
ከ 5 ሰአት በፊት
መሳይ ‘ድሮ’ ሰፈር ውስጥ ኳስ ስትጫወት አያያዟን ያላለደነቀ፤ “ይህቺ ልጅ ትልቅ ቦታ ትደርሳለች” ያላለ አልነበረም።
በትምህርት ቤት ጨዋታዎች “ድንቅ” እግር ኳሰኛ እንደሆነች ለማስመስከርም ጊዜ አልፈጀባትም። ኳስ ከመግፋት እና ከመለጋት ያለፈው ‘የእግር ኳስ ጥበቧ’ በፍጥነት ወደ ትልቅ መድረኮች ወስዷታል።
ከትምህርት ቤት ወረዳ፣ ከወረዳ ዞን፣ ከዞን ክልልን ወክላ ለመጨዋት የወሰደባት “በጣም አጭር” ጊዜ ነበር።
በአጭር ጊዜ ውስጥ “ፕሮፌሽናል” እግር ኳስ ተጫዋች ሆና የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ ተጫውታለች። በተመሳሳይ ፍጥነት ነገሮች ተቀያይረው ከምትወደው እግር ኳስ ጋር ተለያየች እንጂ።
የቀድሞዋ “ፕሮፌሽናል” ተጫዋች አሁን “የተገኘውን” ሥራ ትሠራለች።
ታዲያ ነገሮች እንዴት በዚህ ፍጥነት ተቀየሩ?
ሆሳዕና ከተማ የተወለደችው መሳይ ተመስገን “ከዕድሜዬ አብዛኛው ያለፈው በኳስ ነው” ትላለች።
በ2006 አርባ ምንጭ ላይ በተካሄደው የመላው ደቡብ ጨዋታዎች ላይ መሳይን ያካተተው የሆሳዕና ዞን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተሳታፊ ነበረች።
ይህ ውድድር ለመሳይ ብዙ ዕድል ከፈተ።
በወቅቱ የሀዋሳ ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ይዞ ወደ ቦታው ያቀናው አሠልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የመሳይ “ኳስ አያያዝ” ተስፋ የሚጣልበት እንደሆነ በማመኑ ለሚያሠለጥነው ክለብ እንድትፈርም ወሰነ።
መሳይ አሠልጣኝ ዮሴፍ ትልቁ ባለውለታዋ እንደሆነ ትናገራለች።
ይህም ብቻ አይደለም። በዚህ ወድድር ያሳየችው ብቃት ደቡብ ክልልን ወክላ ባሕር ዳር ለሚደረግ የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እንድትመረጥ አደረጋት።
መሳይ በአጥቂነት የተሳተፈችበት የደቡብ ክልል ሴቶች ቡድን ውድድሩን አሸንፏል። በዚህ ውድድር መሳይ ኮከብ ተጨዋች ሆና ያጠናቀቀችበት ጨዋታዎች ነበሩ።
መሳይ ስለዚህ ውድድር ስትናገር “ብዙ የተሻሉ ነገሮችን አይቼበታለሁ። ልምዶችን አግኝቼበታለሁ። ብዙ እንዳለኝ የተረዳሁበት ውድድር ነበር ራሴን በፕሮፌሽናል ደረጃ ማሰብ የጀመርኩት ከዚያ በኋላ ነው” ትላለች።

ከዚህ ውድድር በኋላ መሳይ ተፈላጊነቷ ጨመረ። በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች እንድትፈርምላቸው ጠየቋት።
‘ፈርሚልን ካሏት’ ክለቦች መካከል ሐዋሳ ከነማ እና ሲዳማ ቡና ይገኙበታል። መሳይ በተመሳሳይ ወቀት ለሁለቱም ክለብ ፈረመች።
ይህንን ያደረኩት “ባለማወቅ” ነው ብትልም ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ ለሁለት ዓመት እንዳትጫወት ተቀጥታለች።
ሐዋሳ ከነማ ይግባኝ ጠይቆ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ወደ እግር ኳሱ ተመለሰች።
መሳይ ያኔ በሴቶች እግር ኳስ ጥሩ በሚባል ክፍያ ነበር የፈረመችው።
“በማገኘው ደሞዝ ቤተሰብን የምረዳው እኔ ነበርኩ። አባቴ ከእኛ ጋር አይደለም። እናቴን የምረዳው እኔ ነኝ” ትለለች።
በሁለት ዓመት ቆይታዋ መሳይን በአጥቂነት የያዘው ሐዋሳ ከነማ የኢትዮጵያ የሴቶች ጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቷል።
