
ከ 5 ሰአት በፊት
በአሜሪካ ፕሬዚዳንት እና ምክትላቸው ዘለፋን ጨምሮ ኃይለቃልን ያስተናገዱት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነት ለመፈራረም አሁንም ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ አመራሮች ጋር የነበረው ንግግር ባይሳካም አሁንም ከአሜሪካ ጋር “ገንቢ ውይይት” ለማድረግ እንደሚፈልጉ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ላውራ ኩንስበርግ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ዜሌንስኪ “የዩክሬን አቋም እንዲሰማ እንፈልጋለን።” ብለዋል።
አክለውም “በዚህ ጦርነት ወራሪው ማን እንደሆነ አጋሮቻችን እንዲያስታውሱ እንፈልጋለን” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ለጦርነቱ ሰላማዊ እልባት ለማግኘት የተናጠል ውይይት ከሩሲያ መሪዎች ጋር ማድረጉን ተከትሎ የአሜሪካ እና የዩክሬን ግንኙነት ሻክሯል።
ይህንንም ተከትሎ ዩክሬን ብርቅዬ የሆነውን ማዕድኗን ለአሜሪካ በመስጠት የአገራቱ ግንኙነት ይሻሽላል እንዲሁም ዩክሬን የጸጥታ ዋስትና ታገኛለች የሚል ተስፋ ፈጥሮ ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ሳምንት አርብ ዋይት ሃውስ በነበረው ውይይት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ የዩክሬኑን መሪ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ፊት ሲገስጿቸው፣ ሲያሸማቅቋቸው እና ሲወርፏቸው ታይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ስምምነቱን ከመፈረማቸው በፊት ዋይት ሃውስን ለቀው እንዲወጡ በአሜሪካ ባለስልጣናት ተነግሯቸዋል።
- ትራምፕ የዩክሬኑ መሪን ‘በሦስተኛው የዓለም ጦርነት ቁማር እየተጫወትክ ነው’ ሲሉ ወረፏቸው1 መጋቢት 2025
- ዜሌንስኪ ከዋይት ሃውስ እንዲወጡ የተደረገበት የዲፕሎማሲ ቀውስ ላይ እንዴት ተደረሰ?1 መጋቢት 2025
- ዓለምን እያነጋገረ ያለው የትራምፕ እና የዜሌንስኪ ጭቅጭቅ በዋሽንግተን1 መጋቢት 2025
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዋና ጸሐፊ ስኮት ቤንሰንት “ያለ ሰላም ስምምነት የምጣኔ ስምምነት ማድረግ አይቻልም” ሲሉ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ መናገራቸውን ተከትሎ ነው ዜሌንስኪ የማዕድን ስምምነቱን መፈረም እፈልጋለሁ ያሉት።
ቤንሰንት እንዳሉት ዜሌንስኪ የማዕድን እና የሰላም ስምምነቱን እንዴት ሊከናወኑ እንደሚገባቸው “ቅደም ተከተሉን ጥሷል” ሲሉ ወቅሰዋቸዋል። አክለውም “በግል መካሄድ የሚገባችውን ውይይት የአደባባይ ሙግት ለማድረግ መርጠዋል” ሲሉም የአሜሪካው ባለስልጣን ተችተዋቸዋል።
እሁድ እለት በለንደን ከተካሄደው የአውሮፓ መሪዎች ጉባኤ በኋላ የተናገሩት ዜሌንስኪ በቅርቡ በዋሽንግተን የተደረገው ኃይለ ቃል የተሞላበት ሙግት አጋር አገራቱን፣ አሜሪካ እና ዩክሬንን አይጠቅምም ብለዋል። ይህ የሚጠቅመው የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ብቻ ነው ሲሉ በጉባኤው ላይ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
ሆኖም አሁንም በአሜሪካ ባለስልጣናት የሚጋበዙ ከሆነ ወደ ዋይት ሃውስ እንደሚመለሱ ዜሌንስኪ ተናግረዋል። ነገር ግን ሩሲያ የወረረቻቸውን የዩክሬን ግዛቶች ለሩሲያ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ዩክሬን በወረራ የተያዘባትን ግዛቶች እንዳሉ መተው የሰላም ስምምነቱ አካል ሊያደርጉት እንደሚችል ፍንጮች ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር የነበራቸውን ውይይት ወደ ጸብ ማምራቱ እንደጸጸታቸውም ጠቆም አድርገዋል። ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ 20 በመቶ የሚሆነውን ግዛቷን ተቆጣጥራ ትገኛለች።