
ከ 5 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እና አገሪቷን ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል አራት ነጥቦችን የያዘ ዕቅድ ይፋ አደረጉ።
ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች አገራት በጥምረቱ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ስታርመር፣ ዩክሬንን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት አሜሪካ እንድትቀላቀል እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
ስታርመር የዩክሬኑን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ በአብዛኛው ከአውሮፓ የሆኑ 18 መሪዎች በተሳተፉበት ጉባኤ ” በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለነው።” ብለዋል።
በዋሽንግተን ከፍተኛ ዘለፋን ያስተናገዱት ዜሌንስኪ በበኩላቸው “ዩክሬን ጠንካራ ድጋፍ እንዳላት ተሰምቷታል፤ ጉባኤውም ለረዥም ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአውሮፓ አንድነት አሳይቷል።” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ያሉት በዩክሬኑ መሪ እና በአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል በዋይት ሃውስ ኃይለ ቃል ልውውጥ ከተደረገ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።
ዜሌንስኪ ከጉባኤው በኋላ ” ለእውነተኛ ሰላም እና የደኅንነት ዋስትና ከአሜሪካ ጋር ትብብር ለመፍጠር በአውሮፓ ሁላችንም አንድ ላይ እየሰራን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
- ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትላቸውን ያስቆጣው የዜሌንስኪ አለባበስ2 መጋቢት 2025
- በትራምፕ የተገፉት ዜለንስኪ ከዩኬ የ2.2 ቢሊየን ፓውንድ ብድር አገኙ2 መጋቢት 2025
- አሜሪካ ተፈላጊው የሊቲየም ማዕድን እያላት ትራምፕ ለምን ከዩክሬን ለመውሰድ ፈለጉ?2 መጋቢት 2025
ከመሪዎቹ ጉባኤ በኋላ ስታርመር በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት መሪዎቹ በአራት ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ነጥቦች፦
- ወደ ዩክሬን የጦር ድጋፍ ፍሰትን ማጠናከር እና በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና መፍጠር፣
- ማንኛውም የሚደረግ የሰላም ስምምነት የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት እንዲያረጋግጥ እና በማንኛውም የሰላም ንግግር መሳተፍ እንዳለባት፣
- በሰላም ስምምነት ወቅትም ሌላ ወረራ እንዳይፈፀምባት የዩክሬንን መከላከያ ማጠናከር እና
- ዩክሬንን ለመከላከል እና የሰላም ዋስትና ለመስጠት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተውን ጥምረት ማጠናከር የሚሉት ናቸው።
ሰር ኬር ስታርመር ጨምረውም ዩክሬን ከ5 ሺህ በላይ የአየር መከላከያ ሚሳኤሎችን እንድትገዛ ተጨማሪ 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
ዩኬ ቀደም ብሎ ከታገዱት የሩሲያ ንብረቶች ከተገኘው ትርፍ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር ድጋፍ ለማድረግ የ2.2 ሚሊዮን ፓውንድ ብድር ለመስጠት ቃል ገብታለች።
” ከባለፈው ስህተታችን መማር አለብን፤ ሩሲያ በቀላሉ ልትጥሰው የምትችለውን ደካማ ስምምነትን መቀበል አንችልም። ማንኛውም ስምምነት ጠንካራ መሆን አለበት” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥምረቱን ለመቀላቀል የተስማሙ አገራት የትኞቹ እንደሆኑ አልጠቀሱም።ሆኖም ቁርጠኛ የሆኑት በአስቸኳይ እቅዱን እንደሚያጠናክሩ፤ አገራቸው ዩኬም በማንኛውም መልኩ ኃላፊነቷን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።
ስታርመር ለስምምነቱ የአሜሪካ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እና ሩሲያን ማካተት እንደነበረበት ከመናገራቸው አስቀድሞ ” አውሮፓ ከባዱን ነገር መሸከም አለባት” ብለዋል።
” ዘላቂነት ያለው ሰላም በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ ከትራምፕ ጋር ተስማምተናል። አሁን ይህንን በጋራ ማድረግ አለብን” ሲሉም አብራርተዋል።
በትራምፕ አስተዳዳር ሥር ያለችው አሜሪካ ተጨባጭ አጋር አልነበረችም ተብሎ ከተጠየቀም ” ባለፈው አርብ የተከሰተውን ማንም ሊያየው አይፈልግም፤ ነገር ግን አሜሪካ ተጨባጭ አጋር አይደለችም የሚለውን አልቀበልም” ብለዋል ስታርመር።
በጉባኤው ላይ ፈረንሳይ ፣ ፖላንድ፣ቱርክ፣ ኖርዌይ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ፣ ዴንማርክ ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ፣ ሮማኒያ ፣ ፊንላንድ ፣ ጣልያን ፣ ስፔን እና ካናዳ ተሳትፈዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ዲር ሊየንም ‘አውሮፓን እንደገና የማስታጠቅ አስቸኳይ ፍላጎት’ እንዳለ በጉባኤው ላይ ተናግረዋል።
ይህ ንግግራቸው በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ( ኔቶ) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩቴም ተስተጋብቷል።
ከጉባኤው በኋላ ዜሌንስኪ ከንጉስ ቻርለስ ሦስተኛ ጋር ወደ ተገናኙበት ሳንድሪንግሃም አቅንተዋል።
በኋላ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም አሁንም ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነቱን ለመፈረም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዩክሬን የጸጥታ ዋስትና ለማግኘት ብርቅዬ የሆነውን ማዕድኗን ለአሜሪካ ለመስጠት ቀደም ብላ ተስማምታ የነበረ ሲሆን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ከፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዋሽንግተን በነበራቸው ቆይታ ያልታሰበ እሰጣ አገባ ውስጥ በመግባታቸው ስምምነቱ መቋጫ ሳያገኝ ነበር የተመለሱት።