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆና ጨርሳለች። በተደጋጋሚ የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።
በኮቪድ-19 ወረረሽኝ ምክንያት የተቋረጠው የ2012 የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበረች።
ይህ የመሳይ የስኬት ጉዞ ግን ፈተና ገጠመው።
” ‘ፆታዋ ልክ አይደለም’ ተባልኩ”
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በሐዋሳ ከነማ ውስጥ ውጤታማ ጊዜ እያሳለፈች የነበረችው መሳይ ቅሬታ ቀረበባት። “የመሳይ ፆታ ልክ አይደለም” በማለት የፕሪሚየር ሊጉ አሠልጣኞች ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ አቀረቡ።
በዚህ ምክንያት መሳይ “መመርመር” አለባት ተባለ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ደብዳቤ ጻፈ። ደብዳቤው መሳይ “እንድትመረመር” የሚጠይቅ ነው።
“ምርመራ አደረኩ። ውጤቱም ‘መጫወት ትችያለሽ’ የሚል ነበር። ውጤቱ ለፌዴሬሽኑ ተላከ። ፌዴሬሽኑ እንድጫወት ፈቀደ” ስትል ትገልጻለች።
ጉዳዩን አስመልክቶ ቢቢሲ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስፖርት ሕክምና ክፍልን አነጋግሯል።
ይህ ክፍል በመስከረም 2015 እንደተቋቋመ የገለጹት የህክምና ክፍሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ ስለጉዳዩ ሲናገሩ ” [ቀደም ብሎ] የተጀመረ ነገር እንዳለ አውቃለሁ። ግን የተገቢነት ምርመራ ውሳኔው እና ሪፖርት እጄ አልደረሰም” ብለዋል።
የሆነው ሆኖ መሳይ በዚያ ዓመት ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመለሰች።
የወድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ የመከላከያ የሴቶች እግር ኳስን ቡድን መሳይን አስፈረመ።
ከቀጣዩ ውድድር ዘመን በፊት ባለው ጊዜ ወደ ትውልድ ከተማዋ ሆሳዕና ተመለሰች።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከእሷ ጋር ለመከላከያ የፈረሙ ሌሎች ሁለት ሴት ተጫዋቾች ደመወዝ መግባቱን የሚገልጽ የጽሁፍ መልዕክት ደረሳቸው።
መሳይ ጋር ይህ መልዕክት አልመጣም። ጠበቀች። የተለወጠ ነገር የለም።
“ደመወዝ አልገባልኝም ብዬ ስደውል። ፌዴሬሽኑ ‘የእሷን ውል አናጸድቅም ብሏል’ አሉኝ። ከባድ ነበር አስደንግጦኛል” ስትል ሁኔታዎችን ታስታውሳለች።
ሁለተኛ ምርማራ ማድረግ አለብሽ ተባለች።
“አንድ ሰው ላይ ሁለት ጊዜ ምርመራ ይደረግ መባሉ” ተገቢ እንዳልሆነ የምትገልጸው መሳይ በውሳኔው ቅር ብትሰኝም ለምርመራው ተስማማች።
“እኔ ፈልጌ የመጣሁት ነገር የለም። የምደብቀው ነገር ስለልሆነ ለሁለተኛ ጊዜ ምርመራ ሲሉኝ ‘እሺ’ ነው ያልኳቸው” ትላለች።
“መጀመሪያ ላይ ወንድ ናት ብለውኝ ነው የመረመሩኝ። ድጋሚ የፌዴሬሽኑ ዶክተሮች መርምረው ሆርሞንሽ መስተካከል አለበት አሉኝ።”
መሳይ መስተካካል አለበት ስለተባለው ሆርሞን ምንነት፣ በምን ያህል መጠን? ወይም በአጠቃላይ ስለ ሆርሞኑ ዝርዝር መረጃው የላትም።
ሆኖም ከ6 ወር በላይ ይፈጃል የተባለውን “የሆርሞን ሕክምና” ለማድረግ ፈተና ገጠማት።
ለዚህ ሕክምና በሐኪም በተደጋጋሚ በሚሰጣት ቀጠሮ ምክንያት አዲስ አበባ መመላለስ ነበረበት።
- ‘ሁለቱንም ፆታ ይዤ በመፈጠሬ መገለል እና ፆታዊ ጥቃት ደርሶብኛል’10 ታህሳስ 2024
- በአልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ ኢማኔ ኸሊፍ ላይ የተነሳው ውዝግብ ምክንያቱ ምንድን ነው?4 ነሐሴ 2024
- “በፆታዋ ምክንያት” በማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሪያ የሆነችው ቦክሰኛ ኢማን ኼሊፍ ተጋጣሚዋን በ46 ሰከንድ አሸነፈች2 ነሐሴ 2024

“በጣም ብዙ ወጪ አወጣሁ። እጄ ላይ የነበረውን ብር ምንም ጥቅም ላላገኝበት ጨረስኩት። ምርምራ በሚል ከሆሳዕና አዲስ አበባ እየተመላለስኩ ነበር። [አዲስ አበባ] ዘመድ የለኝም። ቤተሰብ የለኝም። አልጋ እየያዝኩ ነበር የምቆየው። በጣም ብዙ ነገሮቸን አሳለፍኩኝ። ከአቅሜ በላይ ሲሆን፣ የሚረዳኝ ሳጣ ምርመራውን አቆምኩ። ከዚያ ሰፈር ላይ ወደማገኘው ሥራ ተመልስኩ” ትላለች።
“ፌዴሬሽኑ ያገዘኝ ነገር የለም። አጠገቤ የነበረ ሰው የለም” ስትል አክላለች።
መሳይ በበቂ ሁኔታ መረጃ እንዳልተሰጣት እና በግልጽ ባልተነገረ መንገድ ከእግር ኳስ እንደተሰናበተች ትናገራለች።
የመጀመሪያውን የምርመራ ውጤት እንኳን ማግኘት አልቻለችም።
“ውጤቱ ፌዴሬሽን እና ሐዋሳ ከነማ ጋር አለ። ሌላ ክለብ ልትሄድ ነው የሚባል ነገር ስለነበር ሀዋሳ ከነማ የምርመራውን ውጤት አልሰጡኝም” ትላለች።
ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት በተመረጠችበት ጊዜ የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ምርመራ ማድረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።
ተጫዋቿ ቀደም ብላ ምርመራ አድርጋ የመጫወት ፍቃድ ካገኘች በኋላ ዳግም እንድትመረመር ለምን ተደረገ? ስንል የጠየቅናቸው ዶ/ር ሳሙኤል ሲመልሱ፡ “ከዚያ በፊት ምርመራ ኖረ አልኖረ የሚለው ጥያቄ አይሆንም። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥር በሚደረግ ውድድር ሥር ያለች ማንኛዋም ሴት ተጫዋች ለሴቶች እግር ኳስ ፍትሃዊነት እና ተገቢነት ፖሊሲ ተገዢ ስለሆነች በማንኛውም ሰዓት ምርመራውን ማድረግ ስለምንችል፣ ምርመራውን አደርገናል። የምርመራው ውጤትም ዛሬ ሌላ ነገ ሌላ የሚሆንበት መንገድም የለም” ሲሉ መልሰዋል።
ኃላፊው የፌዴሬሽኑ የተገቢነት ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረገ ነው ሲሉም ይገልጻሉ።
“ማንንም ‘ሰው ሴት ነሽ፣ ወንድ ነህ’ ብለን የምንወስንብት ምንም ዓይንት መሠረት የለንም” የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የሆርሞን እና የክሮሞዞም መጠን እንዲሁም ውስጣዊ የሰውነት መዋቅርን (internal structure) የተመለከቱ መስፈርቶች መሟላት እንዳለባቸው ያነሳሉ።
“ይህንን አሟልተው ወደ ውድድር የሚመለሱበት መንገድ አስቀምጠናል” የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል ከዚህ አኳያ መሳይ “ያላሟቻቸው ጉዳዮች አሉ” ሲሉ ገልጸዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል መሳይ በደፈናው “ያላሟላቻቸው ጉዳዮች አሉ” ከማለት በዘለለ “የሕክምና ውጤቶች በምሥጢራዊነት ከመያዛቸው አንጻር” ዝርዝሩን መናገር እንደማይችሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ፌዴሬሽኑም የዚህን ምርመራ ወጪ የመሸፈን ኃላፊነት የለበትም ብለዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል ከፆታ ጋር ያሉ ቅሬታዎች በዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ሊታይ እንደሚችል ይገልጻሉ።
