የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

ከ 1 ሰአት በፊት

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አርብ፣ የካቲት 21/ 2017 ወደ ዋይት ሃውስ ሲያቀኑ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር መልካም ውይይት አደርጋለሁ በሚል መንፈስ ነበር።

ዩክሬን ብርቅዬ የሆነውን ማዕድኗን ለአሜሪካ በመስጠት በምላሹም የጸጥታ ዋስትና እንድታገኝ ቢያልሙም ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ያልታሰበ ሁኔታ ገጥሟቸዋል።

በዓለም መገናኛ ብዙኃን ፊት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ “ምስጋና ቢስ” የሚሉ ቃላትን ጨምሮ ተግሳጾች፣ በኃይለቃል የተሞላ ወቀሳ እንዲሁም ዘለፋዎችን ሰንዝረውባቸዋል።

ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ከአሜሪካ ባለስልጣናት ለቀረበላቸው ሃሳብ ዜሌንስኪ ጠንከር አድርገው ተቃውመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ትራምፕ እና ምክትላቸው “አክብሮት የጎደለው” ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።

ውይይቱ ሳይጠናቀቅ እንዲሁም በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት ከትራምፕ ጋር የዜና መግለጫ መስጠት ቢኖርባቸውም ዜሌንስኪ ከዋይት ሃውስ እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

ለሳምንት ያህል ሲሞገስ የነበረው የማዕድን ስምምነቱም ሳይፈረም ቀርቷል። “ለሰላም ዝግጁ ስትሆን ተመልሰህ ና” ሲሉም ትራምፕ የዜሌንስኪ መኪና ለቆ ከመውጣቱ በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።

በዚህ ዘለፋ በተሞላበት ውይይት የተለያዩ ነጥቦች ቢሰሙም አራቱን አንጥረን አውጥተናል።

የዜሌንስኪ እና ቫንስ ኃይለ ቃል የተሞላበት ምልልስ

በዋይት ሃውስ የነበረው የመጀመሪያው ግማሽ ሰዓት ውይይት ሰላማዊ ነበር። ሆኖም ቫንስ “ለሰላም እንዲሁም ለብልጽግና መንገዱ በዲፕሎማሲ መፍታት ነው” ካሉ በኋላ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ እያደረጉት ያሉት ይህንኑ ነው” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጣልቃ በመግባት ሩሲያ ወረራ ከመፈጸሟ ከሶስት ዓመታት በፊት ያልተሳካ የተኩስ አቁም ስምምነትን በማጣቀስ “ማንም አላስቆመውም” ሲሉም የሩሲያ አቻቸውን ቭላድሚር ፑቲንን ወቅሰዋል።

“ጄዲ ምን ዓይነት ዲፕሎማሲ ነው የምታወራው? ምን ማለትህ ነው?” ሲሉም ዘለንስኪ ጠየቁ።

የሁለቱ ባለስልጣናት ንግግር ውጥረት እንደተሞላበት ባሳየው በዚህ ቅጽበትም ቫንስ “የአገርህን ውድመት የሚያስቆመው ዲፕሎማሲ አይነት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።

በመቀጠልም ቫይስ ፕሬዚዳንቱ “አክብሮት የጎደለው” በሚል ዜሌንስኪን ዘልፈዋቸዋል።

ቫንስ እየተናገሩ የነበሩት ትራምፕ ጦርነቱን ለማቆም ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑን ጋር የተናጠል ውይይት በማድረግ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረቡትን ሃሳብ በመደገፍ ነው።

“ለወደፊቱ ምን ሊሰማን እንደሚችል አትነግረንም”

ቫንስ ዩክሬን ወታደሮችን ለመመልመል እንዲሁም ለብሔራዊ ግዳጅ እያቀረበችው ያለው ጥሪ ችግር ገጥሟታል ሲሉ በዚህ ወቅትም የዩክሬኑን መሪ አፋጠዋቸዋል። ዜሌንስኪም “በጦርነት ወቅት ሁሉም አገራት ችግር ያጋጥማቸዋል፤ እናንተም ጭምር። በመካከላችን ጥሩ ውቅያኖሶች ስላሏችሁ ላይሰማችሁ ይችላል። ነገር ግን ለወደፊት ይሰማችኋል” የሚል ምላሽ ሰጡ።

