የሆሊውድ ፊልም ኢንዱስትሪ

ከ 1 ሰአት በፊት

የኦስካር ሽልማት በተካሄደባት ትናንት ምሽት፣ የካቲት 23/ 2017 ዓ.ም ሆሊውድ በርዕደ መሬት ተመትታ ነበር ተባለ።

የርዕደ መሬቱ ማዕከል የነበረው የኦስካር ሽልማት ከተዘጋጀበት ሰሜናዊ ሆሊውድ፣ ዶልቢ ቲያትር አቅራቢያ መሆኑም ተገልጿል።

3.9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበው ርዕደ መሬት ስላደረሰው ጉዳት የተገለጸ ነገር የለም።

ርዕደ መሬቱ የተከሰተው የኦስካር ሽልማትን ተከትሎ ታዋቂው ቫኒቲ ፌይር መጽሄት በሚያዘጋጀውና በርካታ ታዋቂ ሰዎች ድግስ ላይ ተሰባስበው በነበረበት ወቅት ነው።

ርዕደ መሬቱ የተከሰተበት ሰዓት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ነበር።

በስፍራው የነበሩ ሰዎች ድንገተኛ ኃይል እንደተሰማቸው የገለጹ ሲሆን ከፍ ያሉ ህንጻዎች ሲንቀጠቀጡ ያዩ በርካቶችም ሲጮሁ እንደነበር ተነግሯል።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ርዕደ መሬቱ በሎስ አንጀለስ ከተማ በርካታ ኪሎሜትሮችን ርቀት በሸፈነ መልኩ መሰማቱን ሪፖርት አድርጓል።

የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ መከላከያ ርዕደ መሬቱ የተሰማበት ንዝረት የሎስ አንጀለስ ከተማን ቢያካልልም መስሪያ ቤቱ በተፈጠረው ክስተት “የመሬት መንቀጥቀጥ” ስጋት አልገባኝም ብሏል።

ጠንከር ያሉ ርዕደ መሬቶች በሚከሰቱበት ወቅት የመጀመሪያ ምላሽ ሰጪዎች እና ባለስልጣናት በህንጻዎች እና መሰረተ ልማት ላይ የደረሰ መዋቅራዊ ጉዳት መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ግምገማ ያደርጋሉ።

የኦስካር ሽልማት

በአሁኑ ወቅት በደቡባዊ ካሊፎርኒያ የተከሰተው ይህ ርዕደ መሬት በቀናት ውስጥ 40ኛው መሆኑን ተገልጿል። ሆኖም ከዚህኛው በፊት የነበሩት እነዚህ በርካታ ርዕደ መሬቶቹ በሬክተር ስኬል 1 ሲሆኑ በርካታ ነዋሪዎችም መከሰታቸውን አልተሰማቸውም ተብሏል።

ባለፈው ወር 3.7 ሬክተር ስኬል የተለካ ርዕደ መሬት በካሊፎርኒያ የምትገኘውን ማሊቡን መትቷል።

ከጥቂት ወራት ከፍተኛ የተባለ 7 ሬክተር ስኬል ርዕደ መሬት ሰሜናዊ ካሊፎርኒያን መትቷት ነበር።

በፊልሙ ዘርፍ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን የኦስካር ሽልማትን በሆሊውድ ይዘግቡ የነበሩ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ድንገተኛው የመሬት ርዕደ መሬት ሲከሰት በስፍራው ላይ የነበሩ ሲሆን፤ በርካቶች በድንጋጤ መጮሃቸውን ሪፖርት አድርገዋል። አንዳንዶች የቦምብ ፍንዳታ የመሰላቸው አልታጡም ።

አንዲት ነዋሪ በህይወቷ የተሰማት ከባዱ ርዕደ መሬት መሆኑን ገልጻ፤ ይህ በሬክተር ስኬል 3.9 ብቻ መሆኑ እንዳስገረማት ተናግራለች።

“እስከ ጥፍሬ ድረስ ነው የተሰማኝ” ስትል ተናግራለች።

ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት ወቅት የቢቢሲዋ ኤማ ቫርዲ ለመጨረሻ የኦስካር ፊልም ቀረጻ ሜካፕ እየተቀባች ነበር። ድንገትም ያጠለቀችው የአልማዝ ጆሮ ጌጥ በራሱ ሲንቀሳቀስ እንዲሁም ባለ አስራ አምስት ፎቅ ህንጻው እየተንቀጠቀጠች መሆኑን ተረዳች።

ይህንን ያህል ከፍታ ያለው ህንጻ በዚህ መልኩ ሲንቀጠቀጥ መሰማቱ ለየት ያለ እንደነበር አስረድታለች።