
እኔ የምለዉ የመሬት ለአራሹ አዋጅ ዋዜማ – መባቻ – ማግሥት
ቀን: March 2, 2025
በዳንኤል ካሳሁን
- መግቢያ
በየካቲት 25 1967 ዓ.ም. በዓይነቱ ሥር ነቀል የሆነ ‹‹የአዋጆች ሁሉ እናት››፣ ‹‹የአክራሪ የግራ ተቃዋሚዎችን እንኳ ያስገረመ››፣ ወዘተ፣ የተሰኘና በወቅቱ የበርካቶችን ይሁንታ ያገኘ ታሪካዊ የመሬት ለአራሹ አዋጅ በደርግ ከታወጀ፣ ‹‹ዋይ ዋይ ባላባት ዋይ ዋይ ባላባት፣ እንግዲህ ቀረ ሳይሠሩ መብላት!›› ተብሎ በአደባባይ ከተዜመ፣ የባላባት ሥርዓቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሥር መሠረቱ ተመንግሎ ወደቀ ከተባለ ድፍን ሃምሳ ዓመት ሞላው።
አዋጁ እንዲታወጅ ተማሪዎች ለአሥር ዓመታት ተሠልፈውለት ሳለ፣ አዋጁ እንዲተገበር ወደ ስልሳ ሺሕ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ገጠር ዘምተውለትና ጥቂት የማይባሉት በጎጇቸው እንዳሉ በእሳት ተቃጥለውለት ሳለ፣ አዋጁ እንዳይቀለበስ ገበሬዎች፣ መምህራንና ወታደሮች ታጥቀው ከሸፈቱ የመሬት ከበርቴዎች ጋር አንገት ላንገት ተናንቀው ሕይወታቸውን ገብረውለት ሳለ፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መሬት መተዳደሪያው ሆኖ በአዋጁ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሥር ሆኖ ሳለ፣ የመሬት አዋጁን በተመለከተ ዛሬም በስሜት የሚያወድሱም ሆነ የሚኮንኑ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ዜጎችና ጸሐፍት እያሉ… የአዋጁ የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳ ባይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ጉባዔ ሳይደርግለት ፀጥ እረጭ ብሎ ‹‹እየተከበረ›› መገኘቱ እንግዳ ነገር ነው።
ለዘመናት የኢትዮጵያ ገበሬ በባላባታዊው ሥርዓት አስከፊ ሕይወት ሲገፋ መኖሩ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ረሃብ፣ ወረርሽኝና ስደት ተደጋጋሚ ዕጣ ፈንታው ነበር። ይህ ማለት ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ የደላው ነበር ማለት አይደለም። የገበሬው አሰቃቂ ችግር ዕረፍት የነሳቸው የወቅቱ ተማሪዎችና ተራማጆች ብቻ ሳይሆኑ ንጉሠ ነገሥቱም ጭምር ነበሩ። ምክንያቱም ንጉሡ በዓመታዊ ፓርላማ የመክፈቻዎች ንግግር ላይ ያነሱት የነበረ ዓብይ ጉዳይ ነበርና [1]፡፡
የኢትዮጵያ የመሬት ስሪትን ጠልቆ በመገንዘብ ሳይሆን ከቬትናም የተቀዳው የመሬት ለአራሹ መፈክር በተማሪው ተስተጋብቶ፣ ‹‹የመሬት ለአራሹን የምትሹ፣ ተዋጉለት አትሽሹ!›› ወደሚል አመፅ ተሸጋግሯል። በአንድ በኩል የመሬት ጥያቄው የብሔር ጥያቄን በ1962 ዓ.ም. ወልዶ የተማሪውን ተቃውሞ ሲያፈረጥም፣ በሌላ በኩል ንጉሠ ነገሥቱ የመሬት ስሪቱን አስከፊነት በመገንዘብ ከችግሩ መጠን የሚስተካከል ፈጣን ዕርምጃ ማከናወን ተስኗቸው ተስተውሏል። የባላባትና የጪሰኛ ግንኙነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እንኳ ለፓርላማ እንዳይቀርብ በማድረጋቸው [1] ለየካቲቱ አብዮትና ለወታደራዊው አመፅ ምቹ መደላድል እንደፈጠሩ አይካድም።
የየካቲት 25, 1967 ዓ.ም. የመሬት አዋጅ የኢትዮጵያውያንን ዕጣ ፈንታ በመሠረታዊነት ቢቀይረውም የመሬት ጉዳይ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የማንነት ጥያቄዎች ማጠንጠኛ ሆኖ ዛሬም ድረስ መቋጫ ያልተገኘለት የመወዛገቢያ አጀንዳ ሆኗል። አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ መልኩን ለመመርመር ከተለያየ ዕይታ አንፃር ማየት ግድ ይላል። ይህ መጣጥፍ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከመሬት አዋጁ ጋር የተያያዙ ስፍራዊ ጠባያት ላይ ያተኩራል።
- የመሬት ሥሪቱ ውስብሰብ ነበር
መሬት የኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ የሕይወትና የማንነት እስትንፋስ ነው። በታሪክም ቢሆን [2] በመካከለኛው ዘመን ማብቂያ አካባቢ ኢትዮጵያውያን ሰማዩን የእግዚአብሔር መሬቱን ደግሞ የንጉሥ ነው ይሉ ነበር፣ ታዲያ ሕዝቡ እንዲህ ይል የነበረው ንጉሠ ነገሥቱን ለማሞካሸት እንጂ መንግሥት ምድራቸውን ይወስዳል ብለው አይደለም፣ ማንም ርስታቸውን ሊወስድባቸው እንደማይችል እርግጠኛ ነበሩና፡፡
በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የመሬት ስሪቱ በርካታና ውስብስብ እንደነበር ዓለምአንተ [1] በዝርዝር አቅርቦታል። የሰሜኑ መሬት የወል ሆኖ፣ የርስት/የጉልት አገር ይባል ነበር። ማንኛውም የአካባቢው ተወላጅ አቅኚ የአባቱን ዘር ቆጥሮ የድርሻውን መሬት የማግኘት መብት ስለሚኖረው ‹‹በሺ ዓመቱ ይገባል ከርስቱ›› ይባል ነበር። መሬቱም አይሸጥም። ይህ የሰሜኑ ክፍል ዋንኛ ችግሩ የእርሻ መሬቱ በትውልድ ሲወራረስ እየተሸነሸነ በመበጣጠሱና ምርታማነቱ በመመናመኑ ነው። ከፍተኛ ክርክርና ሙግትም ያስከትል ነበር። በደቡብ ደግሞ መሬት የግል ሆኖ የገባር/ጪሰኛ መሬት ይባላል። ገባሩ በመሬቱ ላይ ዋስትና ስለሌለው የሚያርስበትን መሬት በባለመሬቱ እየተነጠቀ በቀላሉ ከነቤተሰቡ ሊፈናቀል የሚችል ነበር። ሌላው ደግሞ የዘላን መሬት (የመንግሥት) ሲሆን በ1955 ዓ.ም. በተደነገገ አዋጅ መንግሥት እንደፈለገው ለፈለገው ይመራውና ያድለው የነበር ነው። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) በየዓመቱ የሐምሌ 16 ልደታቸውን በማስመልከት የዘላኑን መሬት በችሮታ ለአርበኞች ያድሉ ነበር [3]፡፡
