
ከ 5 ሰአት በፊት
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አርብ ዕለት ዋይት ሐውስ ደርሰው ከመኪናቸው እንደወረዱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስቀድመው አስተያየት የሰጡት ስለ አለባበሳቸው ነበር።
ዜሌንስኪ በወታደራዊ የደንብ ልብስ አምሳያ የተሠራውን ጥቁር ሹራባቸውን ለብሰው ከመኪና ሲወርዱ፣ ትራምፕ ለሰላምታ እጃቸውን እየዘረጉ “ዛሬ ደግሞ ዘንጠሃል” ሲሉ ተናገሩ።
በእርግጥ በወቅቱ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ሙገሳ ይሁን ሽንቆጣ የተረዳ አልነበረም።
ዜሌንስኪ ሱፍ፣ ሸሚዝ እና ከረባትን ከተጠየፉ ሦስት ዓመት ሞላቸው።
አገራቸው ከሩሲያ ጋር በተለያዩ ግንባሮች ልጆቿን አሰልፋ መዋጋት ከጀመረችበት ዕለት አንስቶ ዜሌንስኪ ከዓለም መሪዎች ጋር በሚያደርጓቸው ወሳኝ ስብሰባዎች፣ ለአሜሪካ ኮንግረስ ንግግር ሲያደርጉ ለወታደሮቻቸው አጋርነታቸውን ለማሳየት በሚል ይህንን አለባበስ መርጠዋል።
ይህ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ዕርዳታ ለሚተቹ ሰዎች ሲያናድድ ቆይቷል።
በአንዳንድ የቀኝ ክንፍ ተቺዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረው ይህ ጉዳይ፣ አርብ ዕለት ዜሌንስኪ ከትራምፕ እና ከምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋር በኦቫል ኦፊስ በነበራቸው ስብሰባ ላይ የዓለምን ቀልብ እና ዓይን የሳበ ጉዳይ ሆኖ ብቅ አለ።
አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ለዜሌንስኪ ዕለቱን የሚመጥን ልብስ አልለበሱም፤ ተገቢውን እና የሚመጥነውን አክብሮት አላሳዩም ሲል የጠየቀው ጥያቄ በቤቱ ውስጥ የነበረውን ድባብ በፍጥነት ቀየረው።
እናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ‘የአክብሮት እና የምስጋና ጉዳዮች’ በዶናልድ ትራምፕ እና በምክትል ፕሬዝዳንታቸው አፍ ላይ ተመላለሰ።
የአውሮፓ አጋራቸውን በዓለም የቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ሲነቅፉ እና ሲዘልፉም ተስተዋለ።
ስብሰባው ከጋዜጠኞች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ሲከፈት ከወግ አጥባቂ ሚዲያ፣ ከሪል አሜሪካስ ቮይስ (የአሜሪካውያን እውነተኛ ድምጽ) የመጣው ብራያን ግሌን፣ አንዲት ጫፏ የሾለ ጥያቄ ወረወረ።
ግሌን “ለምን ሱፍ ልብስ አልለበሱም?” ሲል ነበር የጠየቀው። “በዚህ አገር ትልቅ የሆነው ቢሮ ውስጥ ነው ያሉት፤ ነገር ግን ሱፍ ለመልበስ ፈቃደኛ አይደሉም።”
“ለመሆኑ ሱፍ አለዎት?” ሲል ቀጠለ። “ብዙ አሜሪካውያን ለዚህ ቢሮ ተገቢውን ክብር ባለመስጠትዎ ቅሬታ አላቸው።”
ይህች እንደ ዘበት የተሰነዘረች ጥያቄ የዜሌንስኪን የትዕግስት ከረጢት በቀላሉ ነው የሸነቆረችው።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት እስከዚያች ደቂቃ ድረስ ከትራምፕ ጋር ዲፕሎማሲያዊ በሆነ ሁኔታ፣ ወዳጅነት በተመላበት ቃና ንግግር ላይ የነበሩ ቢመስልም፣ ይህች መዘዘኛ ጥያቄ መናደዳቸውን እና መሰላቸታቸውን እንዳይሸሽጉ አደረገቻቸው።
ዜሌንስኪ “ይህ ጦርነት ካበቃ በኋላ እንደሱ እለብሳለሁ” ሲሉ መለሱ።
ከዚያም የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከጋዜጠኛው ጋር ጥቂት የቃላት ጠጠር ተወራወሩ።
“ምናልባት እንዳንተ ዓይነት፤ አዎ። ምናልባትም ደግሞ የተሻለ ነገር፤ አላውቅም” ካሉ በኋላ በቤቱ ውስጥ ሳቅ ሞላ። “ምናልባትም ደግሞ ረከስ ያለ ነገር ሊሆን ይችላል።”
የግሌን ጥያቄ በግዙፉ የአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሲብላላ የቆየውን ስሜት ገንፍሎ እንዲወጣ አድርጎታል።
እንደ ጄዲ ቫንስ ያሉ አንዳንዶች የዩክሬኑ መሪ አሜሪካ ለሦስት ዓመታት ስትሰጠው ለነበረው ወታደራዊ ዕርዳታ በቂ ምስጋናም ሆነ ክብር አላሳዩም የሚል የውስጥ ለውስጥ ጉምጉምታ ነበረባቸው።
ጋዜጠኛው ግሌን ቅልጥ ያለ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ነው።
ባለፈው ዓመት ለ’ፖሊቲኮ’ እንደተናገረው ከሆነ “የፕሬዚዳንት ትራምፕ እና አሜሪካ ትቅደም የሚለው አጀንዳቸው መቶ በመቶ ደጋፊ ነኝ” ብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2020 የተመሠረተው የሪል አሜሪካስ ቮይስ በአንፃራዊነት ግልፅ ያልሆነ የቀኝ ክንፍ የዜና ማሠራጫ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተፈጠሩት የትራምፕ ደጋፊ መገናኛ ብዙኃን አንዱ ነው።
በጣቢያው ላይ የሚቀርቡ እንግዶችም ሆኑ አቅራቢዎቹ የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን፣ የ2021 የካፒቶል ግርግር በተመለከተ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሴራ ትንተና ንድፈ ሃሳቦችን ያሠራጫሉ።
በጣቢያው ዝግጅቶች ላይ የትራምፕ የቀድሞ ዋና አማካሪ ስቲቭ ባነን፣ የፖለቲካ አክቲቪስት ቴድ ኑጀንት እና የወግ አጥባቂ ቡድን መሥራች የሆነው ቻርሊ ኪርክን ጨምሮ ከግዙፉ የፖለቲካ ዓለም የሚመጡ ትልልቅ ስም ያላቸውን ይጋበዛሉ።
ቢቢሲ ጣቢያው በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል።
ከዋይት ሐውሱ እሰጣ አገባ በኋላ ግሌን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገጹ ላይ “ለዩክሬን ሕዝብ በጣም ርኅራኄ አለኝ” ነገር ግን የዜሌንስኪ አለባበስ ለአሜሪካ ያለውን “ውስጣዊ ንቀት” ያሳያል ሲል ለጥፏል።
በዜሌንስኪ ወገን የሚሰለፉ ተሟጋቾች ደግሞ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ዊንስተን ቸርችል ቀለል ያለ ልብስ ለብሰው የሚያሳዩ ምሥሎችን አጋርተዋል።

ከግሌን ጥያቄ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫው አሜሪካ ወደ ዩክሬን ተጨማሪ ጦር ትልክ እንደሆነ የሚል ጥያቄ ላይ አተኩሮ ቆየ።
በመልሱ መጨረሻ ላይ ትራምፕ የዜሌንስኪ አለባበስ ላይ የተነሳውን ጥያቄ መልሰው ጠቅሰዋል።
“አለባበስህን ወድጄዋለሁ” ካሉ በኋላ ወደ ዜሌንስኪ እያመለከቱ “በሚያምር መልኩ የለበሰ ይመስለኛል” አሉ።
ከዚህ ንግግር በስተጀርባ የትራምፕ አመለካከት ትንሽ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ዘገባዎች ጠቁመዋል።
አክሲዮስ የተሰኘው መገናኛ ብዙኃን ከስብሰባው በፊት የዋይት ሐውስ ሠራተኞች ዜሌንስኪ ሱፍ እንዲለብስ መጠየቃቸውን እና በኋላም ቅር እንደተሰኙ ዘግቧል።
ሆኖም ሁለቱ የዓለም መሪዎች ባልተለመደ መልኩ ክርክር ከመጀመራቸው በፊት ለ20 ደቂቃዎች ያህል ይብዛም ይነስ በአክብሮት፣ በምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ እስኪቋረጥ ድረስ፣ ጥያቄዎችን መቀበላቸውን እና መመለሳቸውን ቀጥለዋል።
ቫንስ ደጋግሞ “አክብሮትን” እያነሳ፣ ዜሌንስኪን “ክቡር ፕሬዝዳንት” እያለ፣ የዩክሬን መሪ ደግሞ “ጄዲ” ሲሉ እየጠሩት አውርተዋል።
“ወደ ኦቫል ኦፊስ [የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት] መጥተህ፣ በአሜሪካ ሚዲያ ፊት ለፊት ለመውቀስ መሞከርህ አክብሮት የጎደለው ይመስለኛል” ነበር ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ።
ውይይቱ ከዚያ በኋላ የቁልቁለት ጉዞውን ተያያዘው።
ዕለቱን እና ቦታውን በሚመጥን መልኩ ሽክ አላሉም የተባሉት ዜሌንስኪ ከዋይት ሐውስ እንዲወጡ ተደረገ።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት አዲስ ዝቅታ ውስጥ መሆኑም ፍንትው ብሎ ታየ።