በሞት የተቀጣችው ሽሃዛዲ ክሃን

ከ 6 ሰአት በፊት

ህንዳዊቷ የቤት ሰራተኛ የአሰሪዎቿን ህጻን ልጅ ገድለሻል በሚል ወንጀል ተከሳ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መዲና አቡዳቢ በሞት ተቀጣች።

ለህንዳውያን ባልና ሚስት ትሰራ የነበረችው ሽሃዛዲ ክሃን ባለፈው ወር መገደሏን የህንድ መንግሥት አስታውቋል።

ግለሰቧ ህጻኑን ማፈኗን የአቡዳቢ ፍርድ ቤት ሰነድ ቢያሳይም ነገር ግን በችሎቱ ላይ የመሰከሩት ዶክተር የአስከሬን ምርመራ ለማድረግ ስላልተፈቀደላቸው ይህንን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በሞት የተቀጣችው ግለሰብ ቤተሰቦች ልጃቸው ንጹህ መሆኗን በመግለጽ፤ የአራት ወሩ ህጻን ህይወቱ ያለፈው በተሳሳተ ክትባት መሆኑን ተናግረዋል።

ግለሰቧ በችሎቱ ሂደት ወቅት የህግ ባለሙያ “በቂ ውክልና አላገኘችም” ሲሉ ወቅሰዋል።

የግለሰቧ የሞት ቅጣት የተፈጸመው የካቲት 8/ 2017 ዓ.ም ቢሆንም የህንድ ባለስልጣናት ያረጋገጡት ከትናንት በስቲያ፣ የካቲት 24 ነው። የግለሰቧ ቤተሰቦች ስለ ልጃቸው መረጃ ለመጠየቅ የደልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባታቸውን ተከትሎ ነው ዜናው ይፋ የሆነው።

የግለሰቧ ግድያ በሚስጥራዊነት መያዙ በበርካታ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ህንድ እና የአረብ ኤምሬቶች የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህንዳውያን በአረብ ኤምሬቶች በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።

ሽሃዛዲ በአውሮፓውያኑ 2021 ለህንዳውያኑ ቤተሰብ ልጁን ለመንከባከብ ወደ አቡዳቢ ማቅናቷን ቤተሰቦቿ ለፍርድ ቤት ካቀረቡት አቤቱታ መረዳት ይቻላል።

የሽሃዛዲ ክሃን ቤተሰቦች

በቤታቸው ከተቀጠረች ከጥቂት ወራት በኋላ ህጻኑ የተወለደ ሲሆን የሷም ዋነኛ ስራ የልጁ እንክባካቤ እንደሆነ ተገልጿል። የሽሃዛዲ አባት እንደሚሉት ልጃቸው አብዛኛውን ጊዜ በህንድ ለሚገኙት ቤተሰቦቿ ትደውል እንደነበር እና ህጻኑንም በቪዲዮ ታሳየን ነበር ብለዋል።

ህጻኑ ከሞተ በኋላ የልጃቸው የስልክ ጥሪ የቆመ ሲሆን በኋላም ሽሃዛዲ በእስር ላይ እንዳለች ተረዱ። እንደ ሽሃዛዲ ቤተሰብ ከሆነ በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 7/ 2022 ዓ.ም ህጻኑ ክትባቱን ከወሰደ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ህይወቱ አልፏል። ሽሃዛዲ ከሁለት ወራት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች።

ህጻኑን መግደሏን እንድታምን ተገዳ የተናዘዘችበት ቪዲዮ እንደተቀረጸ እና በፍርድ ቤትም ተገቢውን የህግ ድጋፍ እንዳላገኘች ተናግራ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2023 የሞት ፍርድ ተፈረደባት፤ በዓመቱ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበችው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ። የሽሃዛዲ ቤተሰቦች ለመጨረሻ ጊዜ ከልጃቸው የሰሙት ከመገደሏ ሁለት ቀናት በፊት ሲሆን ስልክ ደውላም በማግስቱ ልትገደል እንደምትችል ነግራቸው ነበር።

“አምርራ እያለቀሰች ነበር። የተለየ ክፍል ውስጥ እንደገባች እና በህይወት እንደማትወጣም እንዲሁም የመጨረሻዋ የስልክ ጥሪ ሊሆን እንደሚችል ነገረችን” ሲሉ አባትየው ሻቢር ክሃን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚያን በኋላ ከልጃቸው ምንም ያልሰሙት ቤተሰቦች ያለችበትን ሁኔታ ለመረዳት ለደልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን አቀረቡ።

የሞት ቅጣት እንደተፈጸመባት የተረዱት ቤተሰቦች “በቂ ህጋዊ ውክልና አልነበራትም። ይህም በሞት ፍርድ እንድትቀጣ ሆኗል” ብለዋል።

“ፍትህ አላገኘችም። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሯሯጥኩ ነበር። ሁሉም ቦታ ሞክሬያለሁ። አቡዳቢ ለመሄድም ሆነ ጠበቃ ለመቅጠር ገንዘብ አልነበረኝም” ሲሉ አባትየው ለህንድ ፕሬስ ትረስት ተናግረዋል።