በቅድመ አብዮት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት የተያዘው አንድ በመቶ በሆኑ ባለሀብቶች ነው ተብሎ በተለያዩ አካላት መገለጹ የሀብት ክፍፍሉን ኢፍትሐዊነት ሲያሳይ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ማንኛውም ሥራ አጥና መሬት የሌለው ዜጋ ግማሽ ግማሽ ጋሻ መሬት እንዲያገኝ ንጉሡ በ1948 ዓ.ም. እና በ1955 ዓ.ም. ማዘዛቸው ጉዳዩን አደናጋሪ ያደርገዋል። ለምሳሌ ራስ መስፍን ስለሺ የአንድ ጠቅላይ ግዛት ያህል ስፋት ያለው መሬት እንደነበራቸውና ልዕልት ተናኜ ወርቅ በሐረርጌ ብቻ 22 ሺሕ ጋሻ መሬት ባለንብረትነት ሳይበቃቸው [3] በአብዮቱ ዋዜማ ወቅት ከአዋሽ እስከ አፍደም ቀበሌ ያለው መሬት የአያቴ የራስ መኮንን ይዞታ ስለሆነ ለእኔ ይገባኛል ብለው ወደ 400,000 ሔክታር ገደማ የዘላን መሬት መጠየቃቸው [1] በወቅቱ የነበረውን ሽሚያ ማሳያ ነው። በተጨማሪ በየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮቱ እየተፋፋመ ሳለ ንጉሡ ለንግድ ሚኒስትሩ ከተማ ይፍሩና ለመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል ከበደ ገብሬ በነፍስ ወከፍ አሥር ጋሻ መሬት በአርሲ በችሮታ መስጠታቸው [5] ሌላው እንቆቅልሽ ነበር።
ከለውጡ ትንሽ ቀደም ብሎ ከመቶ የሚበልጡ ዘላን የአፋር አዛውንቶች ለአቤቱታ አዲስ አበባ መጥተው ለደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ የዘላን መሬት የመንግሥት ነው ተብሎ መሬታችንን ወስደው ጨረሱ፣ ዘራችን ሊጠፋ ነው፣ እኛም ልንጠፋ ነው ብለው ነበር [3]።
ሁሉም ገበሬ በጋራ በአስከፊ ጭቆና ሥር ይማቅቅ የነበረ ቢሆንም ከሰሜኑ ይልቅ የደቡቡ ገበሬ የበለጠ የተጎዳ ነበር። ጭሰኛው ተከራይቶ በሚያርሰው መሬት ላይ የይዞታ ዋስትና ስለሌለው ባለቤቱ በፈለገው ጊዜ በማናቸውም ምክንያት ሊያባርረው ይችላል። ምርት ሲቀንስ ተበድሮ እንዲከፍል ይደረጋል አሊያም ከርስቱ ይነቀላል። የደቡቡ ገበሬ ተፈጥሮ የሰጠው ለም መሬቱ የበለጠ ሊጠቅመው ሲገባ በተቃራኒው የመፈናቀል ፅዋ መቅመሻ ሰበብ መሆኑ በተለምዶ እንደሚባለው የመሬቱ ለምነቱ እርግማን ሆኖበት (Resource Curse) ይሆን? ያስብላል።
በወቅቱ የነበረው የመሬት ስሪት ጎጂነቱ በተለያየ አካላት ተደጋግሞ ይወሳ ነበርና ሆን ብሎ ላዳመጠ በርካታ የማንቂያ ደወሎች ነበሩት። ከዓለምአንተ [1] መረዳት እንደሚቻለው ለምሳሌ የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ አልጋ ወራሽ ልዑል አስፋወሰን፣ ‹‹ካሁን በኋላ ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን መሬት ያገኛል›› ብለው ለኢትዮጵያውያን አስተላልፈው ሳለ፣ በ1957 ዓ.ም. ተማሪዎች መሬት ለአራሹ ብለው በአደባባይ ጠይቀው ሳለ፣ በ1958 ዓ.ም. የመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር ተቋቁሞ የችግሩን ግዝፈት እያሳወቀ ሳለ፣ ለጋሽ አገሮች በመሬት ጉዳይ ላይ አንድ ዕልባት አድርጉ እያሉ እየወተወቱና አለበለዚያ ዕርዳታችንን እናቋርጣለን ብለው እያስፈራሩ ሳለ፣ ጥቅምት 23 ቀን 1961 ዓ.ም. ንጉሡ ለፓርማው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱ መሬት እንዲኖረው ለማድረግ ያላቸውን ርዕይ ተናገረው ሳለ፣ የመሬት ይዞታ ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ‹‹የባለርስትና ጭሰኛ ግንኙነት አዋጅ በአስቸኳይ በሥራ ላይ ካልዋለ ኢትዮጵያ የደም ጋን ትሆናለች›› ብለው አስጠንቅቀው ሳለ፣ የዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ ምሁር ኬኔት ፓርሰንስ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥሳሴ የኢራን ንጉሥ መሬታቸውን ለጪሰኞቻቸው አከፋፍለው ሰጥተው ለአገራቸው መፍትሔ እንዳበጁ ሁሉ ኢትዮጵያም ይህን አርአያነት እንድትከተል አበክረው ጠይቀው ሳለ፣ በርካታ የገበሬዎች አመፅ ተከስተው ሳለ… በጭሰኛውና በባለመሬቱ መካከል ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ውል እንዲኖር የሚያስችል መጠነኛ ማሻሻያ አዋጅ ለፓርላማ እንኳ እንዳይቀርብ አንዲት ጋት ፈቀቅ አለማለታቸው ለተጨማሪ ጥናት የሚጋብዝ ክስተት ነው።
በርካታ ምሁራን (ለምሳሌ ባሕሩ፣ ደሳለኝ) እንደሚገመግሙት የባላባት – ጪሰኛ ግንኙነት ማሻሻያ አዋጅ በሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም የንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣን ዕድሜም ሆነ የመሬት አዋጁ ሥር ነቀልነት ፍፁም የተለየ መልክ በያዘ ነበር። በሌላ በኩል የሥርዓቱ ቋጠሮ ውል እንዳይጎለጎል በሚል ሥጋት (Slippery Slope Argument) ሊሆን ይችላል ብሎ መከራከር ይቻላል። ለውሻ በተፈቀደ ቀዳዳ ጅብ ሊገባ እንደሚችል ሁሉ፣ ለስላሳ የተባለው የማሻሻያ አዋጅ ቢፈቀድ ውሎ አድሮ የከረረና የገዘፈ ጥያቄ አስከትሎ ለንጉሠ ነገሥቱ ሕልውና አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ይህ ሥጋት አፍንጫዋን በርዷት የነበረችው ግመል በድንኳን ውስጥ የነበረው ግለሰብ ላይ ያደረገችውን ታሪክ ሊያስታውስ ይችላል። ሆኖም አንዳርጋቸው [4] ንጉሠ ነገሥቱ ለውጥን ባለመሻት የራሳቸውን አስከፊ ውድቀትና መቃብር ሲያዘጋጁና ሲቆፍሩ ኖሩ ብሎ ማለቱ ከንጉሡ ውሳኔ ጀርባ አንዳችም አመክንዮና ዕሳቤ እንዳልነበረ የሚፈርጅ ግርድፍ ትንታኔ ይመስላል።
የሚገርመው ኋላቀርና ፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ ተብሎ ይነቀፍ በነበረ ሥርዓት ንጉሡም ሆነ ፓርላማው ፍፁም ላይቀበሏቸው የሚችሉ አዋጆች በመንግሥት በጀት በሚተዳደር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለምሳሌ የባላባት – ጪሰኛ ግንኙነት ማሻሻያ አዋጅ – መርቀቅ መቻሉ ነው። በተቃራኒው ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ይህን መሰል ሙከራ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ/ብልፅግና ዘመናት ማየት አለመቻላችን ወደኋላ የቀረነው ያኔ ወይስ አሁን የሚል ግርምት ይፈጥራል።
- ታሪካዊው የመሬት ለአራሹ አዋጅ
