በዓለም በርካታ አስም ያለባቸው ሕፃናት ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ እየተሰቃዩ ነው

ማኅበራዊ ሕፃናት የሚፈተኑበት የመተንፈሻ አካል በሽታ

ታደሰ ገብረማርያም

ቀን: March 2, 2025

ከባድ የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች ከአምስት ዓመት በታች ለሚገኙ ሕፃናት ሕመምና ሞት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥና ብክለት ጋር ተያይዞ አሁንም ዋና የማኅበረሰብ ጤና ችግር በሆኑት የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች፣ በዓለም 7.6 ሚሊዮን ሕፃናት አምስት ዓመታቸውን ከማክበራቸው በፊት እንደሚሞቱ የናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ሔልዝ መረጃ ያሳያል፡፡

በሕፃናት ላይ ኢንፍሉዌንዛ፣ ማስነጠስ፣ የንጥፍ  መዝረክረክና ትኩሳት ያለው የተለመደው ጉንፋን፣ አስም፣ ብሮንካይትስ፣ የጉሮሮ ሕመም፣ ኒሞኒያ (የሳንባ ምች) እና ሌሎችም የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቁ በሽታዎች በተለይ ለሕፃናት ሞት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከአምስት ዓመት በታች ካሉ ሕፃናት 15 በመቶ የሆነው ሞት የሚከሰተው ደግሞ በኒሞኒያ ነው፡፡

እነዚህ የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች ታዲያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየተባባሱ ይገኛሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥና የመተንፈሻ አካል ጤናን አስመልክቶ ስቶፕ ኒሞኒያ የግሎባል በርደን ኦፍ ዲሲዝ 2021 መረጃን ጠቅሶ በድረ ገጹ እንዳሠፈረው፣ በአየር ብክለት ምክንያት በመተንፈሻ አካል ሕመም 2.8 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 1.8 ሚሊዮን ያህሉ በሳምባ በሽታ (Pulmonary Disease) 650 ሺሕ በኒሞኒያ እንዲሁም 370 ሺሕ ከሳንባ ካንሰር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ሞት ከቀዳሚዎቹ አንዱ ኒሞኒያ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጡም በጤና እክሎች በተለይም በሳምባና ሳምባ ነክ፣ በእናቶችና በሕፃናት ሕመሞች፣ በተላላፊና ውኃ ወለድ በሽታዎች፣ በሜኔንጃይትስና በአየር ብክለት እንዲሁም በመተንፈሻ አካል ሕመም ላይ ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር ለሞት የሚዳርገውም መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡

የሳምባና የሳምባ ነክ ሕመሞች ደግሞ ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ተላላፊ ሕመሞች ቲቢ፣ የሳንባ ምችና ኢንፌክሽኖች ሲሆኑ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ደግሞ አስምና የአየር ቧንቧ ሕመም ናቸው፡፡

የሕፃናት፣ የሳምባና የፅኑ ሕሙማን ሰብ-እስፔሻሊስት ሐኪምና የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ራሔል አርጋው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የሙቀት መጠን ተላላፊ ሕመሞች እንዲባባሱ፣ ኢንፌክሽኖችም እንዲበዙ እያደረገ ነው፡፡

ሕፃናት ከልጅነታቸው ጀምሮ ለአየር ብክለት ተጋላጭ ሆነው ካደጉ የሳንባ ዕድገታቸው ላይ ጫና ከማሳረፉም ባሻገር፣ ካደጉም በኋላ የአስምና የአየር ቧንቧ ተጠቂ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ቀደም ሲል ተጠቂ የነበሩትን ደግሞ እንዲባባስባቸውና የሞት ምጣኔው ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡

‹‹የአየር ንብረት ለውጥ በጤና እክል ላይ የሚያሳድረው ጫና›› በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ቶራሲክ (THORACIC) ሶሳይቲ አሥራ አንደኛው ዓመታዊ ጉባዔ የተከናወነበትን ሥነ ሥርዓት አስመልክተው ራሔል (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳብራሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሚገኙና የማኅበሩ አባላት በሆኑ ኤክፐርቶች አማካይነት በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት የአየር ብክለቱ የአስም ተጠቂ በሆኑ ሕፃናት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ ተረጋግጧል፡፡

በውጭ አገር የተካሄደ ሌላው ተመሳሳይ ጥናት ደግሞ የአስም ሕመም ያለባቸው ሰዎች ብክለቱ ለሚያሳድረው ጫና በ26 በመቶ ተጠቂ መሆናቸውን ራሔል (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ብክለት በሕፃናት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ያሉት ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ እንደ ኢንጂነሯ፣ የአየር ብክለቱ የመተንፈሻ አካል ችግር በመፍጠሩ ሕፃናትን ለሞት እየዳረገ ነው፡፡

እነዚህንና ሌሎችም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እክሎች ለመግታት ባለሥልጣኑ ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

የአየር ብክለትን የሚያስከትሉ ኢንዱስትሪዎች፣ የተሽከርካሪ ጭሶችና ማገዶዎች በተቻለ መጠን እንዲቀንሱ የግንዛቤ ሥራ እየተሠራና በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