቀሩት አራት የኡጋንዳ እና አንድ ናይጄሪያ ዜጎች ናቸው።

ዜጎቻቸውን ወደ አገራቸው በፍጥነት የመለሱት አገራት በአብዛኛው ታይላንድ ውስጥ ኤምባሲ ያላቸው እንደሆነ የእርዳታ ድርጅት ምንጮች ተናግረዋል።

በአገሪቱ ኤምባሲ የሌላቸው ደግሞ በእርዳታ ድርጅቶች በኩል ዜጎቻቸውን ማስወጣት እንደቻሉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያውያኑን በተመለከተ ጥያቄ ሲቀርብለት የነበረው በሕንድ የሚገኘው ኤምባሲ፤ ዜጎቹን ለመመለስ “ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየሰራ” እንደሆነ እና “ከሚኒስቴሩ ምላሽ እየጠበቀ” መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱን ምንጮቹ ገልጸዋል።

አንድ ምንጭ፤ “ሲመስለኝ፤ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየወሰኑ ነበር። እንደ እኔ ሀሳብ ግን ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ምላሽ ለመስጠት የወሰደባቸው ጊዜ እጅግ ረዥም ነው” ብለዋል።

በሕንድ የሚገኘው ኤምባሲ ምላሽ ለመስጠት ቢዘገየም በመጪው እሁድ የካቲት 23/2017 ዓ.ም. ሁለት ኃላፊዎችን ወደ ታይላንድ ሊልክ እንደሆነ ማስታወቁን ምንጮቹ ተናግረዋል።

አዳራሽ ውስጥ ወለል ላይ የተዘረጉ መተኛዎች
የምስሉ መግለጫ,በታይላንድ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን እንዲያርፉ በተደረጉበት ሰፊ አዳራሽ ውስጥ የሚተኙት ወለል ላይ አንጥፈው ነው

“ሁለት ኃላፊዎች ወደ ታይላንድ መምጣት ጀምረዋል። እሁድ ይደርሳሉ። [ኃላፊዎቹ] የሚመጡት [ለኢትዮጵያውያኑ] የጉዞ ሰነድ ለመስጠት እና የራሳቸውን የአውሮፕላን ትኬት ለመቁረጥ መክፈል የሚችሉትን ከታይላንድ እንዲወጡ ለማገዝ እንደሆነ ተረድተናል።

“እንደምረዳው የራሳቸውን ትኬት መቁረጥ የሚችሉት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ስለዚህም ትኬት መቁረጥ ስለማይችሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ስጋት ገብቶናል” ሲሉ አንድ የእርዳታ ድርጅት ምንጭ ተናግረዋል።

ምንጮቹ እንደሚያስረዱት ዜጎቻቸውን ከታይላንድ ካስወጡ አገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ የተጎጂዎቹን የመመለሻ ትኬት ቆርጠዋል። የኢትዮጵያ ኤምባሲ እገዛ የሚያደርገው በራሳቸው ትኬት ለሚቆርጡት ዜጎች እንደሆነ መግለጹን ተከትሎ፤ ለሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በታይላንድ እና ከታይላንድ ውጪ ከሚገኙ አገራት በሚሰበሰበው ገንዘብ “ጊዜ ቢወስድም” ኢትዮጵያውያኑን ‘መመለስ ይቻላል’ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ቢቢሲ፤ ስለ ጉዳዩ ኒው ደልሂ ከሚገኘው ኤምባሲ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዛሬ አርብ የካቲት 21/2017 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከምያንማር ወደ ታይላንድ የተሻገሩ “246 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን” ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ለኢትዮጵያውያኑ “አስፈላጊውን የሰነድ ማጣራት እና የጉዞ ዝግጅት እየተከናወነ” እንደሆነ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንደተናገሩ ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስቴሩ እየተከናወነ እንደሆነ የጠቀሰው “የጉዞ ዝግጅት” የመመለሻ የአውሮፕላን ትኬትን ያካትት እንደሆነ በመረጃው ላይ አልጠቀሰም።

በታይላንድ የሚገኙት የእርዳታ ድርጅቶች፤ አሁን በአገሪቱ ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ትኬት ለመቁረጥ እንደሚችሉ ቢያምኑም፤ በምያንማር ታጣቂዎች እጅ ስለሚገኙ እና ወደ ታይላንድ ይላካሉ ተብለው ስለሚጠበቁት ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያን ስጋት ገብቷቸዋል።

“አሁንም ድረስ [ወደ ታይላንድ ለመምጣት] እየጠበቁ ስላሉት ብዙ ቁጥር ያላቸው [ኢትዮጵያውያን] እጅግ ስጋት ይገባኛል። ሁሉንም ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚጠይቀው የገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው” ሲሉ ምንጯ ስጋታቸውን አስረድተዋል።

ከምያንማር ታጣቂዎች እጅ ወጥተው ወደ ታይላንድ ለመምጣት በተስፋ እየተጠባበቁ ያሉት ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ስጋታቸው አይሎባቸዋል።

ከኢትዮጵያውያኑ አንዱ፤ “ይህንን ድንበር እስካልተሻገርን ድረስ ምንም ደህንነት አይሰማንም። ድጋሚ ወደዚያ ካምፕ ተመለስን ማለት በሕይወት የሚወጣ አንድ ሰው አይኖርም ማለት ነው” ሲል ፍርሃቱን ገልጿል።