ደርግ እንደ ተማሪው ቀድሞ በፖለቲካ የነቃ አልነበረም። የመሬት ለአራሹን ጉዳይ ያነሳው የካቲት 21 ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በሔሊኮፕተር በበተነው ወረቀት ላይ ነው። ካቀረባቸው 11 ጥያቄዎች መሀል 4ኛው መሬት ለአራሹ እንዲሰጥ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ገና በሥልጣን ላይ እያሉ ነበር ለመሬት ይዞታ ሚኒስትሩ ለአቶ በለጠ የመሬት አዋጅን በሚስጥር እንዲያረቁ ያዘዛቸው [5]።
ከዓለምአንተ [1] መገንዘብ እንደሚቻለው ከመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ‹‹ተራማጅ›› ምሁራን ባሻገር ኤክስፐርቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የደርጉ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኮሚቴ ፅንፈኛ የሆነ የመሬት አዋጅ እንዲታወጅ ጫና አሳርፈዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የስዊድንና የአሜሪካ መንግሥታት እንዲሁም በርካታ የደርጉ አባላት ለዘብ ያለ አዋጅ እንዲታወጅ ፈልገው ነበር። ሌላው ይቅርና አዲስ አበባ የሚገኙ የሶሻሊስት አገሮች አምባሳደሮች ደርጉ ያረቀቀው አዋጅ ቢታወጅ ሊያስከትል የሚችለውን ምስቅልቅል በመሥጋት አዋጁ በፍጥነት እንዳይተገበር ተማጽነዋል። ‹‹በአገራችን በሥር ነቀል የመሬት አዋጅ ሳቢያ ተከትሎ ከመጣብን ችግር ተማሩ›› [6] ብለው መክረውም ነበር፣ ሰሚ አላገኙም እንጂ።
የመሬት ይዞታ ጣራውም አጨቃጫቂ ነበረ። ለደርግ የቀረበው ሐሳብ ጣራው አምስት ጋሻ ሲሆን ራሱ የሚያርስ ከሆነ አንድ ጋሻ ነበር። ደርግ ‹‹የፊዳላዊውን ሥርዓት ከናካቴው እንድናጠፋ ይረዳናል›› በሚል ዕሳቤ [7] ጣሪያው እስከ አሥር ሄክታር ብቻ ተደረገ። አሥር ሄክታር ምን ያህል ስፋት እንዳለው ለደርጉ አባላት ለማስገንዘብ በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ችካል ተቸክሎ እንዲመለከቱት ተደርጓል [5]። በርካታ የእርሻ ባለሙያና ኢኮኖሚስት ባለበት አገር ወታደሮች የመሬት መጠንን በዓይን ብቻ ተመልክተው አዋጁን እንዲያፀድቁ መደረጉ ትልቅ ስህተት ነበር። ምናልባትም ከኢሕአፓ ጋር የነበረውን የሶሻሊስታዊነት ፉክክርን ለማሸነፍ በሩጫ አዋጁን ለማወጅ ከመሻት ይሆን?
በረቂቅ አዋጁ ላይ ድምፅ ከመስጠቱ በፊት ሻለቃ አጥናፉ አባተ የሰጡት ትንቢታዊ የሚመስል ማስገንዘቢያ ዘመኑን የቀደመ አስተያየት ነበር ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡ ይህ አዋጅ ከፀደቀ አገራችን የማትወጣው ችግር ማጥ ውስጥ ትዘፈቃለች… ባለመሬቶች ይሸፍታሉ፣ የእርሻ ሥራ ተቋርጦ የእህል እጥረት ይከሰትና ረሃብ ሊከተል ይችላል፣ ቤተ ክህነት የምትደዳረው ከመሬት በሚገኝ ጥቅም ስለሆነ ብዙ ቤተ ክርስቲያናት ሊዘጉ ይችላሉ፣ ከመምዕናን ጋር ቅራኔ ውስጥ እንገባለን፣ ትርምስና ብጥብጥ በአገሪቱ ይሰፍናል፣ የኤርትራ ወንበዴዎች አጋጣሚውን ይጠቀማሉ፣ ሶማሊያም ኦጋዴንን ይወራል [8] ብለው መናገራቸው ከእህል እጥረትና ረሃቡ ዘግየት ብሎ የመከሰት ጉዳይ በቀር ሁሉም ትንቢቶች ዕውን ሆነው ነበር።
የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ከተስተጋባ በአሥር ዓመቱ የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. ሲታወጅ መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ፣ በወለድ አገድ የማይያዝ፣ በኪራይ መልክ ወደሌላ የማይተላለፍ ሆኖ ተደነገገ። በተዘዋዋሪም መንግሥት ማኘክ ከሚችለው በላይ ጎረሰ። የውርሱን መብት ሙሉ ለሙሉ ባይሽረውም ማገዱ፣ መሬትን ማከራየት ከመከልከልም አልፎ በቅጥር ጉልበትን ማሳረስንም ማገዱ፣ እያንዳንዱ ባለይዞታ መሬቱን በራሱ ጉልበት ብቻ መጠቀም እንዳለበት መወሰኑ በርካታ አንድምታዎችን አስከትሏል፣ እስከ ዛሬ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። አዋጁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲታተም ብዛቱ ከመደበኛው የዕለታዊ 40,000 ኮፒ ወደ 120,000 ማደጉ [5] ሕዝቡ ምን ያህል አዋጁን ለመረዳት መፈለጉን ያመላክታል።
የመሬት አዋጁ እጅግ ፅንፈኛና ሥር ነቀል ሆኖ ሳለ፣ በፍጥነት ከተደረገለት ታላቅ ሕዝባዊ የድጋፍ ሠልፍ ባሻገር የፖለቲካ ድርጅቶችም አድናቆታቸውን ሳይሰስቱ ችረውታል። ፋሲካ [9] የመሬት ይዞታ አዋጁ ድፍረትና ሀቀኝነት የተንፀባረቀበት እንደነበረ ገልፆ ከመሬት ባለቤቶችና ደጋፊዎቻቸው በስተቀር ሕዝቡ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ ደግፎት ነበር። ኢሕአፓ የመሬት አዋጁ ከፍተኛ ቆራጥነት የሚጠይቅ ታሪካዊ ዕርምጃ [10] ነው ብሎ መስክሯል፣ መኢሶን ደግሞ ኢትዮጵያ እንደዚያን ዕለት በሕዝቦቿ ደስታ ፈገግ እንደማታውቅ… አዋጁን ማመሳከር የሚቻለው ሌኒን በ1917 ካወጀው መሬት ለአራሹ ጋር ብቻ እንደሆነ [4] ተነግሯል። ደርግ ባይሆን ኖሮ ይህን መሰል ሥር ነቀል የመሬት አዋጅ ሥራ ላይ ማዋል አይቻልም ነበር [5] ተብሏል። ሆኖም ግን ንጉሠ ነገሥቱ የተካው ደርግ ባይሆንም ኖሮ ተመሳሳይ የከረረ መሬት አዋጅ መውጣቱ አይቀሬ ነበር ለማለት ያስደፍራል።
- አዋጁ በርካታ ሥፍራዊ ጠባያት ነበሩት
ኢትዮጵያ ትልቅና በበርካታ የሥነ-ምኅዳርና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የበለፀገች አገር ብቻ ሳትሆን በተነባባሪነት በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በሕዝብ አሰፋፈር፣ በኢኮኖሚ፣ ወዘተ የተሰባጠረች ናት። በተጨማሪም የመሬት ስሪቱ፣ የጭቆና መጠኑ፣ የእርሻ መሬት ስፋትና ጥበቱ፣ የአፈር ለምነቱና መራቆቱ፣ ወዘተ ከሥፍራ ሥፍራ ይለያይ ነበር። ይህ መሠረታዊ የሥፍራ ልዩነት የመሬት ለአራሹ አዋጅ ገፊ ምክንያትን፣ ቅቡልነትን፣ ተቃውሞን፣ ስኬትንም ሆነ ውድቀትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሻራውን ያሳረፈ መሆኑን ለመገንዘብ በሚከተለው መልኩ ተዘርዝሯል።
