ፍልስጤማውያን በጋዛ

ከ 5 ሰአት በፊት

የእስራኤል መንግሥት ከሃማስ ጋር የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በመጠናቀቁ ምክንያት ማንኛውም የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ማገዱን አስታወቀ።

የጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ሃማስ እስካሁን ድረስ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መልዕክተኛ፣ ስቲቭ ዊትኮፍ፣ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ማራዘሚያ አልቀበልም ማለቱን ተናግሯል።

የሃማስ ቃል አቀባይ እርምጃውን “ርካሽ ውንጀላ” እና የተኩስ አቁም ስምምነት “ግልበጣ” በማለት እስራኤል የእርዳታ አቅርቦቷን እንድትቀጥል አሸማጋዮቹን አሳስበዋል።

ሃማስ የድርድሩ ቀጣይ ምዕራፍ መጀመርያ በተደረገው ድርድር መሰረት ታጋቾችን እና የፍልስጤም እስረኞችን በመፍታት እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ በማስወጣት እንዲቀጥል ይፈልጋል።

አርብ ምሽት ላይ ሃማስ የድርድር ቀጣይ ምዕራፍ እንደሚካሄድ ከአሜሪካ፣ ከኳታር እና ከግብፅ ሸምጋዮች ዋስትና ካላገኘ በስተቀር በምዕራፍ አንድ የተኩስ አቁም ማራዘም እንደማይስማማ ተናግሮ ነበር።

በኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት መግለጫ መሰረት፡ “የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመርያ ምዕራፍ በማብቃቱ እና ሃማስ ለቀጣይ ንግግሮች የዊትኮፍ መግለጫን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ እስራኤል ተስማምታለች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚገቡ እቃዎች እና አቅርቦቶች በሙሉ እንዲቆሙ ወስነዋል።

የሃማስ ቃል አቀባይ “ኔታንያሁ ዕርዳታ ወደ ጋዛ መግባቱን ለማቆም መወሰናቸው የእስራኤልን ወረራ አስቀያሚ ገጽታ ያሳያል…የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የእስራኤል መንግሥት ሕዝባችንን ማስራቡን እንዲያቆም ግፊት ማድረግ አለበት” ብለዋል።

ትናንት ማምሻውን የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት እንደተናገረው አሜሪካ በረመዳን እና በአይሁዶች የፋሲካ በዓል ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለስድስት ሳምንታት ያህል እንዲቀጥል ባቀረበችው ሀሳብ የእስራኤል መንግሥት ተስማምቷል።

በዚህ የተኩስ አቁም ማብቂያ ላይ ድርድሩ ውጤት አልባ ከሆነ እስራኤል ወደ ጦርነት የመመለስ መብቷ የተጠበቀ ነው።

የአሜሪካው ተወካይ ዊትኮፍ ሃሳቡን ለሕዝብ ይፋ አላደረጉም።

እንደ እስራኤል ገለጻ የተኩስ አቁሙ ከቀሩት በሕይወት ያሉ እና የሞቱ ታጋቾች መካከል ግማሹን በመልቀቅ ይጀምራል።

የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ሃማስ በስድስት ሳምንት የተኩስ አቁም ማራዘሚያ ላይ አቋሙን ከቀየረ እስራኤል ወዲያውኑ ድርድር ትጀምራለች ብሏል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በጥር 19 ተግባራዊ የሆነው የተኩስ አቁም የመጀመሪያው ምዕራፍ ትናንት፣ ቅዳሜ ዕለት፣ አብቅቷል።

ስምምነቱ በሃማስ እና በእስራኤል ጦር መካከል ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት በማቆም 33 እስራኤላውያን እና አምስት የታይላንድ ታጋቾችን እንዲሁም 1,900 የሚሆኑ የፍልስጤም እስረኞች ነጻ እንዲወጡ አስችሏል።

ነገር ግን በቀጣይ ቀሪ ታጋቾችን ማስልቀቅ እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ የሚጠይቀው የድርድር ምዕራፍ ገና አልተጀመረም።

አሁንም 24 ታጋቾች በሃማስ እጅ በሕይወት እንዳሉ ሲገመት ሌሎች 39 ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።

ሃማስ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 7 2023 በእስራኤል ላይ በድንገት ጥቃት ፈጽሞ፣ ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ 251 ደግሞ ታግተዋል።

እስራኤል ለጥቃቱ በጋዛ ሰርጥ ባደረገችው የአየር እና የምድር ዘመቻ ምላሽ የሰጠች ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ቢያንስ 48,365 ሰዎች መሞታቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።