በስፖርት ዘርፍ ዕልባት ያላገኘው የፆታ ዕድገት ልዩነት
ይህ ጉዳይ በመሳይ ላይ ብቻ ያጋጠመ አይደለም። በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በርካታ ስፖርተኞች በፆታ ምክንያት ችግር ውስጥ ይገባሉ።
ለዚህም በአንድ ኦሊምፒክ የሁለት ወርቅ ሜዳልያ ባለቤት የሆነችው ደቡብ አፍሪካዊቷ የ800 ሜትር አትሌት ካስተር ሴሜኒያ ተጠቃሽ ናት።
በአውሮፓውያኑ 2017 ሴሜኒያ “ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ብልጫ ለማግኘት” የሚያስችላት ከፍ ያለ ተፈጥሯዊ ቴስቴስትሮን አላት ሲል ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።
አትሌቷ ግን ይህን አትቀበለም።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ በሴቶች የቦክስ ውድድር ተሳታፊ የነበሩት አልጄሪያዊቷ ኢማኒ ኻሊፍ እና ታይዋንን የወከለችው ሊን ዩ ቲንግም ከዚህ ጉዳይ ጋር ስማቸው ተያይዞ ሲነሳ ቆይቷል።
የፆታ ዕድገት ልዩነት (differences of sex development/DSD) ያላቸው ሰዎች፤ ብዙውን ጊዜ ወንድ ወይም ሴት ተብሎ በግልጽ ፆታን ለመበየን የሚያስችሉ መገለጫዎች አይኖሯቸውም።
በዚህ ዓይነት ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ሰዎች በዘረመል፣ ቴስቴስትሮን፣ በክሮሞዞም፣ በሆርሞን እና በመራቢያ አካላት ላይ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል።
ታዲያ የፆታ ዕድገት ልዩነት ያላቸው ሰዎች በስፖርት ውስጥ ከሌሎች ከፍ ያለ ብልጫ (advantage ) አላቸው ወይ? የሚለው ጥያቄ በተመራማሪዎች መካከል እንኳን አንድ ቁርጥ ያለ መልስ የለውም። አንዳንዶች በዚህ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ሴቶች የአካላዊ ጥንካሬ ብልጫ ሊኖራቸው እንደሚችል ይከራከራሉ።

በአንድ ወቅት የፆታ ዕድገት ልዩነትን በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በማንችስተር ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ኢንስቲትዩት የዘረመል ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አሉን ዊሊያምስ የዋይ [Y] ክሮሞዞም መኖር ብቻ አንድን ሰው ሴት ወይም ወንድ ለማለት በቂ አይደለም ይላሉ።
በዋና ዋና የስፖርት ዘርፎች የሞሎኪውል ዘረመል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሻኔ ሄፈርማን የተለየ የፆታ ዕድገት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ላይ ጥናት እየሠሩ ይገኛሉ።
ታዲያ ይህ ዓይነት ተፈጥሮ ያላቸው ሰዎች በሙሉ በአንድ ዓይነት ዕይታ መመዘናቸው ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ እያንዳንዱ የፆታ ዕድገት ልዩነት ያለው ሰው የራሱ ልዩ ሁኔታ እንዳለው ያስረዳሉ።