4.1 የመሬት ስሪቱ ሥፍራዊ ጠባይ ነበረው: የመሬቱ ስሪቱ ገበሬውን ለድህነትና ኢፍትሐዊነትን የዳረገ ቢሆንም ችግሩ በሁሉም የኢትዮጵያ ምድር ተመሳሳይ አልነበረም። የመሬት ስሪቱ እንኳንስ በመላው አገሪቱ በጠቅላይ ግዛቶች መሀል ከፍተኛ ልዩነት ነበረው። የተማሪዎች ንቅናቄ ‘መሬት ለአራሹ’ ብሎ ሲነሳ ትኩረቱ ደቡብ ላይ ሰፍኖ የቆየውን ጭቆና መሠረት በማድረግ ነበር። የሰሜኑና የደቡቡ ገበሬ የሚለያየው በባላባታዊው ሥርዓት የጭቆና መጠን ብቻ አልነበረም። የሰሜኑ ገበሬ በመሬት ጥበትና መራቆት የተሰቃየ ሲሆን የደቡቡ ገበሬ ደግሞ መሬት አልባ ጭሰኛ መሆኑ ነበር። መስፍን ወልደማርያም [11] የመሬት አዋጁን ከነቀፈበት ምክንያቶች አንዱ ደርግ በሰሜንና በደቡብ ያለውን የመሬት ይዞታ ችግር ተመሳሳይ ማድረጉና ተመሳሳይ መፍትሔ መስጠቱ ነው።
የፓርላማ አባላት በከፍተኛ ደረጃ የንጉሠ ነገሥቱን የመሬት ስሪት የሚደግፉና በርካቶቹ የመሬት ከበርቴ ቢሆኑም ሰሜኑንና ደቡቡን ክፍል የሚወክሉት የፓርላማ አባላት ሥፍራዊ ጠባይ ነበራቸው። እንደ ዓለምአንተ [1] ትውስታ ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ተመርጠው የመጡት የፓርላማ አባላት ለባለመሬት ጪሰኛ ግንኙነት ረቂቅ አዋጁ ወገንተኛ የነበሩ ሲሆኑ ከደቡብ ኢትዮጵያ ተመርጠው የመጡት የፓርላማ አባላት ግን ከፍተኛ የመሬት ባለንብረቶች ነበሩና የረቂቅ አዋጁ ፍጹም ተቃዋሚ ነበሩ።
4.2. የሜካናይዜሽኑ ስርጭትና ጣጣ ሥፍራዊ ጠባይ ነበረው፣ ሜካናይዝድ እርሻ የምርት ዕድገትን ለማሳደግና ለማዘመን የሚረዳ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ሥርጭቱም ሆነ በተጓዳኝ ያስከተለው መዘዝ ሥፍራዊ ጠባይ ነበረው። በሜካናይዜሽኑ ሳቢያ ገበሬው ከቤትና ንብረቱ መፈናቀሉ እጅግ የበረከተው በደቡብ ነበር። ከ1940ዎቹ ጀምሮ ሜካናይዜሽን በአዋሽ ተፋሰስ (የተንዳሆ ጥጥ እርሻ፣ የወንጂና የመተሐራ የስኳር ፋብሪካ) ሲስፋፋ ዘላኖችን በማፈናቀል ተጀምሮ በቀጣይነትም በሰላሌ፣ በአድአ፣ በጭላሎ፣ በሻሸመኔ ወዘተ አካባቢዎች ተስፋፍቷል። ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች ሲስፋፉ የደሃው መሬት ቤቱ ሳይቀር በቡልዶዘር እየተጠራረገ ከይዞታው ተነቀሏል።
በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ ጥያቄ እየበረከተ ሲመጣ፣ ‹‹ይህ ነገር ጥያቄ ሊያስነሳብን ይችላል›› በሚል ሥጋት የልዑል አሥራተ ካሳ ቤተሰቦች ጭሰኞቻቸውን ሰላሌ ውስጥ በሁለት ወረዳዎች ከነበሩበት መሬቶቻቸው ነቅለዋቸው ወደ አምቦ፣ ግንደ ብረት፣ አርሲ፣ ባሌ፣ በመሄድ ባገኙት ክፍት ሥፍራዎች እንዲሰፍሩ ተገደዋል [5]። በሰላሌ አካባቢ ገበሬው ከመሬቱ ተፈናቅሎ አዲስ ሕይወት ለመመሥረት ወደ ተለያየ ሥፍራ በእግሩ ጉዞ በጀመረ ጊዜ ታሪካዊ በሆነ እንጉርጉሮ:
“ባለርስቱ ወጣሁልህ፣ ባለርስቱ ወጣሁልህ፣
አይጥ ጭሰኛ ከሆነልህ፣ ዳዋው (ሙጃው) ጎረቤት ከሆነልህ፣
ዝንጀሮ ጅጊ (ደቦ) ከወጣልህ፣
ከሀገር ወጣሁልህ፣ ባለርስቱ …”
እያለ እንደሚቀጥል ፋሲካ ሲደልል (2014: 76) በልጅነቱ ይሰማው እንደነበረ ያስታውሳል።
የደቡቡ ክፍል የጭሰኝነት ሥርዓቱን በተወሰነ መልኩ ሚዛኑን ጠብቆ በመሬቱ ተረጋግቶ የቆየ ቢሆንም የሜካናይዜሽን እርሻ ሲጀመር ቀድሞ የነበረው ሚዛን በመዛነፉ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል። ሜካናይዜሽን እርሻ ሲስፋፋ ምርታማነትን ከማበልፀግ ባሻገር ትኩረቱ ሥፍራው በነበረ የጪሰኛ ሕይወት ላይ ባለመሆኑ የበርካታ ደቡብ ጭሰኞች ያለምንም ማስጠንቀቂያና ማካካሻ አፈናቅሏል፣ በተማሪው ንቅናቄ ትኩሳት ላይ ነዳጅን አርከፍክፏል፣ ደርጉ ወደ ፖለቲካ ዘው ብሎ እንዲገባም በሩን ወለል አድርጎለታል።
ከ1959 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ብቻ እስከ 5,000 ገባር ቤተሰቦች በሜካናይዝድ እርሻ ሳቢያ ከመሬታቸው ተፈናቅለዋል [6]። በሜካናይዜሽን ሳቢያ የተፈጠረው የጪሰኛው የሕይወት መቆርቆዝና በአንዳንድ ጭሰኞች የተካሄደው አመጽ [14] ሥፍራዊ ጠባይ እንደነበረው መረዳት ይቻላል።
4.3. ገበሬው የመሬት አዋጁን የተቀበለበት ፍጥነት ስፍራዊ ጠባይ ነበረው፣ የመሬት ከበርቴውና አራሽ ገበሬው የመደብ ተቃርኖ የነበራቸው ቢሆንም በሰሜኑና በደቡቡ የሚታየው የተቃርኖ መጠን እኩል አልነበረም። የሰሜኑ ገበሬ ለባላባቱ የሚከፍለው ከደቡቡ ገበሬ አነስተኛ ነበር። ምንም እንኳ በሰሜኑ እስከ 15 በመቶ ጭሰኛ የነበረ ቢሆንም ለባላባቱ እንዲከፍል የሚጠየቀው መጠን ከአቻ የደቡቡ ጭሰኛ እጅግ ያነሰ ነበር። የሰሜኑ ገበሬ ከባላባቱ መደብ የነበረው ቅራኔ እጅግ የከረረ ስላልነበረ በሰሜን ኢትዮጵያ የመሬት ለአራሹ አዋጅ ቅበላን ቀዝቃዛና ዘገምተኛ አድርጎታል።
በ1952 የፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት የደቡቡ ገበሬ እስከ 75 በመቶ የፍሬውን ውጤት ለባለመሬቱ ፈሰስ እንዲያደርግ ይገድድ ስለነበር የመደብ ተቃርኖው በደቡቡ እጅግ የከረረ ነበር። ለዚህም ይመስላል የደቡቡ ክፍል የመሬት አዋጁን ብቻ ሳይሆን የገበሬ ማኅበራት ምሥረታና የመሬት ክፍፍሉን በሙሉ ልብ ፈጥኖ የተገበረው። ባሕሩ [12] እንደሚገልጸው አዋጁ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ይገኙ የነበሩትን ጪሰኞች በላቀ መልኩ ተጠቃሚ አድርጓል። ተስፋዬ ዲንቃ [13] በሰሜኑና በደቡቡ ገበሬ መሀል የመሬት አዋጁ ‹‹የቅበላ ልዩነት›› (Enthusiasm Gap) እንደነበረው መግለጻቸው ከላይ የተጠቀሰውን ሥፍራዊ ጠባይ ያጠናክራል።
