
ከ 9 ሰአት በፊት
ከትናንት በስቲያ በዋይት ሐውስ የታየውን የማይታመን የዲፕሎማሲ ቀውስ ተከትሎ ወደ ለንደን ያቀኑት የዩክሬኑ ዜለንስኪ በ’ዶውኒንግ ስትሪት’፣ ከሰር ኪየር ስታርመር ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በሞቀ ፈገግታ አቅፈው የተቀበሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪየር ስታርመር፣ ለቮሎዲሚር ዜለንስኪ “ዩናይትድ ኪንግደም ለእርስዎ ሙሉ ድጋፍ ትሰጣለች” ብለዋቸዋል።
ዜለንስኪ በበኩላቸው “እንደ ዩኬ ያለ ወዳጅ” በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አጸፋ መልሰዋል።
ዜለንስኪ እና ሰር ኪየር ለዩክሬን ወታደራዊ አቅርቦቶች የሚውል 2.2 ቢሊዮን ፓውንድ ብድር ተፈራርመዋል።
ይህ ብድር የሚከፈለው እንዳይንቀሳቀሱ ከተደረጉ የሩሲያ ንብረቶች ትርፍ ነው።
ሰር ኪየር ከስምምነቱ በኋላ ከትራምፕ እና ከማክሮን ጋር በስልክ መክረዋል። በስልክ ንግግራቸው ምን አንስተው ምን እንደጣሉ የተባለ ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነትን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት መልክ ያስይዛል ተብሎ የሚጠበቀውን የአውሮፓ መሪዎች ጉባኤን ዛሬ እሑድ በለንደን ያስተናግዳሉ።
ሰር ኪየር ከቀናት በፊት ወደ ዋሺንግተን በማቅናት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በዩክሬን ጉዳይ ላይ መምከራቸው አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሆድና ጀርባ እየሆኑ ያሉትን የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካንን በማቀራረብ ረገድ ጉልህ ሚና ለመጫወት ደፋ ቀና ይላሉ።

ሰር ኪየር ስታርመር ዋሺንግተን ባቀኑ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በእንግሊዝ ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ የሚጋብዝና ከንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ የተጻፈ ደብዳቤ ለትራምፕ በእጅ አድርሰው ነበር።
ሆኖም ዋሺንግተን በዜለንስኪ ላይ ያደረሰችውን ዲፕሎማሲያዊ ውክቢያ ተከትሎ አንዳንድ የእንግሊዝ የሕዝብ እንደራሴዎች ይህ ግብዣ እንዲሰረዝ ውስጥ ውስጡን እየወተወቱ ነው ተብሏል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪየር ስታርመር ትራምፕና ምክትላቸው ከዜለንስኪ ጋር በነበራቸው ያልተጠበቀ የቃላት መቆራቆስና የዲፕሎማሲ ኪሳራ ተከትሎ ወደ ሁለቱም ወገኖች በመደወል ‘አንተም ተው-አንተም ተው’ ማለታቸው ተዘግቧል።
ሆኖም ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ‘ለአሜሪካ የሚገባትን ክብር አልሰጠም’ በሚል ከዋይት ሐውስ እንዲለቁ በመጠየቃቸው ሁኔታዎች ሊካረሩ ችለዋል።
ከዚህ ዓለምን ጉድ ካሰኘ የዲፕሎማሲ ውጥንቅጥ በኋላ በቀጥታ ከዋሺንግተን ወደ ለንደን ያቀኑት ዜለንስኪ በ’ዶውኒንግ ስትሪት’ ደጅ የ’አይዞን-ከጎንዎ ነን’ ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ ጠብቋቸዋል።
ሰር ኪየር ለዩክሬን መሪ ሞቅ ያለ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ “የአገሬ ሰዎች ምን ያህል እንደሚደግፉህ ተመልክተሃል?” ብለዋቸዋል።
አክለውም “እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርስዎ እና ከዩክሬን ጎን እንደምንቆም ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ” ብለዋቸዋል።
ዜለንስኪ በበኩላቸው በተመለከቱት ነገር ልባቸው መነካቱን ጠቁመው ‘ለሁሉም ከልቤ አመሰግናለሁ’ ብለዋል።
ዜለንስኪ በጠየቁት መሠረትም ዛሬ እሑድ ከንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ ጋር ይገናኛሉ።
ከዳውኒንግ ስትሪት አጭር ስብሰባ በኋላ ዜለንስኪ እንደተናገሩት የዩናይትድ ኪንግደም የ2.2 ቢሊዮን ፓውንድ ብድር በዩክሬን ውስጥ የጦር መሣሪያ ለማምረት እንደሚውል ተናግረዋል።
ገንዘቡ ከሩሲያ ኪስ የሚከፈል ይሆናል።
“ይህ ፍትሐዊ አሠራር ነው – ጦርነቱን የጀመረው ነው ዕዳውን መክፈል ያለበት ” ብለዋል።
ሩሲያ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ንብረቷ እንዳይንቀሳቀስ ሆኗል።
ዛሬ እሑድ በለንደን የሚጀመረው ጉባኤ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
አሜሪካ በቅድመ ድርድሩ ዩክሬንንም ሆነ የአውሮፓ ኅብረትን ገሸሽ ማድረጓ በተለይ ለአውሮፓ መሪዎች ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።
የዛሬው ጉባኤ በዋናነት ዩክሬን ከስምምነት በኋላ የደኅንነት ዋስትና የምታገኝበትን መንገድ ያፈላልጋል።
ከዚህ ሌላ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው ድጋፍ ማቋረጧን ተከትሎ የሚፈጠረው ክፍተት እንዴት ይሞላ በሚለው ዙርያ ንግግሮች ይደረጋሉ።
በቅርቡ በፓሪስ በተደረገ ተመሳሳይ ጉባኤ ዩኬ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።
ሆኖም አሜሪካ ተጨማሪ የደኅንነት ዋስትና እንድትሰጣት ትሻለች።
ትራምፕ በበኩላቸው ምንም ዓይነት ወታደር ወደ ዩክሬን እንደማያሰማሩ በማያሻማ ሁኔታ ተናግረዋል።
ሆኖም መንግሥታቸው የከበሩ ማዕድናትን ለማውጣት በዚያ መሰማራቱ በራሱ እንደ ደኅንነት ዋስትና እንዲታይ ይፈልጋሉ።
ትራምፕ፣ እኛ ወደ ዩክሬን ማዕድን ለማውጣት ከገባን ፑቲን አይተናኮሱም ብለው ያምናሉ።
ዓርብ በዜለንስኪና በትራምፕ መካከል ጄዲ ቫንስን ያካተተ ዲፕሎማሲያዊ መተነኳኮስን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጥ እርዳታ እንዲቆም ተእዛዝ ሰጥተዋል የሚሉ መረጃዎች ከወደ አሜሪካ መሰማት ጀምረዋል።
ሦስት ዓመት ያለፈው የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በካርኪቭ በድሮን ጥቃት በርካታ ዩክሬናዊያን መቁሰላቸው ተዘግቧል።
ሩሲያ በበኩሏ ከዩክሬን የተተኮሱ 84 ድሮኖችን ማክሸፏን ተናግራለች።