
3 መጋቢት 2025, 17:04 EAT
በኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ሊቀመንበር አብዲራህማን ማህዲ የሚመራው የፓርቲው ክንፍ፤ ከአሁን በኋላ “ከመንግሥት ጋር ግንኙት እንደማያደርግ” እና ቀጣይ የትግል ስልቱን በተመለከተ ለመወሰን “ከሕዝብ ጋር ውይይት ሊያደርግ” መሆኑን ለቢቢሲ ገለጸ።
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆኑን የገለጸ ሌላ ቡድን በአንጻሩ ባወጣው መግለጫ፤ይህ አቋም “ፓርቲውን የማይወክል” መሆኑን አስታውቋል።
ከስድስት ዓመታት በፊት የትጥቅ ትግልን በማቆም ወደ አገር የገባው ኦብነግ ይህንን አቋሙን ያስታወቀው ትናንት የካቲት 23/2017 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ ባወጣው መግጫ ነው።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ የነበረው ኦብነግ፤ ወደ ሰላማዊ ትግል የገባው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን መምጣት በኋላ ጥቅምት 2011 ዓ.ም ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ በመድረሱ ነው።
ከስድስት ዓመት በፊት በኤርትራ አሥመራ ከተማ በተደረገው ስምምነት ኦብነግ ሲታገልለት የነበረውን “የኦጋዴን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በተመለከተ ተከታታይ ውይይቶችን” በማድረግ መፍትሔ ለመስጠት መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አብዲቃድር አዳኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኦብነግ፤ ይህ ጥያቄ እንዲመለስ በሶማሌ ክልል ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ፍላጎት እንዳለውም አስረድተዋል።
ቃል አቀባዩ እንደሚያስረዱት በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን “ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ቅሬታዎች እንዲሁም መገለል” ጉዳይን ከመሰረቱ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበርም አስታውሰዋል።
“የኦብነግ ታጣቂዎችን ወደ ክልሉ የጸጥታ ኃይል ማስገባት” እና “በጦርነት ለተጎዱ የመልሶ ማቋቋም” ተግባራትን ማከናወንም ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሆኑም ገልጸዋል።
ይሁንና እነዚህ በወቅቱ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች “አለመፈጸማቸውን” ቃል አቀባዩ ይናገራሉ። ኦብነግ የነበሩት “18 ሺህ ታጣቂዎች በየቦታው መበተናቸውን” አክለው ተናግረዋል።
- “አጋሮቻችን በዚህ ጦርነት ወራሪው ማን እንደሆነ እንዲያስታውሱ እንፈልጋለን” ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ3 መጋቢት 2025
- የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ለዩክሬን የሰላም ዋስትና ለመስጠት ‘የፈቃደኞች ጥምረት’ መመስረቱን አስታወቁ3 መጋቢት 2025
- ደም በመለገስ የ2.4 ሚሊዮን ሕፃናትን ሕይወት የታደጉት አውስትራሊያዊ ሞቱ3 መጋቢት 2025
ኦብነግ፤ ከስድስት ዓመት በፊት የተደረሰውን ስምምነት “ለመመለስ እና ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች” እንዲተገበሩ ለማድረግ “ላለፉት ስምንት ወራት ጥረት ሲያደርግ” መቆየቱን አቶ አብዲቃድር ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ጅቡቲ ላይ ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞ አለመሳካቱን የሚናገሩት አቶ አብዲቃድር፤ ቀጥሎም ኬንያ ላይ ለመወያያት ስምምነት እንደነበር አንስተዋል። እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ የኬንያውን ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው ላለፈው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 18/2017 ዓ.ም. ነበር።
ፓርቲው ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይም በኬንያ ሊደረግ ነበር ስለተባለው ንግግር የጠቀሰ ሲሆን “የፌደራሉ መንግሥት፤ የገባውን ቃል በመፈጸም ፈንታ ድርድሩን ትቶታል” ሲል ከስሷል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሀሰንም “ከኦብነግ ጋር የተገናኙ በማስመሰል የሀሰት ሕዝባዊ ሁነት አዘጋጅተዋል” ሲል ወቀሳውን አሰምቷል።
የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ አብዲቃድር፤ “የሶማሌ ክልል መንግሥት፤ ከራሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ጥቂት አባላት ጋር ንግግር በማድረግ ኦብነግን ለመከፋፈል ሞክሯል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከክልሉ መንግሥት ጋር የተገናኙት “እ.አ.አ በ2020 ከፓርቲው የተሰናበቱ” አባላት ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ጉዳዮች ተከትሎም ኦብነግ “ከአሁን በኋላ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት እንደማያደርግ” ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
“ኦብነግ፤ ሆነ ብሎ የሰላም ሂደቱን ካፈረሰ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከዘጋ መንግሥት ጋር ከአሁን በኋላ ግንኙነት አያደርግም” ሲል ውሳኔውን ገልጿል።
ፓርቲው አክሎም፤ “እነዚህን ጉዳዮች ተከትሎም ኦብነግ፤ የሶማሌ ሕዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ ፍትህ እና ክብር ለማረጋገጥ በንቃት አማራጭ ጎዳናዎችን እያፈላለገ ነው” በማለት በመግለጫው አስፍሯል።
ይህንን የመግለጫው ክፍል እንዲያብራሩ ጥያቄ የቀረበላቸው የኦብነግ ቃል አቀባይ አቶ አብዲቃድር፤ “ከስምምነቱ ወዲህ የነበሩ ሁኔታዎችን በዝርዝር ለመግለጽ” ሕዝባዊ ውይይት እንደሚያካሂድ እንዲሁም ቀጥሎ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በማድረግ “ቀጣይ ፖለቲካዊ ምዕራፉን እንደሚወስን” ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ኦብነግ ከአሁን በኋላ የሚቀጥለው በሰላማዊ ወይስ በትጥቅ ትግል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ አሁን ላይ “እንታገላለን ማለት አልችልም። ሰላማዊ ትግል እንቀጥላለንም ማለት አልችልም፤ ምክንያቱም አንችልም። ሁልጊዜ ጥቃት [ይፈጸማል]። ቢሯችንንም ዘግተዋል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ሕዝባችንን እናማክራለን። በሩን እና ንግግሩን ለድርጅቱ አመራር ብቻ ሳይሆን [ለሁሉም] በስፋት ለመክፈት እንሞክራለን” ሲሉ ፓርቲው ቀጣይ የትግል ስልቱን ለመወሰን ሕዝባዊ ውይይቶችንን እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።
“በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንችላለን ወይስ ትተነው መታገል አለብን?” የሚለው በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ ለንግግር እንደሚቀርብም አስታውቀዋል። ሕዝባዊ ውይይቱ የሚደረገው በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ አገራት ከሚገኙ የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት ጋር እንደሆነም አክለዋል።
ኦብነግ ሕዝባዊ ውይይቱን የሚያካሂደው ከሶማሌ ሕዝብ “ቁርጠኝነት ስለሚያስፈልገው” እንደሆነ አስረድተዋል።
እነዚህ ውይይቶች በተያዘው መጋቢት ወር ለማካሄድ እንደታሰበ የገለጹት አቶ አብዲቃድር፤ በሚያዝያ ወር ደግሞ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
“የመጨረሻው ውሳኔ” የሚተላለፈውም በማዕከላዊ ኮሚቴው በሚደረገው ስብሰባ እንደሆነ ገልጸዋል።
በሊቀመንበሩ አብዱራህማን ማህዲ የሚመራው ኦብነግ ይህንን ቢልም ከፓርቲው “ማዕከላዊ ኮሚቴ” እንደተሰጠ የተጠቀሰ ሌላ መግለጫ ይህንን አቋም ውድቅ አድርጎታል።
በሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የፌስቡክ ገጽ ላይ የተለጠፈው ይህ መግለጫ “ከናይሮቢ ኬንያ የተሰጠው መግለጫ ከኦብነግ እውቅና ውጪ” መሆኑን አስታውቋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን ጥሷል” በሚል የተሰጠው መግለጫ “ከድርጅቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈፃሚ አባላት እውቅና ውጭ በተወሰኑ ግለሰቦች ፍላጎት የወጣ” ነው ብሏል።
ቡድኑ፤የሰላም ስምምነቱን እንደሚደግፍ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው ጠቅሷል።
“እስካሁንም የፌዴራል እና የሶማሌ ክልል መንግሥት ለአሥመራው ስምምነት ተግባራዊነት ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅናን እንሰጣለን” ብሏል።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደንብ መሰረት “በቅርቡ ጉባኤ እንደሚካሄድ” የገለጸው መግለጫው፤ “በጉባኤው ሰላማዊ ትግሉን የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን” እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል።
ቢቢሲ ይህንን መግለጫ በተመለከተ ከቡድን አመራሮች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።