4.4. የባላባቱ ተቃውሞ ስፍራዊ ጠባይ ነበረው፣ በርካታው የመሬት ከበርቴ የመሬት አዋጁንም ሆነ አብዮቱን ለመቀልበስ ብረት ባያነሳም ጥቂት የማይባሉ የተቆጡ የመሬት ከበርቴዎች ግብረ አበሮቻቸውን አስከትለው በመሸፈት መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። ምንም እንኳ ያመጹት ባላባቶች የተነጠቁት ደቡብ የሚገኘውን መሬታቸውን ቢሆኑም ለሽፍትነት የመረጡት ሥፍራ ደግሞ በመሀልና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ነበር። ብዙ የትግራይ፣ ጎጃምና የበጌምድር እንዲሁም የተወሰኑ የወሎና የሸዋ አውራጃዎች ከመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነፃ ሆነው ለደርግ መንግሥት ሥጋት መሆናቸው የሚያመላክተው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ከደቡቡ የሚለይበት ሌላው ጠባይ ነበር።
4.5. የተማሪው የፖሊቲካ ጥያቄ ስፍራዊ ጠባይ ነበረው፣ የመሬት ለአራሹ በውስጡ የኢኮኖሚ ጥያቄ ቢኖርበትም በዋናነት ግን የፖለቲካ ጥያቄ ነበር። የመሬት ይዞታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሆኑት እነ ዘገየና ዓለምአንተ በአዋጁ ዝግጅት ወቅት ተሳታፊዎቹ ተራማጅ የነበሩ እንጂ የብሔር ፖለቲካ እንዳልተቀላቀለበት በቅርብ በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች የመሰከሩት ጉዳይ ቢሆንም የብሔር ጥያቄን ከመሬት አዋጁ ጋር ተንጠላጥሎ ለመጓዙ ጥቂት አመላካቾች የነበሩ ቢሆንም አዋጁ ከታወጀ በኋላ በበርካታ ሥፍራዎች ታይቷል። አዋጁን እንደ ኖህ መርከብ የተጠቀሙበት የብሔር አራማጅ ግለሰቦችና ድርጅት እንደነበሩ ማሳያዎች ቢኖሩም እርግጠኛ ለመሆን ጠለቅ ያለ ምርምር የሚሻ ጉዳይ ነው።
የሰሜኑ ገበሬ ከባላባቱ ጋር በቋንቋና በሃይማኖት አንድ በመሆናቸው የመደብ ተቃርኖው የለዘበ ነበር። እንደውም አዋጁን ለኦሮሞውና ለሙስሊሙ እንጂ ለአማራ ትግሬ ክርስቲያኑ እንዳልመጣ ተቆጥሮ ይታይ ነበር [14]፡፡ በደቡብ የነበረው የከረረ የመደብ ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶችንም ያስተናግድ ነበር። ባላባቱ ክርስቲያኖች፣ ጭሰኞቹ እስላሞች ወይም ሃይማኖት የለሾች ስለነበሩ በባላባቱና በጪሰኛው መሀል የነበረው የልዩነት መስመር ደመቅ ያለ ነበር። በመሆኑም የመደብ ልዩነት ከብሔር ጥያቄ ጋር የተቆራኘበት ሁኔታ ሥፍራዊ ልዩነት እንደነበረው መገንዘብ ይቻላል።
እንደ ደሳለኝ [15] ከሆነ በወቅቱ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ብሔረሰብን ማዕከል አድርጎ የሚሽከረከር አልነበረም፣ የብሔረሰብ ጭቆናው ዋንኛ መሠረቱ የመሬት ስሪቱ ነበር። በሌላ በኩል እንደ ደቡቡ ክፍል ጎልቶ አይታይ እንጂ በጎጃም ደጋ ዳሞት በመሬት አዋጁ ማግሥት በርካታ የሙስሊም እምነት ተከታይ አርሶ አደሮች ከቀያቸው ተባረው በመጨረሻ መንግሥት በመተከል አውራጃ ቻግኒ አካባቢ እንዳሰፈራቸው ተመስክሯል [1]። ሁኔታው የሚያስገነዝበው ከመደብ ልዩነቱ ጋር ተነባብሮ ሃይማኖታዊ ተቃርኖ እንዳስተናገደም ነው። ደርግ የመሬት ስሪት መፍትሔ ማምጣት ማለት አብዛኛው የተገፉና የተጨቆኑ ብሔረሰቦችን የሚመለከት እንደሆነ አልተገነዘበም ነበር። ከላይ የተጠቀሱትን ክስተቶች መሠረት በማድረግ ላለፉት ሦስት አሦርት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕጋዊነት ተላብሶ በሥራ ላይ የዋለው የብሔር ተኮር ፖለቲካ የተጠነሰሰው ምናልባትም ከመሬት ለአራሹ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ ነበረ? የሚል መላምትን መሰንዘር ይቻላል፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችንም ለምርምር ይጋብዛል።
በአጠቃላይ ከአዋጁ ማግስት ጀምሮ ደርጉ አቅሙ በፈቀደ የገበሬውን ሕይወት ለማሻሻል በገበሬ ማኅበራት፣ በመንደር ምሥረታ፣ በሰፋፊ የሰፈራ ፕሮግራሞችና በምግብ ለሥራ የሚደጎሙ እርከን ሥራና ደን ተከላ ፕሮግራሞች፣ ወዘተ ጥረት ቢያደርግም የገበሬውን ሕይወት ከፍፁም ድህነትና ምግብ ዋስትና ዕጦት ሊያላቅቀው አልቻለም።
- የኢሕአዴግ መንግሥትና የመሬት አዋጁ
ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲጨብጥ የደርግን ኢዴሞክራሲና ኢፍትሐዊ ሥርዓትን አስወግጄ ነፃ ገበያን በኢትዮጵያ አሰፍናለሁ ብሎ ቃል ቢገባም የገጠር መሬት ባለቤትነትን በተመከለተ ከደርጉ አልተለየም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 የገጠርና የከተማ መሬት ባለቤትነት መብት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቱ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ብቻ ነው። መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው ብሎ ደነገገ። እርግጥ ነው በሒደት መሬት ማከራየትና በራስ መሬት ላይ የቅጥር ጉልበት መጠቀምን ፈቅዷል፣ መሬትን በውርስ የማስተላለፍ መብት ሰጥቷል፣ የገበሬዎችን የመሬት ባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ የመሬት ምዝገባና ማረጋገጫ ሠርተፍኬት ሰጥቷል። ሆኖም መሬት የሚሸጥው በመቃብሬ ላይ ብቻ ነው ብሎ ላለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ዘልቋል። የደርግ ሥርዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ ከዳር አስከዳር እኩል ባለመሬት ለማድረግ አዋጅ አወጀ፣ ርስትንም ማደሪያንም ሽሮ የመሬት ባለቤትነትን በዜግነት ላይ ተከለ። የወያኔ ሥርዓት ሲመጣ የገጠር መሬትን በፖለቲካ ታማይነት ደለደለ ብሎ መስፍን ወልደ ማርያም [11] መኮነኑ ለተነሳው ጉዳይ ገላጭ አባባል ይሆናል።
የኢሕአዴግ/ብልፅግናም ሆነ ሌሎች የብሔር ፖለቲካ ቡድኖች የመሬት ባለቤትነት ክርክርን ከብሔር ፖለቲካ መነፅር ብቻ እንዲመዘን ሞግተዋል። በተቃራኒው ጉዳዩን ከኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ መርህ አንፃር መሞገት የድሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚል ስያሜን የሚያሰጥ ጉዳይ ሆኗል። መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም የሚለው መፈክር እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬቶቿን ለውጭ ባለሀብቶች ከስምንት ዶላር (በሔክታር) ጀምሮ ሆኖ እስከ 99 ዓመታት ድረስ በሚፀና የሊዝ ውል በገፍ አከራይታለች። ለመሬት ተከራዮቹ ‹‹የክፍለ ዘመኑ ስምምነት›› ቢባልም ‹‹መሬት ነጠቃ›› (land grab) የሚለው አጠራር የበለጠ ይገልጸዋል [16]።
