
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዘለፋ ጭምር የተቀላቀለበት በኃይለ ቃል የተሞላ ውይይት በዋይት ሐውስ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ዜሌንስኪን “አክብሮት የጎደለው” እንዲሁም “በሦስተኛው የዓለም ጦርነት ቁማር እየተጫወትክ ነው” ሲሉ ገስጸዋቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ካለበለዚያ ግን “እኛ እንወጣበታለን” ሲሉም ትዕዛዝ በተሞላበት መልኩ ነግረዋቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች የማዕድን ውል ለመፈራረም ተይዞ በነበረው ውይይት በዓለማችን መገናኛ ብዙኃን ፊት አንዳቸው፣ አንዳቸውን በተደጋጋሚ ሲያቋርጡ ታይተዋል።
ትራምፕ ለጦርነቱ ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ከሩሲያ ጋር የተናጠል ውይይት ማካሄዳቸውን ተከትሎ ከዩክሬን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻክሯል።
መሪዎቹ ይደርሱበታል የተባለው ስምምነት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያሻሽላል የሚል ተስፋን ፈጥሮ ነበር።
ነገር ግን ዜሌንስኪ ስምምነቱን ከመፈረማቸው በፊት በአሜሪካውያን ባለሥልጣናት እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል።
በዚህ ተግሳጽ በተሞላበት ውይይታቸው ትራምፕ፣ አሜሪካ ለዩክሬን ላደረገችው ወታደራዊ እና ፓለቲካዊ ድጋፍ “ምስጋና ቢስ ነህ” እንዲሁም “ከሦስተኛው የዓለም ጦርነት ጋር ቁማር እየተጫወትክ ነው” በማለት ወቅሰዋቸዋል።
ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ማመቻመች አይገባም ብለው ቢከራከሩም፤ ትራምፕ በበኩላቸው የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ማድረግ የሚገባቸውን መፈጸም እንዳለባቸው ነግረዋቸዋል።
- ትራምፕ በቅርቡ አምባገነን ያሏቸውን ዘለንስኪን “ጀግና” ሲሉ አወደሱ28 የካቲት 2025
- የትራምፕ ‘የወርቅ ካርድ ቪዛ’ ምንድን ነው? በዓለማችን ሌሎች ተመሳሳይ ቪዛዎች አሉ?28 የካቲት 2025
- ከምያንማር የወንጀል ካምፖች የወጡ ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ታጣቂዎች እጅ ይገኛሉ28 የካቲት 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነቱን በመጀመር ዜሌንስኪን ወንጅለው እንዲሁም “ድርድር ላይ ቀደም ብሎ መድረስ ይችል ነበር” ሲሉ ከዚህ ቀደም ወቅሰዋቸዋል።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ የዩክሬንን ተፈጥሯዊ ጋዝ፣ ነዳጅ እና ብርቅዬ ማዕድናት ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ላይ ለመድረስ ነበር አርብ ዕለት ሁለቱ መሪዎች በዋይት ሐውስ የተገናኙት።
ከውይይታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ትራምፕ ለዩክሬን መሪ “ትልቅ ክብር” እንዳላቸው በመግለጽ ለስለስ ያሉ መስለው ነበር።
ነገር ግን ከትራምፕ ጋር አብረው ከነበሩት መካከል የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ጦርነቱ በዲፕሎማሲ መቋጨት እንዳለበት ለዜሌንስኪ በትዕዛዝ መልክ መናገራቸውን ተከትሎ ውይይቱ ሲካረር ታይቷል።
ዜሌንስኪ በአውሮፓውያኑ 2019 የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በማጣቀስ “ምን ዓይነት ዲፕሎማሲ?” በማለት ሲጠይቁ ታይተዋል።
ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከመፈጸሟ ከሦስት ዓመታት በፊት ትደግፋቸው የነበሩ የዩክሬን ተገንጣዮችን በተመለከተ የተደረሰ ነበር።
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪን “አክብሮት የለህም” በማለት በመገናኛ ብዙኃን ፊት ወርፈዋቸዋል።
ከዚያም በኋላ ውይይቱ ሙግት እና ኃይለ ቃል የተሞላበት ሲሆን፣ ትራምፕ እና ምክትላቸው አገራቸው ለሦስት ዓመታት ላደረግችላቸው ድጋፍ ምስጋና አላቀረቡም እንዲሁም ዜሌንስኪ አሜሪካ ምን ማድረግ እንዳለባት መናገር የሚችሉበት አቋም ላይ አይደሉም ብለዋቸዋል።
ውይይቱን ሳይጨርሱ እንዲሁም ከተቃደው መርሃ ግብር ቀደም ብሎ ዜሌንስኪ በመኪናቸው ከዋይት ሐውስ ሲወጡ ታይተዋል።
ትራምፕ ከዚህ ውይይት በኋላም “ዜሌንስኪ አሜሪካን በተከበረው ቢሯዋ አዋርዷታል” ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ጽፈዋል።
“ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ አሜሪካ የምትሳተፍበት ከሆነ ለሰላም ዝግጁ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ። የእኛ ተሳትፎ በድርድሩ ላይ ለእሱ ጥቅም እንደሚያስገኝለት ይሰማዋል። እኔ ጥቅም አልፈልግም። ሰላም እፈልጋለሁ” ብለዋል።