በዩክሬን የሚገኘው ሊቲየም ማዕድን በዓለት ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ይነገራል
የምስሉ መግለጫ,በዩክሬን የሚገኘው የሊቲየም ማዕድን በዓለት ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ይነገራል

2 መጋቢት 2025

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በዋሽንግተን “በጣም ትልቅ” የተባለውን ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ቢጠበቅም አደባባይ የወጣ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ሳይሳካ ቀርቷል።

ኪየቭ እና ዋሽንግተን፣ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ለሰጠችው እርዳታ ከዩክሬን የማዕድን ሀብት ድርሻ ለማግኘት ንግግር ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በምላሹም ዩክሬን የደኅንነት ዋስትና ከአሜሪካ በኩል ማግኘት ትፈልጋለች።

ምንም እንኳን ከፍተኛ መጠን ያለው ማዕድናት በሩሲያ በተያዙ ግዛቶቿ ውስጥ ላይ ቢገኙም፣ ትራምፕ የተለያዩ ተፈላጊ ለሆኑ ባትሪዎች እና ለከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚያገለግሉ ማዕድናት ላይ ፍላጎት አላቸው።

ዩክሬን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ በኮምፒውተሮች እና በሞባይል ስልኮች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉት ባትሪዎች ዋና አካል የሆነው የሊቲየም ማዕድን ከፍተኛ ክምችት እንዳላት ይታመናል።

ከእነዚህ ማዕድናት ውስጥ አንዳቸውም ወጥተው ጥቅም ላይ አልዋሉም።

ምንም እንኳ አሜሪካ የራሷ በጣም ከፍተኛ የሊቲየም ክምችት ያላት ቢሆንም የራሷን አውጥታ ከመጠቀም ይልቅ ዓይኗን ዩክሬን ላይ ጥላለች። ለምን ?

ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ

ዩክሬን ምን ያህል የሊቲየም ክምችት አላት?

የዩክሬን ጂኦሎጂካል አገልግሎት አገሪቱ ከአውሮፓ ትልቅ የሆነ፣ በግምት 500,000 ቶን ሊቲየም አላት ሲል አስቀምጧል።

የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ በበኩሉ በአውሮፓውያኑ 2021 በምድር ላይ ያለው አጠቃላይ የሊቲየም መጠን 71 ሚሊዮን ቶን እንደነበር ገምቷል።

በዓለም ላይ ሊቲየምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቱት አገራት አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ቺሊ እና ቻይና ናቸው።

በአሜሪካ እና በቻይና ውስጥም ሌሎች ትላልቅ ክምችቶች ተገኝተዋል።

በዓለም ላይ ከሚመረተው ሦስት አራተኛው ሊቲየም እንደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ ኮምፒውተሮች እና ሞባይል ስልኮች ባሉ ባትሪዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል።

በሶቭየት ኅብረት ዘመን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በማዕከላዊ ዩክሬን ውስጥ በፖሎኪቪስኬ እና ዶብራ እንዲሁም አሁን በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው ክሩታ ባልካ ክልል ውስጥ የሊቲየም ክምችቶች ይገኛሉ።

አንድ የማዕድን ኩባንያ በአውሮፓውያኑ 2017 ሊቲየም ለማውጣት ፍቃድ አግኝቶ በፖሎኪቪስኬ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ይኹን እንጂ በዩክሬን የሚገኘው የበርሚንግሃም ወሳኝ ንጥረ ነገሮች እና ቁሶች ማዕከል ባልደረባ ፕሮፌሰር ፖል አንደርሰን “በዩክሬን የማዕድን አቅርቦቶች ላይ ያለው መረጃ ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ ማንም እርግጠኛ አይደለም፤ ዩክሬናውያን ዋጋቸውን እያዋደዱ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

አሜሪካ በኔቫዳ ውስጥ የሚገኘው እና ሲልቨር ፒክ ተብሎ የሚታወቀው አንድ የሊቲየም ማዕድን ማውጫ ብቻ ነው ያላት

አሜሪካ ምን ያህል ሊቲየም አላት?

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ስርቬይ በ2021 አሜሪካ በግምት 8.3 ሚሊዮን ቶን የሊቲየም ክምችት እንዳላት ገልጿል።

ከዚያም፣ በጥቅምት 2024 ቢያንስ 4.5 ሚሊዮን ቶን የያዘ ሌላ ግዙፍ የሊቲየም ክምችት በአርካንሳስ መገኘቱን አስታውቋል።

ሆኖም፣ አሜሪካ በኔቫዳ ውስጥ የሚገኘው እና ሲልቨር ፒክ ተብሎ የሚታወቀው አንድ የሊቲየም ማዕድን ማውጫ ብቻ ነው ያላት።

በእንግሊዝ በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የብረታ ብረት እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ጋቪን ሃርፐር “ሌሎች አገራት ሊቲየም ማዕድንን ቆፍረው ማውጣታቸው እና በርካሽ በማቅረባቸው የተነሳ የማዕድን ቁፋሮው እንዲቀዛቀዝ ሆኗል” ብለዋል።

ፕሮፌሰር አንደርሰን “በአሜሪካ ውስጥ የባትሪውን ኢንዱስትሪ ዕድገት አስቀድሞ የተነበየ ማንም የለም” ሲሉ በዘርፉ ላይ የነበረውን ድክመት ጠቅሰዋል።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ እንደሚለው አገሪቱ አሁን ከምትጠቀምበት ሊቲየም ግማሹን በአብዛኛው ከቺሊ እና ከአርጀንቲና ታስገባለች።

ቻይና 75 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሊቲየም-አዮን ባትሪ የመስራት አቅም እንዳላት

አሜሪካ ለምን የዩክሬን ሊቲየምን ፈለገች?