ምሳሌ ሲጠቅሱ አንድሮጅን ኢንሴንሲቲቪቲ ሲንድሮም (Androgen Insensitivity Syndrome) የሚባል የፆታ ዕድገት ልዩነት ያላት ሴት በአብዛኛው የወንዶች መገለጫ የሆነ ኤክስዋይ [XY] ክሮሞዞም እንደምትይዝ ይገልጻሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን ከሴቶች ከፍ ያለ ቴስቶስትሮን ታመነጫለች። ሆኖም ሰውነቷ ይህንን ማቀነባበር አይችልም። ስለዚህ ከሌሎች ሴቶች የተለየ ወይም የበለጠ የሚያስገኝላት ምንም ዓይነት ጥቅም እንደሌለ ያክላሉ።
ይህም ለውድድር ተገቢነት የሚቀመጠው መስፈርቶች ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ቀጥለው ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ለተሳታፊነት ያስቀመጣቸው መስፈርቶች አሁን ባለው በረቀቀው ሳይንስ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም ይላሉ። ለዚህ ነው ይህ መስፈርት ዳግም እንዲጤን ከሚጠይቁ በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ የሚሉት።
ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባወጣው የፆታ ዕድገት ልዩነት መመሪያ ላይ ተመርኩዞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተመሳሳይ መመሪያ አዘጋጅቷል። በዚህ መመሪያ መሠረት መሳይ መስፈርቶቹን እንደምታሟላ ተገልጿል።
ሆኖም ተጨዋቿ በምርመራ ስለተደረሰበት ግኝት በቂ ገለጻ እንዳልተደረገላት እና የምርመራው ውጤትም እጇ ላይ እንደሌለ ታነሳለች።
“ህልሜ ትልቅ ነበር”
መሳይ በውድድሮች በምትሳተፉበት ጊዜ ዘለፋዎች ይደርሱባታል። “ይህ ነገር [መጀመሪያ ለውድድር ከሄደችበት] ከአርባ ምንጭ ጀምሮ የነበረ ነው” ትላለች።
“አንዳንድ ነገሮች እላፊ ሲሆኑ ይከፋኛል። አንዳንዱ ራሴ እንዳመጣሁት እና እንደ መጥፎ ፍጥረት የሚያየኝ አለ። ጭንቅላት የሚነካ ንግግር የሚናገሩ አሉ” የምትለው መሳይ “ፈጣሪ ፈቅዶ ነው የፈጠረኝ ብዬ ስለማሰብ ነገሮችን ቀለል አደርጌ ነበር የማልፋቸው” ስትል ጨምራለች።
ለመላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር ወደ ባሕር ዳር በተጓዘችበት ወቅት የገጠማትን አትዘነጋውም።
“ይኼማ ወንድ ነው ብለው ሙሉ ደጋፊው ከትሪቡን ወርዶ ከበበኝ። ያ የመጀመሪያዬ ስለነበር ትንሽ አስደንግጦኛል። ግን እየተሳደቡ ትቻቸው ወጣሁ” ትላለች።
በአፍሪካ አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጀ የእሷን ዓይነት ተፈጥሮ ያላቻው ሴቶችን ስትመለከት ‘እኔም ተስፋ አለኝ’ ትላለች።
በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ከሎዛ አበራ ጋር ለአጭር ጊዜ የመጫወት ዕድል የነበራት መሳይ፣ እሷ የደረሰችበት ደረጃ የመድረስ ምኞት አላት።
“ህልሜ ትልቅ ነበር። ሙሉ ሕይወቴ ፈተና ነው” የምትለው መሳይ አሁንም “መታገል” እና ወደ እግር ኳስ መመለስ ትልቁ ምኞቷ ነው።
ትልቁ ችግር ግን በምን መልኩ “መታገል” እንዳለባት አታወቅም። መንገድ የሚያሳያት፣ አቅጣጫ የሚመራት ሰው የለም።
ለዚህ ነው ህልሟን እርግፍ አድርጋ ትታ በተወለደችበት ከተማ መናኸሪያ ውስጥ ዕቃ ማውረድ እና መጫን ላይ የተሠማራችው።
“በእግር ኳስ የቆየሁት አጭር ጊዜ ቢሆንም ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ። አሁን ላይ ያለው የሴቶች እግር ኳስ እኔ ከነበርኩበት ጊዜ አንጻር የተሻለ ነው። በእግር ኳስ ብቀጥል ኖሮ ጥሩ ደረጃ እደርስ ነበር” ትላለች።