ኢሕአዴግ ለገበሬው የተለየ ተቆርቋሪነትና አጋርነት አለኝ በማለት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዬ የግብርና መር ነው ብሎ፣ የተለያዩ የግብርናና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞችን ዘርግቶ፣ የሳሳካዋ ግሎባል 2000 የተሰኘ አረንጓዴ አብዮት ቀመስ ፕሮግራም አራምዶ፣ በአንድ በኩል የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሥር የነበሩ አንጋፋዎቹን የእርሻ ኢኮኖሚክስና የእርሻ ምኅንድስና ዲፓርትመንቶችን ያለ አሳማኝ ምክንያት ዘግቶ፣ በምትካቸው የእርሻ አክስቴንሽን ኮሌጆችን በአገሪቱ አስፋፍቶ፣ የኢትዮጵያ እርሻ ወኪሎች ብዛት ከቻይናና ከህንድ ቀጥሎ በዓለም በሦስተኛ ደረጃ እንዲገኝ ቢያደርግም ይህ ሁሉ ጥረት ተደማምሮ በቅድመ መሬት አዋጁ ዘመን የጭላሎ እርሻ ልማት (ካዱ) ያሳየውን ዓይነት ውጤት እንኳ አላስገኘም።
- የአዋጁ ትሩፋትና ጉዳት
የመሬት አዋጁ እንደታወጀ ወደር የማይገኝለት ሕዝበኝነትን ተጎናፅፏል። በወቅቱ የማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም በተማሪው እንደፋሽን ይታይ ነበር። ይህ ርዕዮተ ዓለም ቀደም ብሎ በሩሲያ፣ ቬትናም፣ ቻይና፣ ወዘተ መሬት ከበርቴዎች ላይ ግዳይ ጥሎ ዝናው ካፅናፍ እስካፅናፍ ናኝቶ ነበርና የ1967 ዓ.ም. ሥር ነቀል አዋጁን መደገፍ ማለት የሞራል ልዕልና እንደመጎናፀፍ የሚቆጠር ጉዳይ የነበረ ይመስላል። ባለ መሬቱን ባንድ ጀምበር ባዶ አስቀርቶ ገበሬውን የመሬት ባለቤት የሚያደርግ አዋጅ እንደ ምሉዕ በኩለሄ ተደርጎ ተወስዷል። በተለይም በደቡቡ ክፍል ደርሶ የነበረው እጅግ አሰቃቂ በደል ተደጋግሞ ለተቃውሞ ማጠናከሪያነት ሲወሳ ስለከረመ የደቡቡ ገበሬ አዋጁን እጁን ዘርግቶ መቀበሉ አይደንቅም። አዋጁ የፈጠረው የመንፈስ ኩራትም ዛሬም ድረስ ህያው ሆኖ በተለይም በደቡቡ ክፍል ፖለቲከኞች እንደ ትልቅ ድል የሚወሳ ጉዳይ ነው።
የአዋጁ ሌሎች ትሩፋቶች [1] ደግሞ በመሬት ክርክር ሳቢያ በየፍርድ ቤቶች ይጠፋ የነበረው ጊዜ ፈፅሞ እንዲወገድ መደረጉ፣ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የግብር ዓይነቶች መወገዳቸው፣ ‹‹አርሶ አደሩ የጉልበቱን ፍሬ ማንም ሳይካፈለው ለራሱና ለቤተሰቡ ፍጆታ ብቻ ማድረጉ›› ናቸው። ሌላው ይቅርና በመሬት አዋጅ ሳቢያ እነ ሶቪየት ኅብረት አያሌ ቁጥር ላለው ሕዝብና ለከብቶች ውድመት ተጋልጠው ሳለ፣ ተመሳሳይ ቀውስ በኢትዮጵያ አለመከሰቱ ሌላው የተመሰከረ የአዋጁ ስኬት ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ቀላል የማይባሉ ትሩፋቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ውሎ አድሮ የመሬት አዋጁ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን አስከትሎ እንደነበር ያለፉት ሃምሳ ዓመታት እንደ መስታወት ያሳዩናል።
አንደኛ የደርጉም ሆነ የመሬት ይዞታ ባለሥልጣናት የመሬት አዋጁ ባላባቶችን አላገለለም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ሚኒስትር ዘገየ አስፋው [3] የመሬት ከበርቴው ከዚህ ነው ከዚያ ነው የመጣኸው ሳይባል የድርሻውን እንደሌላው ገበሬ ማግኘት ይችላል ሲል ያየህ ይራድ ቅጣው (ዶ/ር) [17] ደግሞ ‹‹ባላባቶች ከአገር ውጡ አልተባሉም›› ብሎ ይመሰክራል። ሆኖም በተግባር የታየው ሌላ ነበር። በበርካታ የደቡብ አካባቢዎች የእርሻ ማሳሪያዎችና በሬዎች ያለ ካሳ ተወርሰዋል፣ ከአዋጁ ቀደም ብሎ ተመርቶ የነበረና በጎተራ የነበረ እህል እንኳ የተወረሱባቸው ሥፍራዎች አሉ፣ ከቀያቸው የመባረርና የመገደል ዕጣ የደረሳቸው ዜጎችም ነበሩ።
ሁለተኛ ከመሬት አዋጁ ቀደም ብሎ ከሰሜንና መሀል ኢትዮጵያ እየተነሱ ገበሬዎች ወደ የደቡብ ምዕራብ ወቅትን እየጠበቁ ለቡና ለቀማ ይመጡ የነበር ቢሆንም ከአዋጁ በኋላ ይህ የፈረቃ ምልልስ (seasonal migration) ተቋርጧል። አንድም አዋጁ አርሶ አደር ሠራተኛ መቅጠርን በመከልከሉ፣ ሌላም በገበሬ ማኅበራት ያልታቀፈ በእርሻ ሥራ ሊሰማራ ስለማይችል ነበር። አልፎ ተርፎም በቡና ለቃሚ ዜጎች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እየተባባሰ መጥቶ ነበር። እንደ ውድ [18] ምሥክርነት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመሬት አዋጁ ‹‹የመሬት ብሔርተኝነትን›› አስፍኖ ነበር።
ሦስተኛ ከአዋጁ በኋላ የገበሬው ምርታማነት እንደሚጨምር ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በተግባር አልታየም። መሬት በገበሬ ማኅበራትና በኅብረት ሥራዎች መተዳደሩ የሥራ ፉክክርን፣ ፈጠራንና ምርታማነትን በእጅጉ አቀጭጮታል። የመሬቱ ሕጋዊ ጣራው አሥር ሔክታር ብቻ በነበረበት ሁኔታና ከ61 በመቶ በላይ የሚሆኑ የአርሶ አደር ቤተሰቦች ከአንድ ሔክታር ያነሰ መሬት በያዙበት አገር የእርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ ማቀድ ጉም እንደ መጨበጥ ሆኖ ቆይቷል። መስፍን [11] የመሬት አዋጁን ሲወቅስ ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረውን ከፍተኛ የትላልቅ የእርሻ ዕድገት ማገዱ ነው ይላል፣ ሌሎች በርካቶችም ሐሳቡን ይጋሩታል። ገበሬው እስከ 75 በመቶ የእርሻ ምርት ውጤቱን ለባላባቱ እንዲሰጥ ይገደድ ነበረና ከአዋጁ በኋላ ገበሬው እጅ የሚገባው የምርት መጠን በሦስት እጥፍ (300 በመቶ) ማደግ ነበረበት። ምንም የተሻለ ነገር አለመገኘቱ ከአሮጌው ጉልታዊው ሥርዓት ሌላ የገበሬውን ሕይወት ቀስፎ የያዘ ሌላ አንኳር ጉዳይ ነበርን ያስብላል።