ይህ ዜሌንስኪ አስተያየት ትራምፕን ያበሳጨ ነበር። በዜሌንስኪ እና በምክትል ፕሬዚዳንቱ መካከል በነበረው የኃይለ ቃላት ልውውጥም ትራምፕ ገቡበት።

የዩክሬኑ መሪ ትራምፕ የጦርነቱን ጀማሪ ወይም ወራሪውን ማየት አልቻሉም የሚለውን የጠቆመ ነበር። እንዲሁም የትራምፕ አካሄድ የሩሲያን መገለል በማስቆም አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ መገፋፋት ፑቲንን ያደፋፍራል፤ በተጨማሪም አውሮፓን አዳክሞ ዩክሬንን የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋታል የሚለውን እሳቤ አንጸባርቋል።

ዜሌንስኪ የጦርነቱ መዘዝ በዩክሬን ብቻ እንደማይወሰን እና ወደ አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገራት እንደሚዳረስ በዚሁ ንግግራቸው ጠቆም አድርገዋል። ትራምፕ በዚህ የዜሌንስኪ ንግግር እሳት ሆነው “ለወደፊቱ ምን ሊሰማን እንደሚችል አንተ አትነግረንም። ይህንን መናገር የምትችልበት አቋም ላይ አይደለህም” ሲሉ በከፍተኛ ድምጽ ተናግረዋቸዋል።

አክለውም “በሚሊዮኖች ህይወት እየቆመርክ ነው” ሲሉ ገስጸዋቸዋል።

“ብቻህን አልነበርክም”

ዜሌንስኪ በንግራቸው መካከል “ከጦርነቱ ጅማሮ ጀምሮ ብቻችንን ነበር እናም እናመሰግናለን” ማለታቸው ትራምፕን በእጅጉ ያስቆጣ ነበር። ትራምፕ ከዚህ ቀደም ጦርነቱ የአሜሪካ ግብር ከፋዮች ሸክም ሆኗል በማለት በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ቆይተዋል።

“ብቻህን አልነበርክም። በዚህ ደደብ ፕሬዚዳንት [ባይደን] በኩል 350 ቢሊዮን ዶላር ሰጥተንሃል” አሉት።

ከዚያም ቫንስ በመቀጠል “በዚህ ሁሉ ወቅት አሜሪካን አመስግነሃል ወይ?” ሲል ዜሌንስኪን የጠያቃቸው ሲሆን በምርጫው ዘመቻ ወቅትም ተፎካካሪያቸውን ዲሞክራቶችን “ትደግፍ ነበር” ሲሉ ወቅሰውታል።

ዜሌንስኪ”ድምጽህን ከፍ አድርገህ ስለ ጦርነቱ ስላወራህ……..” እያሉ በሚናገርበት ወቅት ትራምፕ አቋርጠው “ጮክ ብሎ አልተናገረም። አገርህ ችግር ውስጥ ናት” ሲሉ በብስጭት መለሱ።

“እያሸነፍክ አይደለም። ከዚህ በጥሩ ሁኔታ ለመውጣት ያለንህ እድል እኛ ነን” ሲሉም በኃይለ ቃል መልሰዋል።

የትራምፕ እና ምክትላቸው ተግሳጽ

“በእንዲህ አይነት መንገድ ስምምነቶች ላይ ማድረግ ከባድ ነው። ባህርይህ መለወጥ አለበት” ሲሉ ትራምፕ ዜሌንስኪን ለመገሰጽ ሞክረዋል።

በዜሌንስኪ “ባህርይ” የተናደዱ የመሰሉት ፕሬዚዳንቱ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለመዝለፍ፣ ለማሸማቀቅና ለመገሰጽ ሞክረዋል።

ቫንስ “አመሰግናለሁ ብቻ በል” ሲልም የዩክሬኑን መሪ አዘውታል።

ዜሌንስኪ አቋማቸውን ለማስረዳት እንዲሁም መረጃዎች እንዳይጣረሱ ለማስተካካል ሲሞክሩም ታይተዋል።

ከዋናው ካሜራ ውጭ በአሜሪካ የዩክሬን አምባሳደር ኦክሳና ማርካሮቫ በዚህ ውርጅብኝ ተደናግጠው ጭንቅላታቸውን በእጃቸው ይዘው ታይተዋል።