ቻይና 16.5 በመቶውን የዓለም የሊቲየም ክምችት የያዘች ሲሆን፣ 60 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሊቲየም ማጣራት ብቻ ሳይሆን 75 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሊቲየም-አዮን ባትሪ የመሥራት አቅም እንዳላት ተንታኞች ይናገራሉ።

“ቻይና በሊቲየም ባትሪ ምርት ግንባር ቀደም መሆን ብቻ ሳይሆን የዘርፉን ፍላጎት ተመልክቶ በዕቅድ በማዳበር ረገድ ቀዳሚ ነበረች” ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት፣ ቻይና ሊቲየም እና የሌሎች ወሳኝ ማዕድናት አቅርቦትን በመቆጣጠር የበላይነት ልትይዝ ትችላለች የሚል ስጋት አለው።

እንደ ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ባለሥልጣን መረጃ ከሆነ የዓለም የሊቲየም ፍላጎት በ2023 ከነበረው አንጻር በ2040 ከስምንት እጥፍ በላይ ይጨምራል።

ጆ ባይደን በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የአሜሪካ መንግሥት ባፀደቀው የዋጋ ግሽበት ቅነሳ ሕግ ላይ ተመሥርቶ ለማዕድን ኩባንያዎች ብድር በመስጠት በአገር ውስጥ ብዙ ሊቲየም እንዲያመርቱ ለማሳመን ጥረት አድርጎ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ለጦር መሳርያዎቹ ባትሪ ለመሥራት እንዲያስችለው ሊቲየም እንዲቀርብለት በሚል በካሮላይና የሚገኘውን የኪንግስ ማውንቴን ማዕድን ማውጫን ለመክፈት ብድር ለመስጠት ተስማምቷል።

ፕሮፌሰር አንደርሰን “በአሜሪካ ውስጥ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ከአብዛኞቹ ከምንም ነገር በላይ ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ለወታደራዊ ምርት እንደሚፈልጉ ተረድቻለሁ።”

ነገር ግን “ትራምፕ በዩክሬን ብርቅዬ ማዕድናት ክምችት ላይ በጣም ፍላጎት ያላቸው ይመስላል” ሲሉ አክለዋል።

በ36 ሚሊዮን ቶን የሚገመቱ አዲስ የሊቲየም ክምችቶች በቅርቡ በኔቫዳ የተገኙ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2026 የማዕድን ማውጣት ለመጀመር ዕቅድ ተይዟል።

በአውስትራሊያ የሚገኝ የሊቲየም ማዕድን ማውጫ
የምስሉ መግለጫ,በአውስትራሊያ የሚገኝ የሊቲየም ማዕድን ማውጫ

የዩክሬን ሊቲየም ለአሜሪካ ምን ያህል አዋጪ ነው?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታካሄደው ጦርነት አገራቸው ድጋፍ በማድረጓ የማዕድን ሀብቷን ድርሻ እንድትሰጥ ይፈልጋሉ።

ይኹን እንጂ ማዕድን ለማውጣት የሚያስፈልገው ወጪ ተሰልቶ ሊቲየም እና ሌሎች ማዕድናት በገበያ ምን ያህል ዋጋ እንደሚኖራቸው አይታወቅም ይላሉ ፕሮፌሰር አንደርሰን።

“የእነዚህን ክምችቶችን ጥራት አናውቅም፤ በኢኮኖሚ አዋጭ ቢሆኑም እንኳ ወደ ገበያ ለመምጣት አሥር ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድባቸው ይችላል። ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት እና ካፒታልም ይጠይቃሉ።”

ዶ/ር ሃርፐር “በዩክሬን ውስጥ ማዕድንን ማውጣት በተለይ በጦርነቱ እና ባደረሰው ጉዳት የተነሳ ፈታኝ ነው” ብለዋል።

የዲኒፕሮ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዘገባ በዩክሬን የሚገኘው ሊቲየም በዓለት ውስጥ ስለሚገኝ ለማውጣት በአንጻራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ እና ውድ መሆኑን አመልክቷል።

በንጽጽር እንደ አውስትራሊያ እና ቺሊ ባሉ አገራት ሊቲየም ከጨው ግግሮች ንጣፍ ስር በቀላሉ ይገኛል።

በዚህ ምክንያት ሊቲየምን ዩክሬን ውስጥ ካለው ክምችት ለማውጣት አዋጭ ይሁን አይሁን አይታወቅም ይላል ዘገባው።

ኩባንያዎች በአሁኑ ጊዜ በሊቲየም ማዕድን ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የማይፈልጉበት ሌላው ምክንያት የምርቱ ዋጋ ባለፈው ዓመት በመውደቁ ነው።

አሁን ያለው የማዕድኑ የገበያ ዋጋ በ2022 ከነበረው 80 በመቶ ያነሰ ሲሆን፣ ይህ የሆነበት ምክንያትም በአቅርቦቱ ውስጥ ባለው መትረፍረፍ ምክንያት ነው።

በዚህም የተነሳ ኩባንያዎች በዩክሬን ወይም በተቀረው ዓለም አዲስ ማዕድን ለማውጣት ያላቸውን ፍላጎት ሊቀንስ ይችላል።

ፕሮፌሰር አንደርሰን “የዋጋውን መውደቅ ተከትሎ፣ ማዕድን አውጪዎች ለጥቂት ዓመታት ይህን ቦታ እንዳለ እንዲቆይ ይፈልጉ ይሆናል” ይላሉ።