አራተኛ ገበሬው የመሬት ባለቤትነት ሲሆን መሬቱን ይንከባከባል፣ ድርቅና ረሃብ ተጋላጭነቱን ይቀንሳል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ከአዋጁም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። ገበሬው ጉልበቱንም ሆነ ገንዘቡን በመሬቱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ከረዥም ጊዜ በኋላ የሰብል ምርታማነትንና የአካባቢ ልማትን ያመጣልኛል ብሎ ለመተማመን አልቻለም። የእርከን፣ የፍሳሽ ቦዮች፣ የደን ማልማት ወዘተ የሚደረግ ተነሳሺነትን ማዳከሙን በርካታ ጥናቶች መስክረዋል። በዚህ ሳቢያ፣ የመሬት የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ ተመናምኗል፣ የምግብ ዋስትናውም እያሽቆልቁሏል፣ ቀላል የማይባል ገበሬ በምግብ ዕርዳታ ላይ ሕይወቱ ተንጠላጥሏል።
አምስተኛ ደርጉ የመሬት አዋጁን አስፈላጊነት ሲያስረዳ የንጉሠ ነገሥቱ የመሬት ስሪትና ኢፍትሐዊነት ለወሎው አስከፊ ረሃብ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሎ ፈርጆ ነበር። የመሬት አዋጁ በታወጀ በአሥር ዓመቱ በ1977 ዓ.ም. ከቀድሞው የባሰ አሰቃቂና አስከፊ ረሃብ በኢትዮጵያ ሲከሰት ሌሎች በርካታ ጉዳዮች መታየት እንደሚገባ አመላካች ነበር። ድርቁን በዘለቄታው ለማስወገድ ተብሎ የተካሄው የሰፈራ ፕሮግራም ያለ በቂ ዝግጅት የተከወነ በመሆኑ ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሎ ሌላው ይቅርና ቀድሞ የመሬት አዋጁን በአድናቆት የተቀበሉት ገበሬዎች ጭምር ቅር ተሰኝተው ነበር።
ስድስተኛ መሬት ከባላባቱና መዳፍ ተላቀቀ ቢባልም ገበሬው በመሬቱ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳይሰጥ አድርጎ መንግሥት ራሱ የመሬት ከበርቴ ሆኖ ቁጭ ብሏል። የገበሬ ማኅበራትን በማስገደድ እህል ከገበያ በታች በሆነ ዋጋ ለእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት እንዲሸጥ አስገድዶ አርሶ አደሩ የተጣለበትን ኮታ ማሟላት ሳይችል እየቀረ ከብቶቹን ሸጦ ከገበያ በውድ ዋጋ ገዝቶ በኪሳራ ለኮታ ማሟያ የሚያስረክብባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። በሌላ ቋንቋ የገበሬው ሰቆቃ በሌላ ገፅና ቁመና ቀጥሎ ነበር።
ሰባተኛ በመሬት ለአራሹ ሳቢያ የመሬት ክርክርና የፍርድ መጓደል አበቃለት ተብሎ የተነገረ ቢሆንም ከአዋጁ በኋላ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሰፈነው የመሬት ነክ ፍርድ ይግባኝ የሌለው፣ ብያኔ የሚሰጠው ደግሞ የሕግ መሠረታዊ ዕውቅትና ልምድ በሌላቸው የገበሬ ማኅበራት ተመራጮች ሆነ። የፈለገ ውሳኔ ገበሬው ላይ ቢጣል ‹‹አሜን›› ብሎ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም።
ስምንተኛ መሬት አልባነት በቅድመ አዋጁ ዘመን አንዱ ችግር ነበረ፣ ከአዋጁ በኋላም አልቆመም፡፡ አዋጁ ከሥነ ሕዝብ ጋር የተያያዙ ለውጦችን ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ መሬት አልባነት ቀጣይነት እንዲኖረው አድርጎታል። የእርሻ መሬት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ሲባል የግጦሽ መሬቶች፣ ዳገታማ መሬቶች፣ ደኖችና ሌሎች በቀላሉ የሚጎዱ ሥነ ምኅዳሮች ለእርሻ ሥራ በመዋላቸው በተለይ የሰሜን ደጋማ አካባቢዎች ከፍተኛ ለሆነ የአፈር መሸርሸርና የውኃ ምንጮች መድረቅና ለአካባቢ መራቆት ተጋልጠዋል።
ዘጠነኛ ቀድሞ የነበረው የመሬት መሸንሸን ከአዋጁም በኋላ ተባባሰ እንጂ አልቀነሰም። የገበሬ ማኅበራቱ ለመሬት አልባ ወጣቶች ሲባል ያልተቋረጠ የመሬት ክፍፍልና ሽንሸና ያደርጉ ስለነበር የነፍስ ወከፍ ይዞታ መጠን ከግማሽ ሔክታር በታች ሆኗል።
- ማጠቃለያ
በዚህ ጽሑፍ በ1967 ዓ.ም. ከነበረው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ ሁኔታ አንፃር የመሬት አዋጁ አይቀሬ እንደነበረ “The writing is on the wall” እንዲሉ፣ የአዋጁ በሚረቀቅበት ወቅት ፅንፈኝነቱን በማለዘብ ለገበሬው የተሻሉ ዕድሎችን ማቅረብ ይቻል እንደነበረ፣ አዋጁ ጠቃሚም ሆነ ጎጂ ገጽታዎች እንዳሉት፣ ዛሬም የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ካለ ሊሻሻል የሚችልባቸው መንገዶች እንዳሉ ተንፀባርቋል። የመሬት አዋጁ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ወደ 23 ሚሊዮን የሚገመት ገበሬ ሕይወትን፣ ዛሬ ደግሞ እስከ 80 ሚሊዮን የሚገመት ገበሬን ሕይወትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚዘውረው በመሆኑ አሁንም ቢሆን ሊፈተሽና ሊሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።
የመሬት አዋጁ ሲረቀቅም ሆነ ሲታወጅ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የተጣጣመ አለመሆኑ ትልቁ ስህተት ነበር። የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ አርሶ አደር የገጠመው ችግር የተለያየ ሆኖ ሳለ አዋጁ ለሁሉም የአገሪቱ ክፍል አንድ ዓይነት የፈውስ መድኃኒት ማቅረቡ ፋይዳውን አሳንሶታል። ለሁሉም ዓይነት ምስማር አንድ ዓይነት መዶሻ አያገለግልምና። ሆኖም አዋጁን በግርድፉ ‹‹አላዋቂው ደርግ ያወጀው›› [11] ብሎ ማጣጣልም ፍርደ ገምድል ያሰኛል። ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የደርግ አባላት እንኳ እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ አዋጁን ሰፊው ማኅበረሰብ ላይ መሞከሩ (social experimentation) ትልቅ ቁማር ነበር። አዋጁ የእርሻ መሬቱን ከባላባቱ መዳፍ አላቀቀ ቢባልም ውሎ አድሮ መሬቱ በመንግሥት ሙሉ ቁጥጥር በመዋሉ የ‹‹መሬት ለአራሹ›› ምላሽ ዛሬም ከሃምሳ ዓመት በኋላ ያልተጨበጠ ጉም ሆኖ ቀርቷል። በውጤቱም ከተበላለጠ ድህነት ወደ እኩል ድህነት ሽግግር ተደርጓል። የመሬት ዋስትና ዕጦቱ ሳቢያ ገበሬው ከገጠር እርሻው እንዳይርቅ ታግቷል፣ የእርሻ መሬቱ በውርስም ሆነ በሌላ እየተሸነሸነ ለዘመናዊ እርሻ እንዲያመች ሆኗል። ምናልባትም መሬቱ በአንድ ስሙ የመንግሥት ነው ተብሎ ቢታወጅ ኖሮ መንግሥት በቀጥታ ተጠያቂነት ኖሮበት አዋጁን ለማሻሻል በፍጥነት ይነሳሳ ነበር።
ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ የመሬት ጉዳይ ከብሔር ማንነት ጋር ተጠላልፎ ተቋጥሯል። በተለይም ላለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት የመሬቱን ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ ለማስተካከል የሚደረግ ሙከራ የብሔር ፖለቲካውን ነርቭ እየነካካ የመፍትሔውን መንገድ አጥብቦታል።
ከመሬት አዋጁ በኋላ የደርጉም ሆነ የኢሕአዴግ መንግሥታት የገበሬውን ችግር ላንዴና ለመጨረሻ ይቀርፋሉ ያሏቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርፀው በርካታ የአገር በጀት፣ የብድርና የዕርዳታ ሀብትን አፍስሰዋል። በጥቂት ማሳዎች ላይ የፕሮግራሞቻቸውን ስኬቶች በሚዲያ ቢያሳዩም የሰፊው ገበሬ ችግር ሲቀንስ አልታየም። ዛሬም ገበሬው የዝናብ ጥገኛ ነው። ከ20 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ በምግብ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ ከመሠረታዊ የኑሮ ደረጃ በታች ይኖራል።
የመሬት ፖሊሲና የብሔር ጉዳይ ሕጋዊ ፍቺ ካላደረጉና በገጠር መሬት ላይ የተከማቸው የገበሬ ቤተሰብ ወደ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ሽግግር ካልተደረገ በቀር፣ ችግሩ ተባብሶ የበለጠ ድህነት፣ የምግብ ዋስትና ማጣት፣ ተረጂነት ይነግሳል። ስለሆነም ይህን 50ኛ የመሬት ለአራሹ አዋጅ የወርቅ ኢዩቤልዩ ተንተርሶ በቀጣይ ሊከወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየቱ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ሊባክን አይገባም።
ምንጮች
[1] ዓለምአንተ ገብረሥላሴ (2024 እኤአ)። ትውስታዎቼ: ስለመሬት ይዞታና የተለያዩ ፖለቲካዊና አገራዊ ገፅታዎች። ዘ ሬድ ሲ ፕሬስ።
[2] ደረሰ አየናቸው (2013)። ሰለሞናውያን፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ (1262-1521)
[3] ዘገየ አስፋው (የካቲት 2016 ዓ.ም)። ከNBC Ethiopia ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ። ዘገየ አስፋው የመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ባልደረባና በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የጭሰኛ ጥናት ኃላፊ፤ በደርግ ዘመን ደግሞ ሚኒስትር ነበሩ።
[4] አንዳርጋቸው አሰግድ (2020 ዓ.ም)። ባጭር የተቀጨ ረዥም ጉዞ፡ መኢሶን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።
[5] ፍስሐ ደስታ (2008 ዓ.ም)። አብዮቱና ትዝታዬ። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።
[6] ኮኸን = Cohen, J. M. (1987). Integrated rural development: the Ethiopian experience and the debate. Nordic Africa Institute.
[7] ብርሃኑ ባይህ (2013)። ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ። የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ። አዲስ አበባ።
[8] ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (2013 እኤአ)። እኛና አብዮቱ። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።
[9] ፋሲካ ሲደልል (2014 ዓ.ም)። ሻምላው ትውልድ። ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት። አዲስ አበባ።
[10] ክፍሉ ታደሰ (1993 ዓ.ም)። ያ ትውልድ ቅጽ 3፡ የለውጥ ማዕበል በኢትዮጵያ የኢሕአፓ ታሪክ፡ 2ኛ ዕትም
[11] መስፍን ወልደማርያም (2012)። መሬት፣ መሬት፣ አንድ። ኢትዮ አንድነት ድረገፅ። https://ethioandinet.wordpress.com/2012/01/09/
[12] ባሕሩ ዘውዴ (1999)። የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ። አዲስ አበባ።
[13] ተስፋዬ ዲንቃ = Tesfaye Dinka (2017)። ETHIOPIA: The Derg Years: An Inside Account. Tsehay Publishers.
[14] ኦታዋይ = Ottaway, M. (1977). Land reform in Ethiopia, 1974-1977. African Studies Review, 20(3), 79-90.
[15] ደሳለኝ ራህመቶ (2024 እኤአ)። ቢቢሲ አማርኛ (19 የካቲት 2024)። መሬት ለአራሹ፡ የገጠሪቱን ኢትዮጵያ መልክ የቀየረው የተማሪዎች ንቅናቄ።
[16] ደሳለኝ ራህመቶ= Dessalegn Rahmato (2011). Land to investors: Large-scale land transfers in Ethiopia (No. 1). African Books Collective.
[17] ያየህ ይራድ ቅጣው። የደርጉ ሚኒስትር የነበሩ የካቲት 2016 ዓ.ም ከNBC Ethiopia ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ።
[18] ውድ = Wood, A. P. (1983). The decline of seasonal labor migration to the coffee forests of South-West Ethiopia. Geography, 68(1), 53-56.
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
