

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ6,500 በላይ የመድኃኒት ዕፀዋት 887 ተመዝግበው ይገኛሉ
ማኅበራዊ ትኩረት የሚሹት ለመድኃኒት የሚውሉ ዕፀዋት
ቀን: March 2, 2025
ኢትዮጵያ ከ6,500 በላይ ብርቅዬ የሚባሉ የዕፀዋት ዓይነቶች እንዳሏት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ዕፀዋቶች ለምግብነት፣ ለመድኃኒት ቅመማና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሲኖሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቅማቸው በውል ሳይታወቅ ለምግብም ሆነ ለመድኃኒት፣ ለማገዶም ሆነ ለቤት መሥሪያ ሳይውሉ እንዲሁ አርጅተው በስብሰው ይቀራሉ፡፡
በተለይ ደግሞ ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ዕፀዋት በአካባቢ መራቆት፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያደርሰው ጫና፣ ከተማን በማስፋፋት፣ በደኖች ለኢንዱስትሪ መመንጠርና በተለያዩ ምክንያቶች ተጎድተዋል፡፡ በመሆኑም ዕፀዋቱ እንዲያገግሙና ዝርያቸው እንዳይጠፋ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
በብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የመድኃኒት ዕፀዋት ዴስክ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ውቤ ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ መድኃኒት የሚሆኑ ፅፀዋት አሉባቸው ተብለው የተለዩ ደኖች ላለፉት አሥር ዓመታት በፕሮጀክት ታቅፈው ቁጥጥርና ክትትል ሲደረግባቸው ቆይተዋል፡፡
በአገሪቱ ያሉ ለመድኃኒትና ለተለያዩ ምርምሮች የሚያገለግሉ ዕፀዋት ዝርያቸው እንዳይጠፋ ዘራቸውን በመሰብሰብ የተለያዩ ምርምሮች ሲደረጉም ነበር፡፡
በተለይ ዝርያቸው ለመጥፋት የተቃረቡ ዕፀዋትን ከተለያዩ አካባቢዎች በማሰባሰብ፣ ወደ አንድ ማዕከል በማምጣትና ዕፀዋቱ ባሉበት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመወያየት ዝርያቸው እንዳይጠፋ ሲንከባከቡ እንደነበር አቶ ሲሳይ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ድርቅን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ፈተና ሆነውባቸዋል፡፡
ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፀዋትን ለማባዛትና ዝርያቸውን ከመጥፋት ለመታደግ ሁለት ዓይነት የደን አጠባበቅ ዘዴዎችን እንደሚከተሉ የተናገሩት አቶ ሲሳይ፣ የመጀመሪያው ዕፀዋቱ የነበሩበትን አካባቢ ሳይለቁ ባሉበት ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ሲሆን፣ ዘራቸውን በማሰባሰብ የአየር ሁኔታው ምቹ ወደ ሆነ አካባቢ በማንቀሳቀስና በችግኝ መልክ በማፍላት በአቅራቢያው ላሉ ሰዎችና ለባህል መድኃኒት ቀማሚዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው የአጠባበቅ ዘዴ ነው ይላሉ፡፡
ነገር ግን ቀደም ሲል ለተከታታይ አሥር ዓመታት፣ ለመድኃኒት አገልግሎት የሚውሉ ዕፀዋትን ጨምሮ ሌሎች ዝርያቸው ሊጠፉ የተቃረቡ ዕፀዋትን ትኩረት ሰጥተው ሲተገብሯቸው የነበሩ ሥራዎች ተቀዛቅዘዋል፡፡
በሁለት ዙር ለተከታታይ አሥር ዓመታት ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ የተለያዩ የምርምር ማዕከላትን በማቋቋም ሲሠሩ መቆየታቸውን የሚያስረዱት አቶ ሲሳይ በዘጌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ፣ በሐረሪ፣ በጂንካና በሌሎች ሰባት ማዕከላት በዋናነት ሲሠሩባቸው የነበሩ ማዕከላት በአሁኑ ወቅት በበጀት እጥረት ምክንያት መቀዛቀዛቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ላለፉት ሦስት ዓመታት በገንዘብ ሲያግዛቸው የነበረው ፕሮጀክት የሥራ ዘመኑን አጠናቆ ከወጣ ወዲህ፣ ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት እንዳጋጠማቸው የዴስክ ኃላፊው ያክላሉ፡፡
በፕሮጀክት ታቅፎ በከፍተኛ በጀት ሲሠራ የቆየው ዕፀዋቱን የመጠበቅ ሥራ በአነስተኛ የመንግሥት በጀት መተዳደር በመጀመሩ፣ በበጀት እጥረት ምክንያት በተገቢው መከናወን እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡
ሥራው ሙሉ በሙሉ ቆሟል ለማለት ያስቸግራል የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ በአንዳንድ የዕፀዋት ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎች ጥሩ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡
በመጥፋትና በመመናመን ላይ ያሉ ዕፀዋትን በመከታተል ዝርያቸው እንዲበዛ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ባለው አነስተኛ በጀት እየሠራ መሆኑን፣ እስካሁን ቅዝቃዜን የሚቋቋሙ ተብለው ወደ ጂን ባንክ የገቡ 133 የዕፀዋት ዝርያዎች መከማቸታቸውን ገልጸዋል፡፡
በየአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከቦታ ቦታ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ዘራቸውን በወቅቱ ለመሰብሰብ አዳጋች እንዳደረጉትና የአየር ንብረት መለዋወጥም ዝርያዎችን በተገቢው ሁኔታ ለማሰባሰብ ሌላው ፈተና እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውስጥ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፀዋትን መትከል አንዱ ተግባር መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ደኤታ አየለ ተሾመ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን በሰፊው እየሠራበት መሆኑን በመግለጽም፣ አገር በቀል ችግኞችን ማፍላት ለሚፈልጉ አካላት በራቸው ክፍት መሆኑንና እስከ ሦስት ጊዜ ጥቅም መስጠት የሚችሉ ለምግብና ለመድኃኒት የሚፈለጉ ዕፀዋትን መትከል ለሚፈልጉ ሰዎች ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰማንያ በመቶ ያህሉ ባህላዊ መድኃኒት ተጠቃሚ ሲሆን፣ 95 በመቶ የባህል መድኃኒቶች የሚዘጋጁትም ከዕፀዋት መሆኑን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ካሉ ከ6,500 በላይ የመድኃኒት ዕፀዋት ዝርያዎችም፣ 887 ተለይተው ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡
